ሩሲያ፡ ራሷን በእሳት አቃጥላ የሞተችው ሩሲያዊት ጋዜጠኛ የመጨረሻ ተቃውሞ

ሩሲያዊቷ ጋዜጠኛ ኢርና ስላቪና ራሷን በእሳት ለኩሳ ህይወቷን ማጥፋቷ አለምን አስደንግጧል። በሞተችባት በዛች እለት ባለቤቷ አሌክሴይ ከባለቤቱ ምንም የተለዬ ባህርይ አላየም።
የእናቷም 70ኛ አመት ልደትም ስለነበር አፕል ኬክም ጋግራ ልታከብር ተዘጋጅታ ነበር።
ወደ ሃያ አምስት ጉዳይ ለስምንት ሰአትም ሲሆን ባለቤቷ ደውሎ አጠር ያለና የተለመደውን ወሬ፣ "ስንት ሰዓት ላይ ነው የምትመጭው?" ተባብለዋል።
ከሁለት ሰዓት በኋላ ግን በህልሙም ቢሆን የማይጠብቀው ነገር ሰማ፤ ስልክ ተደወለላትና ባለቤቱ ኢርና በአገር ውስጥ ሚኒስቴር ፊት ለፊት አካባቢ ራሷን አቃጥላለች ተባለ።
በፌስቡኳ የፃፈችውም የመጨረሻ ነገር " ለሞቴ የሩሲያን ፌዴሬሽን ጥፋተኛ እንድታደርጉ እጠይቃለሁ" የሚል ነበር።
ፅንፍ የወጣ ተቃውሞ
ከሞስኮው በ400 ኪሊሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ኒዝህኒ ግዛት ነዋሪ ነበረች ኢርና።
የኢርና ቅርብ ጓደኞችም ሆነ ቤተሰቦች ጋዜጠኛዋ ምን እንዳቀደች የሚያውቁትም ነገር ስላልነበር ለማስቆምም ጊዜውም አልነበራቸውም።
ነገር ግን ሁሉም የሚስማሙት ተስፋ ቆርጣ ሳይሆን ሆን ብላ ያደረገችው ፖለቲካዊ ተቃውሞ መሆኑን ነው።
"ኢርና ስላቪና ድብርት የሚባል ነገር አያውቃትም" ትላለች የበርካታ አመት ጓደኛዋ ኢርና ኢንኬቫ
"ቀና አስተሳሰብ ያላት፣ ሰዎችን የምታነቃቃ፣ ደግነት፣ ብርሃን የተሞላች ሴትም ነበረች" ትላላች ስለ ጓደኛዋ ምስክርነት ስትሰጥ።
ከሞቷም ጥቂት ጊዜ በኋላም አሟሟቷን የሚያሳይ ቪዲዮም በርካቶች ተመልክተውታል።
ኢርና ስላቪናም ትልቅ ከሚባለው የአገር ውስጥ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ህንፃ ፊት ለፊትም ራሷን ስታቃጥል የሚያሳይ ነው።

የሩሲያ የፖሊስ አባላትን ለመዘከር የቆሙ ሶስት ከነሃስ የተሰሩ ሃውልቶች ያሉበት ወንበር መሀል ተቀመጠች።
እሳቱ ሰውነቷ ላይ የተለኮሰው በግራ እጇ በኩል ሲሆን በሰኮንዶችም ውስጥ መላ ሰውነቷ ሲቀጣጠል ያሳያል።
በአካባቢው ሲያልፍ የነበረ መንገደኛም ጃኬቱን አውልቆ እሳቱን ለማጥፋትና ሰውነቷን ለመሸፈን ሙከራ ቢያደርግም ጋዜጠኛዋ ሁለት ጊዜ የገፈተረችው ሲሆን፣ ከዚያም ወደቀች። የህይወቷም መጨረሻ በዚሁ ተደመደመ።
"መስዋዕትነቴ ትርጉም የሌለው ይሆን?"
