የምንፈልገውን ሥራ እና እድገት ለማግኘት ራሳችንን እንዴት እንግለጽ?

ሰላምታ የሚለዋወጡ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ስለራስ መናገር ምቾት አይሰጥም፤ አይደለም ለአለቃ ለወዳጅ እንኳ ቢሆን 'ምን ጉራህን ትቸረችራለህ' ሊያስብል ያስችላል።

የሰው ጀማ ተሰብስቦ ስለራስ 'ጥሩንባ መንፋት' የተለመደ አይደለም፤ ይህ ግን የኢትዮጵያውያን ችግር ብቻ ሳይሆን ፈረንጆቹም እዚህ ላይ ትንሽ ቆንጠጥ ያደርጋቸዋል።

ስለራሳቸው ለመናገር ጀምረው ድምጻቸው የሰለለባቸው፣ እጃቸውን ያላባቸው፣ አፋቸውን የፈቱበት ቋንቋ የጠፋቸውን የየመሥሪያ ቤቱ ደጃፍ ይቁጠራቸው።

ለስቴፋኒ ስዎርድ ዊሊያምስ ግን "ይህ ክህሎት ሁለቴ ማሰብ የማያስፈልገው ሁሉም ሊኖረን የሚገባ ነው" ትላለች።

ስቴፋኒ ራስን በብቃት መግለጽ መቻል ላይ በበርካቶች የተነበበ መጽሐፍ አዘጋጅታለች።

በሠሯቸው ሥራዎች፣ ባገኟቸው ውጤቶች መኩራራት፣ ደረትን መንፋት ልክ እንደ በጎ ምግባር ሊቆጠር ይገባል ስትል ታስረዳለች።

ነውር አለመሆኑንም አጽንኦት ሰጥታ ነው የምትናገረው።

በዚህ ፉክክር በበዛበት ዓለም ያለዎትን ክህሎት ማጉላት በሥራ ቦታ ለውጤትዎ ላቅ ያለ ድርሻ ይኖረዋል።

በሥራዎ እድገት ለማግኘት፣ አዲስ ሥራ ለመቀየር፣ በአለቃዎ ዕይታ ውስጥ ለመግባት እና የድርጅትዎን የእድገት መሰላል በቀላሉ ለመውጣት ስለራስዎ ያለመሸማቀቅ መናገር ያስፈልግዎታል፤ ይጠበቅብዎታልም።

ለአንድ ሥራ በርካቶች የማመልከቻ ዶሴ ተሸክመው በየቀጣሪዎች ደጅ በሚንከራተቱበት በዚህ ወቅት፣ ሁሉም ዲግሪ እና ማስተርስ ኖሮት ያለችው ጥቂት እድገት ላይ ዓይኑን ጥሎ በሚጠብቅበት የሥራ ቦታ "ራስን መሸጥ" ተገቢ ክህሎት ሆኖ ይገኛል።

ይህ ደግሞ ዓይን አፋር ለሆኑ እና ራሳቸውን መግለጽ ለሚቸገሩ ሴቶች አስፈላጊ ክህሎት ነው።

የራሳቸውን ሥራ ከቤታቸው ሆነው ለሚሰሩ፣ በኮቪድ ወረርሽኝ የተነሳ የገበያ ዕድሎችን ሳስተው፣ ከብዙኃኑ ጋር ተቀላቅሎ ለመወዳደር ፈተና በሆነበት በዚህ ወቅት ያለው አማራጭ ስለራስ ስኬት፣ ስለ አገልግሎትዎ እና ስለ ክህሎትዎ ደረትን ነፍቶ ማስረዳት መቻል ነው።

"የራሳችንን እሴቶች ለማሳየት ጊዜ የማንወስድ ከሆነ፤ እንደ ተፈላጊ የመቆጠር ዕድላችን ላይ በር እንዘጋለን" ስትል ስዎርድ ዊሊያምስ ታስረዳለች።

"ስለ ራሳችን የምንታወቅበትን ነጥቦች ይፋ በማድረግ፣ ማንንነታችንን በማሳየት ታሪካችንን ራሳችን መንገር ያስፈልገናል" ባይ ናት። ስለ እኛ ሌሎች እንዲመሰክሩልን መጠበቅ የዋህነት ነው ስትልም ታክላለች።

ራስን ማስተዋወቅ በቀላል ብያኔ ሥራዎና ስኬትዎ ተገቢውን ትኩረት እንዲያገኝ ማድረግ ማለት ነው።

ስለዚህ ስለራስዎ በማኅበራዊ ድረ ገጽ ላይ የሚያስቀምጡት መግለጫ፣ ወይንም በኢሜል መልዕክት ላይ የሚያስገቡት ማብራሪያ ካልሆነ ደግሞ ከአለቃዎ ወይንም ከቁልፍ ሰዎች ጋር በሚኖርዎት ውይይት ወቅት የሚያነሷቸው ነጥቦች ራስዎን በሰዎች ፊት ሞገስ በማሰጠት ረገድ ትልቅ ሚና አላቸው።

