ቀጣሪ ድርጅቶች ከእኛ የሚፈልጉት ምንድን ነው?

ሲቪ ለመጻፍ መነሻው ምንድን ነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አዲስ ተመራቂ ናችሁ? ወይስ ሥራ ለመቀየር ማስታወቂያ እየተመለከታችሁ ነው?

የሥራ ቅጥር ማስታወቂያ ከመመልከት ባልተናነሰ የትምህርት ሁኔታ፣ የሥራ ልምድና መሰል ግላዊ መረጃዎችን የሚይዘውን ሲቪያችንን [የሥራ ማመልከቻችንን] በአግባቡ ማደራጀት ወሳኝ ነው።

በርግጥ ሥራ ለማግኘት ሲቪ ብቻውን ወሳኝ አይደለም። ግን ጥሩ ለመወዳደር እና በሚገባ ራስን ለመሸጥ ጥሩ ሲቪ ያስፈልግጋል።

የሚወዳደሩት ከበርካታ አመልካቾች ጋር በመሆኑ፣ እርስዎ የተሻሉ ተወዳዳሪ መሆንዎን ለማሳየት ጥሩ ሲቪ ሊጽፉ ይገባል።

ጥሩ ሲቪ የመጀመርያው መመረጫ ቢሆንም ሥራውን ለማግኘት ግን ማረጋገጫ አይደለም።

ሥራ እፈልጋለሁ ካሉ ጥሩ ሲቪ ማዘጋጀት የግድ ነው። ማን መሆንዎን? ያለዎትን የሥራ እና የትምህርት ዝግጅት የሚያሳዩት በሲቪዎ ነው።

ይሀ አጠር ያለ የሥራ ልምድ መግለጫ የሚፈልጉትን ሥራ ለማግኘት ለቃለ መጠይቅ አልያም ለጽሑፍ ፈተና እንዲቀርቡ በር ከፋች ነው።

ሲቪ የቀጣሪዎን ልብ በር የሚያንኳኩበት፣ ከእርስዎ ቀድሞ ቀጣሪዎ እጅ የሚገባ ማስረጃ ነው።

ስለዚህ ተገቢውን ጥንቃቄ አድርጎ ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ የኢትዮጆብስ ሰርቪስ ማናጀር እና ሥራ ፈላጊዎችን አሰልጣኝ የሆነችው ኮከብ አየለ ታስረዳለች።

ኢትዮጆብስ በኢትዮጵያ የመጀመርያው የሥራና ሠራተኛ አገናኝ ድረገጽ ነው።

ተቀምጣ የምትጽፍ ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቀጣሪዎች ከሲቪያችን ላይ የሚያዩት ምንድን ነው?

ቀጣሪዎች የሥራ ማስታወቂያ ሲያወጡ ክፍት የሆነ ቦታ ኖሯቸው በመሆኑ የሚቀጥሩት ሰውም ይህንን ክፍተት የሚሞላ መሆን ይኖርበታል።

ስለዚህ የአመልካቾችን ሲቪያቸውን በሚዘጋጁበት ወቅት ይህንን ክፍት ቦታ ይሞላዋል? የሚል ጥያቄ በአእምሯቸው ይዘው ነው የሚገመግሙት።

ይህንን ከሚወስኑ ሌሎች ነጥቦች መካከል ደግሞ በቅጥር ማስታወቂያው ላይ የሰፈረው የሥራ ልምድ አንዱ መሆኑን ኮከብ ታነሳለች።

አመልካቾች በተጠየቀው የሥራ ልምድ ልክ ይህንን ክፍት ቦታ ይሞላሉ ወይ? የሚለው ጥያቄ ቀጣሪዎች አአምሮ ውስጥ የሚመላለስ ነጥብ ነው።

የተጠየቀው የሥራ ልምድ ያለው አመልካች ባይገኝስ?

ቀጣሪዎች በቀጥታ ላወጡት ክፍት የሥራ ቦታ የሚፈልጉትን የሥራ ልምድ ያለው ሰው ካላገኙ፣ ተያያዥ የሆኑ የሥራ ልምዶች ሏቸውን አመልካቾች መፈለጋቸው አይቀርም።

አንዳነድ ጊዜ ደግሞ አመልካቾች የሰሩበት ድርጅት በቀጣሪዎች ዘንድ እንደሚታይ ኮከብ ታስረዳለች።

ከአንድ ድርጅት ወደ ሌላ ድርጅት በምንሄድበት ወቅት ከዚህ ቀደም የሰራንበት ተቋም ጠንካራ ልምድ ሰጥቶናል ተብሎ ስለሚታመን የሰራንበት ድርጅት በቀጣሪዎች ዘንድ ከሚታዩ መስፈርቶች መካከል አንዱ ነው።

