ኮሮናቫይረስ፡ በቫይረሱ የተያዘ ሰው ያልተገኘባት የሰሜን አሜሪካ ክፍል

የፎቶው ባለመብት, Alamy
በኮቪድ-19 የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በአንዳንድ የካናዳ አካባቢዎች እየጨመረ ቢሆንም አንዲት በሰሜናዊ በኩል የምትገኝ አካባቢ ግን ቫይረሱ በማህበረሰቡ ውስጥ እስካሁን አልገባም። ቦታዋም 'ኑናቩት' ትባላች።
ባለፈው መጋቢት ወር በርካታ የዓለማችን አገራት ድንበራቸውን እየዘጉ በነበረበት ወቅት የኑናቩት ኃላፊዎችም ቢሆኑ የሚመጣውን አደጋ በማሰብ የጥንቃቄ እርምጃ ለመውሰድ ወስነው ነበር።
በዚህም ከካናዳ የሚመጡ ሰዎችን በተመለከተ ጠበቅ ያለ እርምጃ የተወሰደ ሲሆን ከነዋሪዎች በስተቀር ማንም ሰው ከካናዳ በኩል ወደ ኑናቩት መግባት አይችልም ነበር።
ነዋሪዎችም ቢሆኑ ከሌላ ቦታ ሲመጡ ለሁለት ሳምንታት እራሳቸውን ለይተው መቀመጥ ግዴታቸው ሲሆን መንግሥት ባዘጋጃቸው ለይቶ ማቆያዎች አልያም እንደ ዊኒፔግ፣ የሎውናይፍ፣ ኦታዋ እና ኤድመንተን ባሉ ከተሞች ውስጥ በሚገኘኑ ሆቴሎች እንዲቆዩ ይደረጋሉ።
የመንግሥት ጥበቃ ኃይሎችም ቢሆኑ በለይቶ ማቆያዎቹ እና ሆቴሎቹ አካባቢ ከፍተኛ ጥበቃ ያደርጋሉ። እስካሁንም 7 ሺ የሚሆኑ የኑናቩት ነዋሪዎች ወደቤታቸው ሲመለሱ በነዚህ ማዕከላት ሁለት ሳምንታትትን አሳልፈዋል።
ነገር ግን ይህ ሁሉ ስራ አልጋ በአልጋ አልነበረም። አንዳንድ ሰዎች ሕጉን በመጣሳቸው ምክንያት ለተጨማሪ ቀናት በለይቶ ማቆያ ማዕከላቱ እንዲቆዩ ተደርገዋል። በማዕከላቱ ውስጥ የነበሩ ሰዎችም የምግብ ጥራት ችግር እንዳለ ገልጸዋል።
ነገር ግን በመላው ካናዳ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ሲመጣና በጎረቤት አካባቢዎች ከፍተኛ የጥንቃቄ እርምጃዎች መወሰድ ሲጀምሩ ኑናቩት ግን እንድም በቫይረሱ የተያዘ ሰው አላገኘችም።
በኑናቩት ወደ 36 ሺ የሚጠጉ ሰዎች የሚኖሩ ሲሆን 25 ማህበረሰቦች ሁለት ሚሊዮን ስኩዌር ኪሎሜትር የሚሸፍን ቦታ ላይ ተበታትነው ኑሯቸውን ይገፋሉ። በሰዎቹ ተፈጥሮአዊ የአኗኗር ዘይቤ ምክንያት አካላዊ ርቀትን መጠበቅ በጣም ቀላል ነው።
ነዋሪዎቹ ያን ያክል ስፋት ባለው ቦታ ላይ ሲኖሩ ከሰዎች ጋር የመገናኘት ዕድላቸው በጣም ዝቅተኛ ነው። መንግሥትም ቢሆን ነዋሪዎቹን በዓመት አንዴም ይሁን ሁለቴ የሚያገኛቸው በአውሮፕላን በመታገዝ ነው።
በመስከረም ወር መጨረሻ አካባቢ ግን ማዕድን ማውጣት ላይ የተሰማሩ ሰራተኞች ከኑናቩት 160 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ አካባቢ በኮሮረናቫይረስ መያዛቸው ተዘግቦ ነበር።