በተሰማሩበት መስክ ለማደግ እንዲሁም ማንነትዎን እና ብቃትዎን [ብራንድ] በሚገባ ለማስተዋወቅ ጠቃሚ ነው።

በተሰማራበት መስክ እስከ መሰላሉ የላይኛው ጫፍ ለመውጣት የሚፈልግ ሰው ደግሞ ይህንን ቢያደርግ መንገዱን የውሃ ያደርገዋል።

ለአለቃዋ ገለጻ የምትሰጥ ሴት

የፎቶው ባለመብት, Alamy

ይህ ዓለም የወንዶች ነው

በሥራው ዓለም የተደረጉ ጥናቶች እንደሚመሰክሩት ከሆነ ስለራስ በመናገር ከሴቶች ይልቅ ወንዶች ይደፍራሉ።

እኤአ በ2019 መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገ አንድ አካዳሚ፣ ይፋ ባደረገው ጥናት ራስን በመግለጽ ረገድ "ትልቅ የሥርዓተ ጾታ ክፍተት ይታያል።"

ተመራማሪዎቹ ለጥናቱ ተሳታፊዎች የሒሳብ እና የሳይንስ ፈተና እንዲወስዱ፣ ከዚያም ብቃታቸውን ራሳቸው እንዲመዝኑ አድርገዋል።

የጥናቱ ተሳታፊዎች ለራሳቸው የሰጡት ውጤት ለአለቆቻቸው ማንን ለመቅጠር እና ምን ያህል መክፈል እንደሚገባቸው መወሰን እንዲችሉ እንዲያውቁት እንደሚደረግ ተነግሯቸዋል።

ምንም እንኳ በጥናቱ ወንዶቹም ሴቶቹም እኩል ውጤት ያመጡ ቢሆንም፣ ወንዶች ግን ለራሳቸው በአማካኝ 61 ከመቶ ሲሰጡ ሴቶች ግን 46 ከመቶ ሰጥተዋል።

ሴቶች ስለምን ከወንዶች የበለጠ ድሃ ሆኑ (Why Women Are Poorer Than Men) የሚል መጽሐፍ ደራሲዋ አናቤላ ዊሊያምስ "ሌሎች በርካታ ጥናቶች እንዳሳዩት ከሆነ ወንዶች ስለስኬታቸው ሲጠየቁ 'እራሳቸውን በመሸጥ' ላይ የተዋጣላቸው ናቸው። በተቃራኒው ሴቶች ደግሞ ችሎታቸውን እና ውጤታቸውን ዝቅ አድርገው ሲያቀርቡ ተስተውሏል" ትላለች።

ሴቶች ከልጅነታቸው ጀምሮ ራሳቸውን ከፍ ከፍ ሲያደርጉ እየተገሰፁ ነው የሚያድጉት። ራሷን ከፍ ከፍ ለምታደርግ ሴትም የሚሰጡ የተለያዩ ቅጽል ስሞች መኖራቸውን ትገልጻለች።

"ነገር ግን ተመሳሳይ ባህሪ የሚያሳይ ወንድ በራስ የመተማመን ብቃት እና የአመራር ችሎታ እንዳለው ይቆጠርለታል" ስትል ታብራራለች።

ስዎርድ ዊሊያምስ በበኩሏ በከፍተኛ የሥራ ኃላፊነቶች ላይ የሚገኙ እና አርዓያ የሚሆኑ ሴቶች ስለራሳቸው መናገር እና ስኬታቸውን ማንቆለጳጰስ ተገቢ መሆኑን ሲናገሩ አይደመጡም ትላለች።

በውጤቱም ሴቶች ለአንድ የሥራ እድል ከወንዱ የበለጠ እንዲታገሉ ያደርጋቸዋል።

በእርግጥ አንዳንድ ወንዶች አይናፋር፣ ሴቶች ደግሞ በተፈጥሯቸው ራሳቸውን መግለጽ እና ሰለ ሥራቸው በድፍረት ለመናገር ችግር ላይኖርባቸው ይችላል።

በቅርቡ በተደረገ ጥናትም ወጣት ሴቶች በእድሜ ከገፉ ሴቶች ይልቅ ስለራሳቸው ደፈር ብለው መናገር እንደሚችሉ ይፋ አድርጓል።

ስለራስ በድፍረት እና በልበ ሙሉነት መናገር ቦታ ካልተመረጠለት ባዶ ጩኸት እና ቀረርቶ ሊሆን እንደሚችል ባለሙያዎቹ ያስረዳሉ።

ቀጣሪን እና አለቃን ከመማረክ ይልቅ ሊያበሳጭ የሚችልባቸውም ዕድሎች አሉ።

በዚህ ወቅትም ስለራስ በልበ ሙሉነት ለመናገር ግቡን መምታት አቅቶት ሲከሽፍ ይስተዋላል።

ስለራስዎ በልበ ሙሉነት ለመናገር ምን ያድርጉ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ስለራስዎ በልበ ሙሉነት ለመናገር ምን ያድርጉ?

