በሶማሊያ ፀረ-ፈረንሳይ ሰልፍ ተካሄደ

በሶማሊያ የተደረገው የተቃውሞ ሰልፍ

የፎቶው ባለመብት, Garowe Online

በሶማሊያ በርካታ ከተሞች ፈረንሳይንና ፕሬዚዳንት ማክሮንን የሚያወግዙ የተቃውሞ ሰልፎች ተካሄዱ።

ሰልፉ ፈረንሳይ የነብዩ መሃመድ የካርቱን ምስል በማተሟ እንዲሁም ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ይህንኑ ደግፈው የሰጡትን አስተያየትም በተመለከተ የተደረገ የተቃውሞ ምላሽ ነው።

በመዲናዋ ሞቃዲሾ የተቃውሞ ሰልፈኞቹ ዋና አውራ ጎዳናዎችን ከመዝጋት በተጨማሪ መፈክሮችን እያሰሙ እንዲሁም የፈረንሳይን ሰንደቅ አላማን በመርገጥና በመቃጠል ተቃውሟቸውን ገልፀዋል።

አንደኛው ተቃዋሚ ሂላል አብዱራህማን ለፈረንሳዩ የዜና ወኪል አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደተናገረው በእንደዚህ አይነት የተቃውሞ ሰልፍ ሲሳተፍ የመጀመሪያው መሆኑን ነው።

አክሎም በዚህ የተቃውሞ ሰልፍ ባይሳተፍ "በራሱ ያፍር" እንደነበር ገልፆ ማክሮን ላይ የተሰማውን ንዴትም መግለፅ እንደነበረበት አበክሮ ተናግሯል።

"ማክሮን ነብያችን መሃመድ እንዲሰደቡ ድጋፍ አድርገዋል። ነብያችን ከፍ ያድርጋቸውና" ብሏል።

የ X ይዘትን ይለፉት
ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

ማሳሰቢያ፡ የሦስተኛ ወገን ይዘቶች ማስታወቂያ ሊኖራቸው ይችላል

የ X ይዘት መጨረሻ

ሌላኛው ተቃዋሚ አህመድ ሼክ ሚሬም በበኩሉ "ማክሮን በርካታ የእስልምና እምነት ተከታዮችን ቆስቁሰዋል፤ በአሁኑ ወቅት አማኙም በፈረንሳይ ላይ ያለውን ቁጣ በመግለፅ ላይ ነው። ይሄ ሁሉ የማክሮን ስራ ነው" ብሏል።

በሶማሊያ ብቻ ሳይሆን በርካታ የእስልምና እምነት ተከታዮች ባሏቸው አገራትም ፕሬዚዳንት ማክሮን በሰጡት አስተያየት ቁጣቸውን እየገለፁ ይገኛሉ።

በርካታ የእስልምና እምነት ተከታዮች ባሉዋቸው ባንግላዴሽ፣ ኩዌት፣ ዮርዳኖስና ሊቢያ በመሳሰሉት አገራትም የፈረንሳይ ምርቶችን አንገዛም በሚል የማእቀብ ጥሪ ተደርጓል።

ውዝግቡ በተለይ የተጧጧፈው የነብዩ መሃመድን ካርቱን በክፍል ውስጥ በማሳየቱ በአሰቃቂ ሁኔታ ተቀልቶ የተገደለው ፈረንሳያዊው መምህርን ተከትሎ ፕሬዚዳንቱ ባደረጓቸው ንግግር ነው።

ፕሬዚዳንት ማክሮን መምህር ሳሙኤል ፓቲ "የተገደለበት ምክንያት የእስልምና እምነት ተከታዮች የወደፊቱ እጣ ፈንታችንን መቆጣጠር ስለሚፈልጉ ነው። ፈረንሳይ ካርቱኗንም ቢሆን አሳልፋ አትሰጥም" ብለዋል።

የነብዩ መሃመድን ምስል በየትኛውም ሁኔታ ማሳየት በእስልምና እምነት ነውርና አፀያፊ ተደርጎም ይቆጠራል። ሆኖም ፈረንሳይ ከእምነት ውጭ ያለ አገዛዝን እንደመከተሏ መጠን የመናገር ነፃነትን የሚቀለብስ ነው ነው በማለትም ትከራከራለች።