ነገር ግን እነዚህ ሰራተⶉች ወደ ክልሉ ባለመግባታቸው አሁንም ነዋሪዎቹ ከኮሮረናቫይረስ ነጻ ናቸው ተብሏል።
ነዋሪዎቹ ወደ ማዕድን አውጪዎቹ አልያም ማዕድን አውጪዎቹ ወደ ነዋሪዎቹ ምንም አይነት ጉዞ ባለማድረጋቸው ቫይረሱ ባለበት ሊቀር ችሏል።
ነገር ግን በዚህ አካባቢ እንደ ፈተና የሚቆጠረው በተገቢው መልኩ የኮሮረናቫይረስ ምርመራ ማድረግ አለመቻሉ ነው። መመርመሪያ መሳሪያዎች በአውሮፕላን በመታገዝ ተበታትነው ወደሚኖሩት ማህበረሰቦች መድረስ አለበት።
በሆነ አጋጣሚ የሆነ ሰው ቫይረሱ ቢገኝበት ከሌሎች ሰዎች ጋር ንክኪ ከማድረጉ በፊት መረጃውን ለማድረስ አልያም ንክኪ ያላቸውን ሰዎች ለመለየት በጣም ከባድ ያደርገዋል።
በተጨማሪም የጤና አገልግሎት መስጫዎች በአካባቢው በበቂ ሁኔታ የሉም። 'ኪኪታኒ' በመባል የሚታወቀው ሆስፒታል ለጽኑ ህሙማን የሚሆኑ 35 አልጋዎች ያሉት ሲሆን በኮቪድ-19 የተያዙ 20 ታማሚዎችን ብቻ ነው ማስተናገድ የሚችለው።
ምናልባት ወረርሽኙ በዚህ አካባቢ ቢከሰት ሕክምና የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች ተገቢውን ክትትል ለማድረግና ለይቶ ማቆያዎችን ለማቋቋም አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል።
ይህ በንዲህ እንዳለ በኑናቩት የሚኖሩት 'ኢኑይት' በመባል የሚታወቁት ቀደምት ማህበረሰቦች ለኮሮረናቫይረስ ተጋላጭ ከሚባሉት መካከል ናቸው።
በቂ ያልሆኑና ደህንነታቸው ያልተጠበቁ ቤቶች፣ በአንድ ቦታ ላይ በርካታ ሰዎች ተሰብስበው መኖር እንዲሁም የቲቢ በሽታ ስርጭት ተጋላጭ ያደርጋቸዋል።
80 በመቶ የሚሆነውን የኑናቩት ነዋሪ የሚሸፍኑት ኢኑይቶች ከሌሎች ነዋሪዎች አንጻር በቲቢ የመያዝ ዕድላቸው 300 በመቶ ከፍ ያለ ነው።
ካናዳ በአጠቃላይ እንደ ሙሉ የእንቅስቃሴ ገደብ ያሉ የጥንቃቄ እርምጃዎች በመውሰዷ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ሞክራለች።ነገር ግን አሁንም ቢሆን ለመቆጣጠር አልቻለችም።
እስካሁንም ድረስ 191 ሺ 732 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን 9 ሺ 699 ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ምክንያት ሕይወታቸው አልፏል።
ነገር ግን እንደ ኪቤክና ኦንታሪዮ ባሉ በርካታ ሰዎች በሚኖሩባቸው ግዛቶች በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ መጥቷል።
በአሁኑ ሰአት 77 ሺ የሚሆኑ ካናዳውያን በየቀኑ የኮሮረናቫይረስ ምርመራ የሚደረግላቸው ሲሆን የአገሪቱ ግብ ግን በየቀኑ 200 ሺ ሰዎችን ለመመርመር ነው።












