ሴኔጋላዊው የፒኤስጂ ተጫዋች ለተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን ድጋፍ አልሰጠም መባሉ አነጋጋሪ ሆነ

ሴኔጋላዊው የፓሪስ ሴንት ዠርሜይን አማካይ ኢድሪሳ ጌዬ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የፒኤስጂው ኢድሪሳ ጋና ጌዬ ለተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪን ድጋፍ ለመግለጽ የቀረበውን መለያ ለመልበስ ፍቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል መባሉ አነጋጋሪ ሆነ።

ሴኔጋላዊው የፓሪስ ሴንት ዠርሜይን አማካይ ኢድሪሳ ጌዬ ለተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪን ድጋፍ ለመግለጽ የቀረበውን መለያ አለብስም ብሏል ሲል አንድ ጋዜጣ ዘግቧል።

የፈረንሳይ ሊግ፤ የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪያን ለሚያደርጉት እንቅስቃሴን ድጋፉን ለመግለጽ ተጫዋቾች መለያቸው ላይ የሚሰፍረውን ቁጥር በቀስተ ደመና ቀለም እንዲሆን አድርጓል።

ባሳለፍነው ሳምንት በነበሩት የሊግ ፍልሚያዎች ተጫዋቾች ይህን መለያ ለብሰው ሜዳ ገብተዋል።

አማካዩ ኢድሪሰ ጌዬ ግን ይህን መለያ ለብሶ ወደ ሜዳ ለመግባት ፍቃደኛ ሳይሆን መቅረቱ በስፋት ተዘግቧል።

የፒኤስጂው አሰልጣኝ ሞሪሲዮ ፖቸቲኖ አማካዩ ሳይሰለፍ የቀረው “በግላዊ ምክንያቶች” ነው ከማለት ውጪ ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።

አጥባቂ የእልምና እምነት ተከታይ የሆነው ኢድሪሳ ይህን መለያ ለብሼ ወደ ሜዳ አልገባም ብሏል የሚሉ ሪፖርቶች መውጣታቸውን ተከትሎ ድጋፍ እና ነቀፌታ እያስተናገደ ይገኛል።

ለኢድሪሳ ድጋፋቸውን ከሰጡት መካከል የሴኔጋሉ ፕሬዝደንት ማኪ ሳል ይገኙበታል።

ፕሬዝደንቱ የኢድሪሳ “ኃይማኖታዊ መርሆች መከበር አለባቸው” ብለዋል።

በተቃራኒው በቅርቡ በተካሄደው የፈረንሳይ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ እጩ የነበሩት ቫለሪ ፔክሬስ ተጫዋቹ ላይ እገዳ መጣል አለበት ብለዋል።

ፕሬዝደንታዊ እጩዋ “የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪን ጥላቻ ለመግታት ለሚደረገው ጥረት ኢድሪሳ ጋና ፍቃደኛ አለመሆን ያለ ቅጣት መታለፍ የለበትም” ሲሉ ጠንከር ያለ አስተያየት ሰጥተዋል።

ሃይማኖተኛ ሕዝብ ባላት ሴኔጋል የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት በብዙዎች ዘንድ ጸያፍ ድርጊት ተደርጎ ይቆጠራል።

በምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት በአምስት ዓመት እስር እና በ2500 ዶላር ያስቀጣል።

በዚህ ምክንያት በአገሪቱ የሚገኙ የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪያን ማንነታቸውን በመደበቅ ለመኖር ይገደዳሉ።