ይህም ከአንድ ድርጅት ወደ ሌላ ድርጅት ሥራውን ለማከናወን የምንሄድበትን ሂደት ፈጣን ያደርገዋል።

ከዚያ ውጪ ግን አመልካቾች በሲቪያቸው ላይ የነበራቸውን የሥራ ድርሻ ብቻ ከመግለጽ ይልቅ፣ በዚያ የሥራ ድርሻ ምን ሰርተውበታል የሚለውን ቢጽፉ ቀጣሪዎች የሠራተኛ ምልመላ የሚያደርጉበት ወቅት ትኩረታቸውን ለመሳብ እና ሥራውን ለማግኘት ዕድል ይፈጥራል።

ይህንንም ኮከብ በምሳሌ ስታስረዳ፣ አንድ የሽያጭ ሠራተኛ በሲቪው ላይ በሽያጭ ሠራተኛነት የዚህን ያህል ዓመት የሥራ ልምድ አለኝ ብቻ ሳይሆን፣ ድርጅቱን በዚህን ያህል ትርፋማ አድርጌዋለሁ የሚል ተጨባጭ የሆነ መግለጫ ማካተት ጠቃሚ መሆኑን ትመክራለች።

ቀጣሪዎች የትምህርት ደረጃንም የሚመለከቱ መሆኑን ኮከብ አየለ ትጠቅሳለች።

ከአንድ ሥራ ወደ ሌላ ሥራ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚዘሉ ሥራ ፈላጊዎች ግን የቀጣሪዎችን ትኩረት ለመሳብ ይቸገራሉ።

ሲቪ ላይ ያልሆኑትን ሆኖ መጻፍ ቀጣሪዎች ከፍ አድርገው እንዲጠብቁን ያደርጋል። ይህ ደግሞ ዕድልም ጦስም ይዟል።

ዕድሉ ለፈተና እንዲቀርቡ ማድረጉ ሲሆን አሉታዊ ጎኑ ደግሞ ከሌሎች ተወዳዳሪዎች በተለየ እኛ ላይ ትኩረት ያደረጉ ጥያቄዎች መነሳታቸው ነው።

ስለዚህ ያልሆነውን ነን ብሎ መጻፍ በኋላ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ኮከብ ታስረዳለች።

ሲቪ ለመጻፍ መነሻው ምንድን ነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሲቪ ለመጻፍ መነሻው ምንድን ነው?

አንድ ሰው ምንም ዓይነት ክፍት የሥራ ማስታወቂያ ሳያይ ከራሱ አአምሮ ጨምቆ ለሰለጠነበት የሥራ ዘርፍ ዝግጁ ነኝ ብሎ ሲያስብ ሲቪውን ሊያዘጋጅ ይችላል።

እንዲህ አይነት ሲቪ ለየትኛውም ቀጣሪ እንዲያገለግል ሆኖ የተሰናዳ ነው።

ሁለተኛው ግን የሥራ ማስታወቂያ ታይቶ ያንን መነሻ በማድረግ፣ ቀጣሪው ምን ይፈልጋል? ተብሎ የሚዘጋጅ መሆኑን ኮከብ አየለ ታስረዳለች።

እነዚህ ሰዎች ሲቪውን ሲያደራጁ ማስታወቂያን አንብበው፣ በሚገባ ተረድተው ለማስታወቂያው ምላሽ የመስጠት ያህል በመጠንቀቅ የሚያዘጋጁ ናቸው።

ቀጣሪዎችን አስበው ሲቪያቸውን የሚያደራጁ ሰዎች፣ ልክ ለቀጣሪዎቻቸው ምላሽ እንደሚሰጡ ሊሰማቸው እንደሚገባ ትመክራለች።

በዚህ ወቅት "ከሌላው ተወዳዳሪ ጎልቼ እንድታይ" በሚል አስተሳሰብ እና ምን ያህል የቅጥሩን መስፈርት አሟላለሁ በሚል ግንዛቤ መደራጀት ይኖርበታል።

እንዲህ ዓይነት ሲቪ ከሥራ ልምድ እና ከሥራ ፍላጎታችን በተጨማሪ ሥራውን ያወጣው ድርጅትን መሰረት ባደረገ መልኩ ካልተዘጋጀ የምንፈልገውን ውጤት ላያስገኝ ይችላል።

በየትኛውም ሁኔታ ረዥም ሲቪ አይመከርም። ሲቪ ከመዘጋጀቱም በፊት የሥራ ማስታወቂያውን ማየት መልካም ነው።

ሰዎች ሲቪያቸውን እንዴት አድርገው ያዘጋጁ?