" ይህንን ለማድረግ ቁርጠኝነቱ ነበራት" የሚለው ሌላው ጓደኛዋና የዲሞከራሲ ደጋፊ የመብት አቀንቃኝ ሚክሃይል ኢዮሲሌቪች ነው
"እንዲህ አይነት ፅንፍ የወጣ ድርጊት መፈፀሟ ራሷን ለማጥፋት ዝም ብሎ ሳይሆን አቅዳና አስባ ያደረገችው የተቃውሞ መንገድ ነው" ይላል።
ከአመት በፊትም ኢርና ይህንን ሃሳብ በፌስቡኳ ጠቆም አድርጋ ነበር። "ራሴን በእሳት ባቀጣጥል ለሩሲያ ምን ላመጣላት እችላለሁ። የተሻለ ወደፊትስ መፍጠር እችላለሁ? ወይም መስዋዕትነቴ ትርጉም የሌለው ይሆን?" በማለት በፌስቡክ የጠየቀች ሲሆን በርካቶችም በቀልድ መልኩ ነው የወሰዱት።
የሁለት ልጆች እናት የሆነችው ኢርና ከባለቤቷም ጋር የተዋወቁት ገና በአስራ እድሜዎቹ እያሉ ነው። የስራ ህይወቷንም በመምህርነት ሲሆን የጀመረችው ካሉት ህጎችና መመሪያዎች ጋር ተያይዞም በጭራሽ እንዳልተስማማትም ባለቤቷ ይናገራል።
"አለምን በተሻለ መንገድ መቀየር"
በጎሮጎሳውያኑ 2003ም ወደ አንድ የአገሪቱ ጋዜጣም ቢሮ አምርታ ስራ እፈልጋለሁ በማለት ጠየቀች።

የፎቶው ባለመብት, Irina Enikeeva
ባለቤቷ አሌክሴይ እንደሚለው በአዲሷ ስራዋም ነፃነት ይሰማት ጀመር።
ነገር ግን የፕሬስ ነፃነት በሩሲያ ውስጥ ጥያቄ ውስጥ ሲገባ በተለይም ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን አስተዳዳር ፕሬሱን አላፈናፍን የማለታቸው አዝማሚያ እየተጠናከረ ሲመጣም ኢርናም የምትከተላቸው መርሆችዋ ችግር ውስጥ ከተታት፤ ከስራም ተባረረች።
"ፅሁፎች ባለስልጣናቱን እንዲደግፉ በሚል የሚደረገው ጫና ጭንቅላቷ ላይ ይወጣ ጀመር" ይላል ጓደኛዋ
በ2015ም በሚክሃይል ኢዮሲሌቪች ድጋፍ ኮዛ ፕሬስ የሚባል የግል ሚዲያም አቋቋመች።
ነፃ የሆነ ጋዜጠኝነትንም በመከተል ስም አተረፈች። ይህም በባለስልጣናቱ በጎ ነገር አላተረፈላትም።
" ባለስልጣናቱም ሆነ የፀጥታ ኃይሉ ያአለግባብ ኃይላቸውን ሲጠቀሙ ያለ ምንም መፍራት በርካታ ፅሁፎችን ትፅፍ ነበር።
ሳታለሳልስ በድፍረት መፃፏም አልተወደለላትም። በራዳራቸው ዙሪያም ውስጥ አስገቧት" በማለት ጠበቃዋ ኤቭገኒ ጉቢን ይናገራል።
በርካታ ክሶችም ይቀርቡባት ነበር፤ ጠበቃውም በተደጋጋሚ ፍርድ ቤት በመቅረብ ተከራክሮላታል።
ህገ ወጥ ተቃውሞን በማደራጀት፣ የታገዱትን የዲሞክራሲ ደጋፊዎችን ቡድን ጋር አብሮ በመስራትም ክስ ከተመሰረቱባት ጉዳዮች መካከል ይገኙበታል።