ስለራስ በልበ ሙሉነት መናገር ግን እንዲሁ የሚገኝ ስጦታ አይደለም፤ ልምምድ ይጠይቃል።

በተለይ በቢሮዎ ውስጥ፣ በወንበርዎ ላይ በወረቀት ክምር መካከል አልያም ከኮምፒውተር ጀርባ ተቀምጠው የዕለት ሥራዎትን ብቻ የሚከውኑ ከሆነ ከዕይታም ከአእምሮም ውጪ የመሆን ዕድልዎ የሰፋ ነው።

እርስዎ ልምዱና ችሎታው እያለዎት ሌሎች አልፈዎት ይሾማሉ፤ ይሸለማሉ።

እርስዎ በነበሩበት የደሞዝ እርከን ላይ ተቀምጠው ሲያለቃቅሱ ሌሎች የጥቅማ ጥቅም እና ደረጃ እድገት በረከት ተቋዳሽ ይሆናሉ።

ስለዚህ ስለራስዎ በሚገባ መግለጽ፣ ስኬቶችዎን በደማቅ ቀለም በአለቃ አእምሮ ውስጥ ለመጻፍ እንዲችሉ ያለማመንታት ልምምድ ያድርጉ።

አለቆች የሰሯቸውን ሥራዎች የሚያስታውሳቸው፣ ስኬቶችዎን እና አስተዋጽኦዎን የሚነግራቸው ይፈልጋሉ።

በተቋሙ ውስጥ ለረዥም ጊዜ ተቀጥረው ቢሰሩ እንኳ ስለራስዎ እስካልተናገሩ ድረስ የመረሳት ዕድልዎ ሰፊ ነው።

ስለዚህ ልክ እንደ አዲስ ክህሎት ራስን በልበ ሙሉነት መግለጽንም ሊማሩት እና ሊለማመዱት የሚገባ ክህሎት ነው።

"የረዥም ጊዜ የሥራ ላይ ህልምዎን እና ፍላጎትዎን ለአለቃዎ ይንገሩ" የምትለው ሃሪት ሚንተር ነች።

ሃሪት ሚንተር በዚህ ዘርፍ ጥሩ የተነበበ መጽሐፍ ደራሲ ስትሆን "አሁን ጊዜው አይደልም አትበሉ። ከዚያ ይልቅ ለኩባንያው ያመጧቸውን ዕሴቶች በመመልከት በዚያ መሰረት ጥያቄያችሁን ሰንዝሩ" ስትል ትመክራለች።

ወረቀት የሚቀባበሉ እጆች

የፎቶው ባለመብት, iStock

ሚለር ስለስኬትዎ ለሥራ አጋርዎ እና አለቃዎ ለማሳወቅ ኢሜል አንዱ መንገድ ነው ትላለች።

በዚህ ኢሜል ውስጥ ማካተት የሚፈልጓቸውን መረጃዎች ማካተትዎን፣ በሚገባ መግለጽዎን እና ቢያንስ በሳምንት አንድ ጊዜ የመላክ ልምድዎን ያዳብሩ፤ አንዴ መላክ ከጀመሩ በቀጣዮቹ ሳምንታት እየቀለለዎ ይመጣል ስትል ሚለር ትመክራለች።

ከዚህ ደግሞ ባለፈ ልምድዎን እና ችሎታዎን ለማሳየት አዲስ ተቀጣሪዎች ሲመጡ ለማማከር፣ ለማለማመድ እና ልምድን ለማጋራት ከፊት ይሁኑ።

ለጀማሪዎች ልምድን በድፍረት ማካፈል ያለዎትን ልምድ እና ክህሎት ለሌሎች ለማሳየት ጥሩ ዕድል ነው።

በዚህ የዲጂታል ዘመን በፌስቡክ፣ በትዊተር እንዲሁም በሊንክዲን ላይ ስለራስዎ የሚያሰፍሯቸውን መረጃዎችም መጠንቀቅ ያስፈልጋል።

በየጊዜው የሚስተለካከሉ እና ያለዎትን ልምድ እና ክህሎት በሚገባ የሚገልጹ መሆናቸውን ያስተውሉ።

ከዚህ በኋላ ስራስዎ መናገር ልክ ታሪክ የመንገር ያህል ቀላል ይሆናል።

እንዴት አድርጌ ብነግረው የበለጠ ይስብልኛል ቀልብም ልብም ይስብልኛል የሚለው ያስጨንቅዎት ይሆናል እንጂ፤ አፍዎ አይተሳሰርም፣ እጅዎን አያልብዎትም፣ ድምጽዎም አይሰልም።