የአሜሪካ ምርጫ፡ ስለ ምርጫው ቀን መታወቅ የሚገባቸው ነገሮች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ጥቅምት 24 የምርጫ ካርዳቸውን የወሰዱ አሜሪካውያን ዶናልድ ትራምፕን አልያም ጆ ባይደንን ፕሬዝዳንታቸው አድርገው ለመምረጥ ድምጻቸውን የሚሰጡበት ቀን ነው።
በምርጫው ቀን በርካታ ግራ የሚያጋቡ መረጃዎች እንደሚወጡ የሚገመት ሲሆን፤ ሁሉም ሊያውቃቸው የሚገቡ ወሳኝ መረጃዎችን እናካፍላችሁ።
• የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫን ለማሸነፍ ብዙ ድምጽ ማግኘት ብቻ በቂ አይደለም። በኢሌክቶራል ኮሌጅ የምርጫ ሥርዓት መሠረት ሁለቱም ተፎካካሪዎች ካሉት 538 ድምጾች ቢያንስ 270 ለማግኘት ነው እየታገሉ ያሉት።
• ከዚህ በፊት ከነበሩት ምርጫዎች አንጻር በዘንድሮው ምርጫ ላይ በርካታ ሚሊየን አሜሪካውያን በፖስታ ድምጽ ይሰጣሉ። ይህ ማለት ደግሞ የምርጫ ውጤቱ ተቆጥሩ ይፋ እስከሚደረግ ተጨማሪ ቀናት ሊወስድ ይችላል ማለት ነው።
• የአሜሪካ የምርጫ ትንቅንቅ የምርጫ ዕለት ብቻ የሚታይ አይደለም። የቅድመ ምርጫ ምርጫም አለው። ድምጽ ሰብሳቢ ድርጅቶች የትኛውን ዕጩ ነው የምትመርጡት? እያሉ ከአሜሪካውያን የሚሰበስቡትን ድምጽ ይፋ የሚያደርጉበት ነው ቅድመ ምርጫ ማለት።
በዘንድሮው ቅድመ ምርጫ ድምጽ ጆ ባይደን ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕን እየመሩ ይገኛሉ። በተሰበሰቡት ድምጾች መሠረት ባይደን ከትራምፕ ቢያንስ በ10 ነጥቦች ልቀው ይገኛሉ።
የቅድመ ምርጫ ድምጾች የትኛው ዕጩ በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት እንዳለው ማሳያ ናቸው።
ነገር ግን ምርጫውን አሸናፊ ማነው? የሚለውን በትክክል ላይጠቁሙ ይችላሉ።
ለምሳሌ በጎርጎሳውያኑ 2016 ሂላሪ ክሊንተን በቅድመ ምርጫው ትራምፕን አስከንድተው ሲመሯቸው ነበር። ነገር ግን በዋናው ምርጫ መሸነፋቸው አይዘነጋም።
በምርጫው ማን እያሸነፈ ነው የሚለውን እንዴት ማወቅ ይቻላል?