ከዚህም በተጨማሪ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ሃሰተኛ ዜናን በማሰራጨት በሚልም እንዲሁ ክስ ተመስርቶባታል።
በአንድ ወቅት የተመሰረተባትን ክስ ስትከራከር "ጨቋኙ ስታሊን አስታወሰን" በማለቷ የአካባቢው ኮሚኒይስቶችን ስሜት ነክተሻል በሚልም 700 ፓውንድ ቅጣት ተጥሎባት ነበር።
"ከነበሩባት ክሶች መካከልም አስር ወይም አስራ ሁለት የአስተዳዳር ጉዳዮች ነበሩ እነዚህም ሁሉ በገንዘብ ተቀጥባቸዋለች። በባለፈው አንድ አመት ከስድስት ወራትም ይቀርቡባት የነበሩ ክሶች ተደጋጋሚም ሆነው ነበር" ይላል ጠበቃዋ።

ሩሲያ ወደ ዴሞክራሲ በምታደርገው ሽግግር በአንድ ወቅት እየመራች ነበር የምትባለው ኒዝህኒ ኖቮጎሮድ ግዛት በቅርቡ ወደኋላ መመለስን አሳይታለች በማለትም በጣት የሚቆጠሩ የሲቪል ማህበረሰቡ መብት ተሟጋቾች ይናገራሉ።
በተቃራኒውም "ፀረ- ፅንፈኝነት" ብሎ በመፈረጅ የአካባቢው ፖሊስ የፖለቲካ ተቃዋሚዎችን ለማፈን ይጠቀምበታልም ተብሏል።
ከኮዛ ፕሬስ ታገኘው የነበረው ገቢም ይህን ያህል ያልነበረ በመሆኑም ፍርድ ቤት የጣለባትን ተደጋጋሚ የገንዘብ ቅጣቶችም ድጋፍ በማሰባሰብ ነበር የምትከፍለው።
"ከጋዜጠኝነቴ ጋር በተያያዘ የሚፈፀምብኝ በቀል ነው" በማለትም በአንድ ወቅት በዩቲዩብ ባስተላለፈችው ቪዲዮም ላይ ተናግራ ነበር።
የቀድሞ የባህር ኃይል ሰራተኛ ባለቤቷም ጋር የጋዜጠኝነት ህይወቷን በዝርዝር ባያወሩም በተደጋጋሚ የተጣሉባት ቅጣቶች "በሃገራችን ላይ ማሸነፍ እንደማንችል ያሳየን ነበር" ይላል ።
አክሎም "እውነት መናገሯ ብዙ አስከፍሏታል፤ ከፍተኛ ጫና እንዲደርስባትም ምክንያት ሆኗል። ይሄም ሁኔታ በጣም ነው የረበሻትም" ይላል።
ኢርና ህይወቷን ከማጥፋቷ በፊት ይደርስባት የነበረውም ጫና በከፍተኛ ሁኔታም ጨምሮ ነበር።
ከአንድ ቀንም በፊት ጥዋት 12 ሰዓት ላይ አስራ ሁለት የታጠቁ ፖሊሶችና መርማሪዎች ቤታቸው ገብተው ለአራት ሰዓትም ያህል ቤታቸውን ገለባብጠው ፍተሻ አካሄዱ።
ይሄም ከጓደኛዋ ሚክሃይል ኢዮሲሌቪች የወንጀል ጉዳይ ጋርም የተያያዘ ነው ተብሏል። ሚክሃይል በየሳምንቱ "የሚበረው ፓስታ ቤተክርስቲያን" በሚል ርእስ በሳቅና ስላቅም ነፃ አስተሳሳብን ለማስፋት በሚልም አንድ ስብሰባ ያካሂድ ነበር።
