በኬንያ የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዋ መገደል ቁጣ አስነሳ

የፎቶው ባለመብት, SHEILA LUMUMBA/FACEBOOK
በኬንያ የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪ የሆነችው ሺላ ሉሙምባ ግድያን ተከትሎ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ቡድኖች መንግሥት ጉዳዩን መመርመር እንዲጀምር ጥሪያቸውን እያሰሙ ነው።
"ማንም ሰው እንዲህ ዓይነት ጭካኔ ሊፈጸምበት አይገባም። ሺላ ያንን ሁሉ ሕመም ልታስተናግድ አይገባም ነበር'' ብሏል በኬንያ የሚገኘው አምነስቲ ኢንተርናሽናል።
በጉዳዩ ላይ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች የሚያደርጉ ቡድኖች እንደገለጹት የሺላ አስክሬን የተገኘው ከጥቂት ቀናት በፊት ነው።
የሺላን ግድያ ተከትሎ ኬንያ ውስጥ ስላለው የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎች ጉዳይ በማኅበራዊ ሚዲያዎች መነጋገሪያ ሆኗል።
የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎች መብት አቀንቃኝ ቡድኖች፣ ኬንያ ውስጥ የተለያየ ዓይነት ማግለል እና ጥላቻ እንደሚደርስባቸው የሚገልጹ ሲሆን ኑሯቸው እንደ ወንጀል እንዳይቆጠር ለማደረግ ያደረጉትም ጥረት አልተሳካም።
ሺላ በማዕከላዊ ኒዬሪ ካውንቲ እንደተገደለች የተገለጸ ሲሆን ከግድያዋ ጋር ተያይዞ ግን የተረጋገጠ መረጃ አልተገኘም።
በሌላ በኩል ደግሞ ሺላ ከመገደሏ በፊት ጾታዊ ጥቃት ተፈጽሞባት እንደነበረ የሚገልጹ ሪፖርቶች እየወጡ ነው።
ሺላ መጥፋቷ ከተገለጸ ከጥቂት ቀናት በኋላ ነው አስክሬኗ የተገኘው።
ይህንን ክስተት ተከትሎ በጉዳዩ ላይ የሚሠሩ ቡድኖች ጥያቄያቸውን እየሰነዘሩ ነው። የኬንያ ማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎችም በጉዳዩ ላይ ሲከራከሩ ከርመዋል።
የሰብአዊ መብቶች አቀንቃኟ ንጄሪ ዋ ሚግዊ በፌስቡክ ገጿ ባስተላለፈችው መልዕክት ከሺላ ጓደኛ ጋር መነጋገሯንና አብረው ማልቀሳቸውንም ገልጻለች።
ፖሊስ እስካሁን ድረስ ሺላ ለምን እንደተገደለች የተረጋገጠ መረጃ መስጠት አልቻለም።
ለሺላ የተዘጋጀ የዝክር ሥነ ሥርዓት የፊታችን ቅዳሜ እንደሚካሄድም ተገልጿል።