አንድ ሲቪ ውስጥ የማይቀሩ ቋሚ መረጃዎች አሉ ትለላች የኢትዮጆብሷ ኮከብ።

የመጀመሪያው ስለ ግለሰቡ መሠረታዊ መረጃዎችን የሚይዘው ክፍል ነው።

ይህ ከግለሰቡ ስም፣ የስልክ ቁጥር፣ ኢሜል እንዲሁም ከማኅበራዊ ሚዲያ ጋር እንዳላቸው አጠቀቃቀም የሊንክዲን አድራሻቸውን ሊያካትቱ እንደሚችሉ ኮከብ ትመክራለች።

ምንም የሥራ ልምድ የሌላቸው አዲስ ተመራቂዎች ሲቪያቸውን ሲጽፉ ደግሞ፣ ቀድመው ሊያሳዩት የሚፈልጉትን መረጃ ማሰብ ይጠበቅባቸዋል።

አንድ ሲቪ ከተጻፈበት መረጃ ይዘት ይልቅ ዕይታው ተጽዕኖ አለው የምትለው ኮከብ፣ በርካታ አመልካች ስላለ ከእነርሱ ሁሉ ልቆ ዓይን ለመያዝ የሚያስችልን ነገር ማሰብ ያስፈልጋል።

አዲስ ተመራቂዎች የሥራ ልምድ ስለሌላቸው እዚህ ሥራ በመቀጠራቸው የት መድረስ ፍላጎት አላቸው የሚለውን የሚያሳይ አጭር መግለጫ ቢያስቀምጡ ለቀጣሪዎቻቸው ጉጉታቸውን እና አቅጣጫቸውን ያሳይላቸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የሥራ ልምድ ስለሌላቸው በበጎ ፈቃደኝነት ለማኅበረሰብ በነጻ የሚሰጡ አገልግሎቶች ላይ የተሳተፉበትን ማስፈር ሲቪያቸው ትኩረት እንዲያገኝ ያደርጋል።

በእነዚህ በተጓዳኝ በሚሰሩ ተግባራት ላይ በምን አቅም እንደተሳተፉ (አባል በመሆን ወይም በአመራር ደረጃ ) የሚለውን ማስቀመጥ ጠቃሚ መሆኑን ኮከብ ትገልጻለች።

የሥራ ልምድ ያላቸው ሰዎች ከግል መረጃ በመቀጠል ያላቸውን የሥራ ልምድ ጠቅለል አድርገው የሚያሳዩበት ክፍል ቢመጣ መልካም ይሆናል።

"እጥር ምጥን ብሎ፣ እኔን ባህሪዬን፣ አቅሜን እና በሙያው ያለኝን ልምድ ሊያሳዩ የሚችሉ ከሦስት እስከ አምስት መስመር የሆነ መግቢያ ማስቀመጥ ይመከራል" ትላለች ኮከብ።

በተለይ የሥራ ልምድ ያላቸው ሰዎች ከሥራ ልምዳቸው በመቀጠል ወደ ትምህርት ዝግጅታቸው በማምራት ሲቪያቸውን ቢያዘጋጁ ይመከራል።

ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ አንዳንድ ቀጣሪዎች ልምድን ካዩ በኋላ ወደ ትምህርት ዝግጅት ስለሚያመሩ መሆኑን ትገልጻለች።

ይህ የሥራ ልምድ እና በሥራቸው ላይ ያሳኳቸውን ነገሮች የሚዘረዝሩበት ክፍል አጠር ብሎ ሲቀመት ከዕይታ ባሻገር ለቀጣሪዎች መረጃን በአጭር እና በግልጽ ቋንቋ በማድረስ ተፈላጊውን ግብ መምታት ይቻላል።

የሥራ ልምድ ሲዘረዘር መሆን ያለበት ከቅርቡ ወደ ኋላ መሆን እንዳለበትም ኮከብ ትመክራለች።

"መጀመሪያ አሁን ያሉበት ድርጅት፣ የሥራ ድርሻ፣ ከመቼ ጀምሮ ይህንን ሥራ መስራት እንደጀመሩ እና በቦታው ላይ እንደቆዩ፣ በመጥቀስ ወደ ቀደመው ሥራ ማለፍ ይቻላል።"

የትምህርት ዝግጅትም ቢሆን በተመሳሳይ መልኩ መቀመጥ እንዳለበት ኮከብ ታስረዳለች።

የትምህርት ዝግጅቱ በቅደም ተከተል ከተደራጀ በኋላ በመቀጠል የሚመጣው የተወሰዱ ሥልጠናዎች የሚለው ክፍል ነው።

ሥልጠናዎቹ በራስ ተነሳሽነትም ሆነ ሥራው በፈቀደ መጠን የተወሰዱ ሊሆኑ አንደሚችሉ ኮከብ አክላ ትናገራለች።

ሥልጠናዎቹ የት እና መቼ እንደተወሰዱ እንዲሁም ስሙን በሚገባ ማስቀመጥ ያስፈልጋል።

እነዚህ የሥልጠና መዘርዝሮች የበለጠ ከሥራው ጋር የሚገናኙ ቢሆኑ እንደሚጠቅም የምትናገራው ኮከብ፣ ይህም ሙያውን አጥርቶ መምራት እና ያለ የዝግጅት እና ብቃትን እንደሚያሳይ ታስረዳለች።

