የአሜሪካ ምርጫ፡ በኮሮናቫይረስ ተይዘው የነበሩት ትራምፕ ወደ ምርጫ ቅስቀሳቸው ተመለሱ

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, EPA

በኮሮናቫይረስ መያዛቸው የአለም መነጋገሪያ ሆነው የነበሩት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ምረጡኝ ቅስቀሳ ዘመቻቸው ተመልሰዋል።

ፕሬዚዳንቱ በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ከተነገረ ሁለት ሳምንታት አልሞላም።

በሺዎች የሚቆጠሩ አሜሪካውያን በፍሎሪዳ፣ ሳንፎርድ ከአዳራሽ ውጭ በነበረው የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ ላይ ተገኝተዋል።

ደጋፊዎቻቸው የተለመደውን "አራት ተጨማሪ አመታትን ይምሩ" በማለት የዘመሩላቸው ሲሆን ፤ በዝግጅቱ ላይ የተገኙትም ደጋፊዎች ሙቀታቸው እየተለካና ጭምብል እየተሰጣቸው ወደተዘጋጀው ቦታ አቅንተዋል።

ደጋፊዎቻቸው ፕሬዚዳንቱ ከሁለት ሳምንት ባነሰ ወቅት በመምጣታቸው ያላቸውን አድናቆት ገልፀዋል።

"ጀግናዬ" ያላቸውን ዶናልድ ትራምፕ ለማየትም አንድ ግለሰብ ከኒውዮርክ ፍሎሪዳ መምጣቱን ለቢቢሲ ተናግሯል።

አልበገር ባዩ ያሉዋቸው ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳ የጊዜ ሰሌዳቸው መሰረት ከተያዙት የመጀመሪያው ነው የፍሎሪዳ የምረጡኝ ቅስቀሳ ዘመቻቸው።

በሚቀጥሉት ተከታታይ ሶስት ቀናትም በተለያዩ ግዛቶች የምረጡኝ ዘመቻቸውን ያካሂዳሉ ተብለዋል።

ዶናልድ ትራምፕና የዲሞክራቱ ተቀናቃኛቸው ጆ ባይደን ጥቅምት 24፣ 2013 ዓ.ም በሚደረገው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ድምፅ ለማግኘትም ቅስቀሳቸውን አጠናክረውት ይገኛሉ።

በትናንትናው ዕለት ጆ ባይደን በኦሃዮ ንግግር አድርገዋል።

አሁን ባለው ቅድመ ትንበያ መሰረት ጆ ባይደን ትራምፕን በአስር ነጥብ እየመሯቸው ይገኛሉ።

ዶናልድ ትራምፕ በኮሮናቫይረስ የተያዙት ከ11 ቀናት በፊት ሲሆን ዋልተር ሪድ የህክምና ማዕከልም ህክምና ማድረጋቸው ይታወሳል።

ከትናንት በስቲያ እሁድም የግል ዶክተራቸው ትራምፕ ኮሮናን ወደሰው እንደማያስተላልፉ የተናገረ ሲሆን በትናንትናውም ዕለት በተከታታይ በተደረገላቸው ምርመራ ነፃ ሆነው ተገኝተዋል ብሏል።

ሆኖም በየትኞቹ ቀናት ምርመራ እንደተደረገላቸው ከመናገር ተቆጥቧል።