ኮሮናቫይረስ፡ በእንግሊዝ በየቀኑ ወደ 100 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በቫይረሱ ይያዛሉ

ጭምብል ያጠለቀች ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በእንግሊዝ ውስጥ ወደ 100 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በየቀኑ በኮሮናቫይረስ እንደሚያዙ አንድ ጥናት ጠቆመ፡፡

እንደለንደን ኢምፔሪያል ኮሌጅ ጥናት ከሆነ ወረርሽኙ በፍጥነት እየጨመረ ሲሆን በየዘጠኝ ቀናትም በበሽታው የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር በእጥፍ ይጨምራል፡፡

አጥኚዎቹ "ወሳኝ ደረጃ ላይ በመሆናችን አንድ ነገር መደረግ አለበት" እያሉ ነው፡፡

ፈረንሳይ እና ጀርመን ቫይረሱን ለመቆጣጠር የተለያየ ደረጃ ያለው ገደብ ጥለዋል፡፡

በፀደይ ወራት ከፍተኛ ደረጃ ደርሶ ወደ ነበረበት ደረጃ በፍጥነት እየተቃረብን ነው በማለት ባለሙያዎቹ ያስጠነቅቃሉ፡፡

ጥናቱ ወቅታዊ የሆነው የኮቪድ -19 ጥናት በመሆኑ ተጽዕኖ ፈጣሪ ነው ተብሎለታል፤ 86 ሺህ የሚጠጉ በጎ ፈቃደኞች የተሳተፉበት እና የመጨረሻዎቹ ምርመራዎች እሁድ የተካሄደበት ጥናት መሆኑን በመጠቆም፡፡

ጥናቱ እንዳሳየው ቫይረሱ በሁሉም የእድሜ ክልል እና በእያንዳንዱ የእንግሊዝ ግዛት እየጨመረ መሆኑን ያሳያል ፡፡

በአሁኑ ጊዜ በሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል ስርጭቱ ከፍተኛ ቢሆንም በደቡብ በኩል ቢሆን በፍጥነት እያደገ ነው፡፡

ከአጥኚዎቹ አንዱ የሆኑት ፕሮፌሰር ስቲቨን ሪሌይ መረጃው መገኘት ሲጀምር እንዳዘኑ ገልፀው "አሁን ያሉት እርምጃዎች በቂ አይደሉም" ብለዋል ፡፡

"ለውጥ መኖር አለበት። ፍጥነት በእውነቱ በጣም ፈጣን በመሆኑ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ከገና በፊት ለውጥ ሊኖር ይገባል" ብለዋል ፡፡

ህዝቡ በደንብ ህጎችን ማክበር አለበት ወይም መንግሥት ከባድ ገደቦችን መጣል አለበት ሲሉም ተከራክረዋል ፡፡

"መረጃዎቹ በፍጥነት መወሰንን የሚሹ ናቸው" ብለው ገልጸዋል።