በአሜሪካ ሁሉም ግዛቶች በፖስታ በኩል የሚመጡ ድምጾችን እንዴትና መቼ እንደሚቆጥሩ የተለያየ ሕግና ደንብ አላቸው። በዚህ ምክንያት ማን አሸነፈ? የሚለውን በተመሳሳይ ጊዜ ማወቅ አይቻልም።
እንደ ፍሎሪዳ እና አሪዞና ያሉ ግዛቶች ከጥቅምት 24 በፊት የምርጫ ሂደቶችን ማሰናዳት ይጀምራሉ። በዚህም የምርጫ ውጤቱን ቀድመው ይፋ ማድረግ ይችላሉ ማለት ነው።
እንደ ዊስኮንሲን እና ፔንሲልቬኒያ ያሉት ደግሞ እስከ ምርጫው ቀን ድረስ በፖስታ የተላኩትን ድምጾች ንክች አያደርጓቸውም። በነዚህ ግዛቶች ደግሞ አጠቃላይ ውጤቱ ይዘገያል።
ሌላው አወዛጋቢ ጉዳይ ደግሞ በፖስታ በኩል እስከመቼ መምረጥ ይቻላል? የሚለው ነው።
እንደ ጆርጂያ ያሉ ግዛቶች እስከ ጥቅምት 24 ድረስ ብቻ ባሉት ቀናት የደረሳቸውን ድምጽ የሚቆጥሩ ሲሆን እንደነ ኦሃዮ ያሉት ግዛቶች ደግሞ ፖስታው ላይ ጥቅምት 24 የሚል እስከተጻፈበት ድረስ ዘግይተው የመጡትንም ይቆጥራሉ።
በዚህ ዓመት በርካቶችን ግራ ሊሚያጋቡ የሚችሉ ነገሮች አሉ።
በአንዳንድ ግዛቶች በምርጫው ቀን በምርጫ ጣቢያ ተገኝተው ድምጻቸውን የሚሰጡ ሰዎች ውጤት ቀድመው ያሳውቃሉ።
በነዚህ ግዛቶች ዶናልድ ትራምፕ የበላይነቱን እንደሚወስዱ ይገመታል። ምክንያቱም የትራምፕ ደጋፊዎች በምርጫው ዕለት ወጥተው ድምጽ ለመስጠት በማቀዳቸው ነው።
በሌሎች ግዛቶች ደግሞ ከምርጫው ቀን አስቀድመው በፖስታ በኩል ድምጻቸውን የሰጡ ዜጎችን ድምጽ ውጤት መጀመሪያ ላይ ይፋ ያደርጋሉ።
በነዚህ ግዛቶች ደግሞ ጆ ባይደን የበላይነቱን ሊወስዱ እንደሚችሉ ተገምቷል።
ምክንያቱም ዴሞክራቶች ከሪፐብሊካኖች በተሻለ መልኩ በፖስታ ድምጻቸውን ስለሚሰጡ ነው።
ሌሎች ምርጫዎች
በዘንድሮው ምርጫ ዶናልድ ትራምፕ እና ጆ ባይደን ብቻ አይደሉም የሕዝብ ድምጽ የሚሰጣቸው።
ሁለቱም ፓርቲዎች (ሪፐብሊካን እና ዴሞክራት) የአሜሪካ ምክር ቤት ምርጫን በትኩረት ነው የሚከታተሉት።
በአሁኑ ሰዓት በምክር ቤቱ ሪፐብሊካኖች ከዴሞክራቶች በሦስት ወንበር አብላጫ ወስደዋል።
የትራምፕ ወዳጅ የሆኑት ሊንዚ ግራሃም በደቡብ ካሮላይና በሕይወታቸው አይተውት የማያውቁት ፖለቲካዊ ጦርነት ውስጥ ገብተዋል። ተቀናቃኛቸው ደግሞ ዴሞክራቱ ጄሚ ሃሪሰን ናቸው።
ምንም እንኳን ሊንዚ ግራሃም ከ2003 ጀምሮ በምክር ቤቱ ወንበር ተቆናጥጠው የቆዩ ቢሆንም ለፕሬዝዳንት ትራምፕ ባላቸው ድጋፍ ምክንያት ግን የአንዳንድ መራጮችን ድምጽ አጥተዋል።
በዘንድሮው ምርጫ ሌሎች ነገሮችም የሕዝብ ድምጽ ያስፈልጋቸዋል።
ለምሳሌ የዕጸ ፋርሰ ጉዳይ ትልቅ መነጋገሪያ ነው።
በአሪዞና፣ ሞንታና፣ ኒው ጀርሲ እና ሳውዝ ዳኮታ መራጮች ዕጸ ፋርስ ለመዝናኛ መፈቀድ አለበት በሚለው ላይ ድምጻቸውን ይሰጣሉ።
በተመሳሳይ በሚሲሲፒ ደግሞ መራጮች ዕጸ ፋርስ ለሕክምና መፈቀድ አለበት ወይስ የለበትም በሚለው ላይ ድምጻቸውን እንደሚሰጡ ይጠበቃል።












