የጋዛ አርሶ አደር ከ4ሺህ አመት በላይ ያስቆጠረችውን የከነዓናውያን አምላክ ሃውልት አገኘ

አናት የተባለችው ሃውልት

የፎቶው ባለመብት, BBC/Rushdi Abualouf

በጋዛ ሰርጥ ጥንታዊ የውበት፣ የፍቅር እና የጦርነት አምላክ የድንጋይ ሃውልት ተገኝቷል።

የፍልስጥኤም አርኪኦሎጂስቶች ይህች ሃውልት የከነዓናውያን አምላክ አናት ስትሆን 4 ሺህ 500 ዓመታትን እንዳስቆጠረችና የነሐስ ዘመን ተብሎ በሚጠራው መገባደጃ ወቅትም ላይ እንደነበር ታሪክን በማጣቀስ ይናገራሉ።

ሃውልተወ የተገኘችው በጋዛ ስርጥ ደቡባዊ ክፍል በምትገኘው ክሃን ዩኒስ በሚገኝ እርሻ ቦታ ላይ መሬቱን እየቆፈረ በነበረ አርሶ አደር ነው።

የቅርሷ ግኝትንም ከትሎ አንዳንድ የጋዛ ነዋሪዎች የአማልከቷ መገኘት አሁን ያለው ግጭት መከሰቱን አይቀሬ መሆኑ ማሳያና ምልክት ናት የሚሉ አስተያየቶችን እየሰጡ ነው።

ከቅርብ አመታት ወዲህ በሃማስ ስር ባሉ የጋዛ ታጣቂ ቡድኖችና በእስራኤል መንግሥት መካከል ተከታታይ ግጭቶች እየተከሰተ ይገኛል።

በተከታታይ በነበሩ ስልጣኔዎች ዋነኛ የንግድ መስመር በነበረው የጋዛ ሰርጥ ይህች በኖራ ድንጋይ የተሰራች ሃውልት መገኘቷ ይህ ስፍራ በቀደምትነት የከነዓናውያን መኖሪያ እንደነበረ ያሳያል ተብሏል።

ይህች 22 ሴ.ሜ ቁመት ያላት ሃውልት የእባብ አክሊል ያጠለቀች አምላክን ፊት ያሳያል።

"በአጋጣሚ ነው ያገኘናት። በጭቃ ተለውሳ ነበር እናም በውሃ አጠብናት" በማለት አርሶ አደር ኒዳል አቡ ኢድ ቅርሷን በእርሻ ወቅት እንዴት እንዳገኟት ያስረዳሉ።

"በጣም ውድ የሆነ ነገር እንደሆነ ብንገነዘብም ነገር ግን ይህን ያህል ትልቅ አርኪኦሎጂያዊ ጠቀሜታ እንዳለው አላወቅንም ነበር" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"አምላክን እናመሰግነዋለን። ከከነዓናውያን ዘመን ጀምሮ በምድራችን በፍልስጥኤም በመቆየቷ እንኮራለን።" ብለዋል

ከታወቁት የከነዓናውያን አማልክት አንዷ የሆነችው የአናት ሃውልት ከጋዛ ጥቂት ሙዚየሞች አንዱ በሆነው ታሪካዊ ሕንፃ በቀስር አል ባሻ ለእይታ ቀርባለች።