ሚክሃይል የሩሲያን ፀጥታ ኃይልም አደጋ ውስጥ ከቷል በሚልም እየተወነጀለ ነው። በተለይም ምርጫን እንዴት መከታተልና መቆጣር ይቻላልም በሚል ስልጠና ማካሄዱንም ተከትሎ ነው እንዲህ አይነት ክሶች እየቀረቡበት ያለው።
የሚያዘጋጃቸው ዝግጅቶችም ፕሬዚዳንት ፑቲን ላይ የሰላ ትችት በማቅረብ የሚታወቀው፣ በአገር ውስጥ ታግዶ በግዞት ላይ ያለው ኦፕን ሩሲያ ቡድንም ከጀርባው አለ በማለት መርማሪዎችይ ይናገራሉ።
ሚክሃይልም ሆነ ኦፕን ሩሲያ ይህንን አይቀበሉትም።
ኢርናና ሌሎች ስድስት የመብት ተሟጋቾችም በጉዳዩ ላይ በምስክርነት የተመዘገቡ ሲሆን ሊከሰሱም ይችላሉ ተብሏል።
አንዳንዶች በኒዝህኒ የሚገኘውን ተቃውሞና ትችት ለማፈን የተደረገ ነው ቢሉም ኢርናን ጨምሮ ሌሎች ደግሞ በአካባቢው እየተገነባ ያለው ፓርክ በሙስና መዘፈቁ ጋር ተያይዞ ካለው ተቃውሞ ጋር ያይዙታል።
ለኮዛ ፕሬስ አዘጋጆችም በኢርና ቤት የነበረው ፍተሻ የመጨረሻ ደረጃ ላይ የደረሰ መሆኑ ማሳያ ነው።
"ከሃገራችን የተሰነዘረ ሌላ የጥፊ ምላሽ ነው" በማለት ከሁሉም ራቅ ለማለት ቤተሰቦቹን ይዞ ከከተማ ለመውጣት በዝግጅት ላይ የነበረው ባለቤቷ ይናገራል።
"ኢርና በዚህ ሁኔታ ከፍተኛ ተፅእኖ ነው የደረሰባት፤ በጣምም ተበሳጭታ ነበር" ብሏል።
ኢርና ከሞተችም ከሰዓታት በኋካ በቤቷ የተደረገው ፍተሻና ራሷን ማጥፋቷ ምንም ግንኙነትም ሆነ ተያያዥነት የላቸውም በማለትም የአካባቢው መርማሪ ኮሚቴ አሳውቋል።
የጋዜጠኛዋን ሞት ተከትሎም በሞተችበት ስፍራ የተቀመጡ አበቦችን የከተማዋ ጠራጊዎች በተከታታይ ቀናት ባሉ ምሽቶችም የከተማዋ ጠራጊዎች አፅድተውት ነበር።
በአሁኑ ሰዓትም አበቦቹን ዝም ብለው እየተዋቸው ሲሆን ለፖሊሶችና ፀጥታ ኃይሎች ቆሞ የነበረው ሃውልቶችም ጥቃትንና ኢ-ፍትሃዊነት የታገለችው ኢርና ማስታወሻ በርካቶች አድርገውታል።
በአካባቢውም ሁለት ፖሊሶችም ሁኔታውን እየተከታተሉ ይገኛሉ።

አንዳንዶች ዜናውን ባይሰሙም የሰሙትን ሁሉ አስደንግጧል፤ አብረክርኳል።
ኢርና ራሷን በዚህ አሰቃቂ መንገድ ያጠፋችው ሰው ከተጫነበትና ከደበተው ዝምታም መንጭቆ ለማውጣትም ነው በማለት አስተያየታቸውን የሰጡም አልታጡም።
የኢርና ባለቤትም ለምን ራሷን በእሳት አቃጥላ አጠፋች ለሚለው ምላሽ የለውም፤ ምላሽም ለመፈለግ እየሞከረ አይደለም።
"እሷን መልሶ አያመጣትም። መቀበል ብቻ ነው። ሆኖም ሞቷ ዝም ብሎ እንዳይሆን እፈልጋለሁ" ብሏል።

የፎቶው ባለመብት, Irina Enikeeva












