በማደጎ የወሰደችውን ህፃን የገደለችው እንግሊዛዊት የ18 አመት እስር ተፈረደባት

የፎቶው ባለመብት, Cumbria Police
በእንግሊዝ በማደጎ የወሰደችውን ህፃን የገደለችው ግለሰብ የ18 አመት እስር ተፈርዶባታል ።
ላውራ ካስትል የተባለችው ግለሰብ የ13 ወራት ዕድሜ የነበረውን ሊላንድ ጄምስ ኮርኪል የተሰኘ ህፃን ባለፈው አመት በጭካኔ መግደሏን ፍርድ ቤቱ አምኗል።
የ38 አመቷ ግለሰብ በነፍስ ግድያና በልጆች ጭካኔ ወንጀል ጥፋተኛ ሆና እንዳገኛትም ገልጾ የ18 አመት እስር ፈርዶባታል።
ግለሰቧ ፍርድ ቤት በቀረበችበት ወቅት ህጻኑን መግደሏን ብታምንም ሆን ብላ እንዳልገደለችው ለችሎቱ አስረድታለች።
ልጁ አምርሮ በሚያለቅስበት ወቅት ሃሳቧ እንደጠፋባት እና ዝም ለማሰኘትም በምትነቀንቀው ወቅት በድንገት ጭንቅላቱን ከሶፋው መደገፊያ ጋር ተጋጭቷል ብላለች።
ጎረቤቶቿ በበኩላቸው በሰጡት ምስክርነት የልጁን ለቅሶ ምንም እንዳልሰሙና የሷን ግን በከፍተኛ ንዴት የተሞላበት ጩኸት ይሰማ ነበር ብለዋል።
የጨቅላውን አስከሬን የመረመሩ የጤና ባለሙያዎች በበኩላቸው ህፃኑ ጭንቅላት ላይ የደረሰው ጉዳት በከባድ ምት የተከሰተ እንደሆነና ጭንቅላቱም ከግድግዳ ጋር ወይም ከወለል ጋር ተጋጭቷል ብለው እንደሚያምኑም አስረድተዋል።
ከሶፋው ጋር መጋጨት ህፃኑ ለታየበት ከፍተኛ የውስጥ ደም መፍሰስ ምክንያት እንደማይሆንና የደረሰበትንም ጉዳት በከፍተኛ ፍጥነት ከሚደርስ የመኪና አደጋ ጋር አመሳስለውታል።

ግለሰቧ በችሎቱ መክፈቻ ላይ ሙሉ ጥቁር ለብሳ ጮክ ብላ ስታለቅስ የታየች ሲሆን የጨቅላው ወላጅ እናት የልጇን ገዳይ "ጭራቅ" ስትልም ጠርታታለች።
ዳኛው ጄረሚ ቤከር ጨቅላው የማደጎ እናቱን በፍጹም ሊለምድ እንዳልቻለ ተናግረው ይህ ሲከሰት ልጁን ከመመለስ ይልቅ "ራስ ወዳድ በመሆኗ ይህ አሳዛኝ ክስተት መፈጠሩንም" ጠቁመዋል።
ፍርድ ቤቱ ባለቤቷን ከጨቅላው ግድያ ጋር በተያያዘ ነጻ አውጥቶታል።
ጨቅላው የስምንት ወር ህፃን እያለ ሲሆን ለማደጎ ወላጆቹ የተሰጠ ሲሆን ግለሰቧ ባሏ ስራ በሄደበት ወቅት ህጻኑን በአጸያፊ ስድብ ከመጥራት ጀምሮ ምን ያህል ትጠላው እንደነበር መልዕክት ልካለታለች ተብሏል።
ታህሳስ ወር መጨረሻም ላይ ግለሰቧ ህፃኑ ከሶፋ ከወደቀ በኋላ ራሱን መሳቱንና በአስቸጋሪ ሁኔታ እየተነፈሰ መሆኑን ለፖሊስ ደውላ ተናገረች።
በማግስቱም በሊቨርፑል ውስጥ በሚገኘው የአልደር ሄይ የህጻናት ሆስፒታል መሞቱም ተነግሯል።