ከዚህ በታች የሚመጣው እና የሲቪያችን ቁልፍ አካል የሆነው ስለእና ምስክርነት ሊሰጡ የሚችሉ ሰዎች ወይም ሪፈረንስ ነው።

ይህ ክፍል ግዴታ አይደለም የምትለው ኮከብ፣ የምናስቀምጥ ከሆነም ስለ እኛ የሚናገሩልን ሦስት ሰዎችን ከነ ሙሉ አድራሻቸው መዘርዘር ይገባል።

እነዚህ ሰዎች ስለ እኛ የሙያ ብቃት እንዲሁም ባሕሪ ጨምረው እንዲያስረዱልን ይጠበቃል።

ይህንን ክፍል ስጠየቅ አቀርባለሁ በሚል መዝለል እንደሚቻልም ጨምራ ታስረዳለች።

Short presentational grey line

ሲቪ ለማዘጋጀት ጠቃሚ ነጥቦች

  • አጭርና ግልጽ የሆነ ቋንቋ ይጠቀሙ
  • ሲቪዎ ከሁለት እና ከሦስት ገጽ አይብለጥ
  • ጠቃሚ የሆኑትን መረጃዎችን ቀድመው ያስፍሩ
  • ሲቪዎትን ለሚያመለክቱት የሥራ ዓይነት እንዲስማማ አድርገው ያደራጁ
  • ያለዎትን ልምድ እና ያሳኳቸውን ተግባራት በሚገባ ይግለጹ
  • የቃላት እና የሰዋሰው ግድፈትን ያርሙ
Short presentational grey line

በሲቪ ላይ የሚታዩ ተደጋጋሚ ስህተቶች

የሥራ ቅጥር ማስታወቂያን ወዳጅ እና ጓደኛ አይቶት ስለነገረን ብቻ ከምናመለክት ራሳችን አንብበን ምን ይፈልጋሉ የሚለውን በሚገባ በመለየት ሲቪን ማዘጋጀት ከስህተት ያድናል።

የሥራ ቅጥር ማስታወቂያው ላይ የተቀመጠውን መመርያ በሚገባ አንብቦ አለመተግበር ቀጣሪዎች የአመልካቾችን ወደ ጎን እንዲገፉ ምክንያት ከሚሆኑ ነገሮች መካከል አንዱ ነው።

ሌላው ሲቪ ላይ በተደጋጋሚ የሚታየው ስህተት የመረጃ ክፍተት መሆኑን ኮከብ ትናገራለች።

ከአንድ ተቋም ወደ ሌላው የሄድንባቸው ዓመታት መካከል ያለ ክፍተት፣ ከአንድ ኃላፊነት ወደ ሌላው ያደረግነው ሽግግር በሚገባ መቀመጥ ይኖርበታል።

በአንድ ጊዜ የተለያዩ ቦታ የሚያመለክቱ ግለሰቦች ደግሞ ማመልከቻቸውንም ሆነ ሲቪያቸውን ለአንድ ድርጅት የጻፉትን የሌላኛውን ቀጣሪ ፍላጎት በማያሳይ መልኩ ያስገባሉ።

ከእዚህ ሁሉ በተጨማሪ ከሌላ ቦታ ላይ ተቆርጠው የመጡ እና የተለጠፉ መረጃዎች ሲቪ ላይ ስለሚያስታውቁ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።

ሲቪ ለንባብ የሚጋብዝ፣ የፊደል ቅርጽ እና መጠኑ በአግባቡ የተመጠነ፣ ከሰዋሰው ስህተት የፀዳ፣ ስልክ ቁጥርና የኢሜይል አድራሻን በትክክል የያዘ መሆን አለበት።

በተጨማሪም አላስፈላጊ የመረጃ ድግግሞሽን ማስወገደፍ ያስፈልጋል።

የአንድ ሰው ሲቪ በጣም ረዥም ከተባለ ሦስት ገጽ ብቻ መሆን እንዳለበት ኮከብ ትመክራለች።

ሲቪያችንን ከጻፍን በኋላ ሌላ ሰው እንዲያው ማድረግ በቀላሉ ሊስተካከሉ የሚችሉ ስህተቶችን ለማረም ዕድል ይሰጣል።