ለ2ኛ ጊዜ የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ሆነው የተመረጡት ማክሮን ሕዝቡን አንድ ለማድረግ ቃል ገቡ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኢማኑኤል ማክሮን ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ሆነው እንዲያገለግሉ በድጋሚ ተመረጡ፡፡
ማክሮን ትናንት በተደረገ አገር አቀፍ ምርጫ ተቀናቃኛቸውን ማሪን ሌ ፔንን በሰፊ ልዩነት አሸንፈዋቸዋል፡፡
የቀኝ አክራሪዋ፣ ስደተኛ ጠል ናቸው የሚባሉት ማሪን ሌ ፔን ሊያሸንፉ የሚችሉበት ዕድል ስለነበረ የፈረንሳይ ምርጫ በተለይ በመላው አውሮጳ ከፍተኛ ትኩረት አግኝቶ ነበር፡፡
ሌ ፔን ሙስሊም ሴቶች ሒጃብ በአደባባይ እንዳይለበሱ ሕግ የማውጣት ፍላጎት ነበራቸው፡፡
ስደተኞችን የማባረር፣ ለአገሬው ሕዝብ በሁሉም ረገድ ቅድሚያ የመስጠት ፖሊሲም እንደሚከተሉ ቃል ገብተው ነበር፡፡
በተጨማሪም ፈረንሳይ ከኔቶ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት እንዲሁም ከአውሮጳ ኅብረት የምትወጣበትን ሁኔታ እንደሚያፈላልጉ ለደጋፊዎቻቸው ቃል ገብተው ነበር፡፡
ይህም በመሆኑ ነው የሳቸው አለመመረጥ በአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት ዘንድ እፎይታን የፈጠረው፡፡
ማክሮን በድጋሚ ፕሬዝዳንትነቱን ያሸነፉት ከድምጽ ሰጪው ሕዝብ 58.55 ከመቶ በማግኘት ነው፡፡
ሌ ፔን ድምጽ ማግኘት የቻሉት ግን 41.45 የሚሆነውን ብቻ ነው፡፡
ይሁንና ለአንድ ቀኝ አክራሪ ፓርቲ መሪ ይህን ያህል ድምጽ ማገኘት እጅግ ከፍተኛ የሚባል ሲሆን አገሪቱ ምን ያህል እንደተከፋፈለች የሚያመላክት ነው ይላሉ ተንታኞች፡፡
ማክሮን ከድል በኋላ ባደረጉት ንግግር የተከፋፈለውን የፈረንሳይ ሕዝብ አንድ ለማድረግ ቃል ገብተዋል፡፡

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ኢማኑኤል ማክሮን በተለይ ለመካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ዜጎች ደንታ የላቸውም፣ እሳቸው የሃብታም ፈረንሳዊያን ፕሬዝዳንት ናቸው በሚል ሲወቀሱ ቆይተዋል፡፡
ማክሮን የኑሮ ውድነትን መቆጣጠር አለመቻላቸውም ከፍተኛ ተቃውሞን አስነስቶባቸዋል፡፡
የምርጫ ውጤቱ ይፋ ከሆነ በኋላ ሌ ፔን ሽንፈታቸውን የተቀበሉ ሲሆን ያገኙት ድምጽ በራሱ ግን ለፓርቲያቸው ትልቅ ድል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በአውሮጳ ከሚንቀሳቀሱ ቀኝ አክራሪ ብሔርተኞች ሌ ፔን ከፍ ያለ ስምና ዝና ያላቸው ቢሆንም እሳቸውም እንደ ወላጅ አባታቸው በተደጋጋሚ ተወዳድረው ድል ሳይሳካላቸው ቀርቷል፡፡
በተለይ በዚህኛው ዙር የሳቸው ፓርቲ ከሩሲያ ባንክ ብድር መውሰዱ፣ እሳቸውም ሩሲያ ክሪሚያን ጠቅልላ በወረራ ስትወስድ ድጋፍ ማሳየታቸውና ከቪላድሚር ፑቲን ጋር የተለየ ቅርበት ማሳየታቸው በምርጫ ክርክር ወቅት ከፍተኛ ነጥብ እንዲጥሉ ሳያደርጋቸው አልቀረም፡፡
የምርጫው ውጤት ከተሰማ በኋላ የአውሮጳ አባል አገራት ከፍተኛ እፎይታ ተሰምቷቸዋል፡፡
ምክንያቱም ሌ ፔን ምርጫውን አሸንፈው ቢሆን ሁነኛ የኔቶ አባልና የአውሮጳ ኅብረት አባል ፈረንሳይ ከኅብረቶቹ ልትወጣ የምትችልበት አጋጣሚ ይኖር ስለነበረ ነው፡፡
ሌ ፔን የፑትንን ወረራ የመደገፍ አዝማሚያ ማሳየታቸው የአውሮጳ ኅብረት አባላትን አስቆጥቶ ነበር፡፡
የማክሮንን ድል ተከትሎ የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን፣ የአውሮጳ ኅብረት ፕሬዝዳንት ቮን ደር ሌዮን እንዲሁም የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ደስታቸውን ገልጸዋል፡፡
ዘለንስኪ ከምርጫው ቀደም ብሎም ቢሆን ፈረንሳዊያዊን በፍጹም ለማሪን ሌ ፔን ድጋፍ እንዳያሳዩ፣ ይለቅ ለማክሮን ድምጽ እንዲሰጡ ተማጽነው ነበር፡፡
ይህም የሆነው ተቀናቃኛቸው ማሪን ሌ ፔን ከፑቲን ጋር ያላቸው ቅርበት ስጋት ስለፈጠረባቸው ነበር፡፡
የመራጮች ቁጥር በታሪክ ዝቅተኛ ከሚባሉት አንዱ ሆኖ የተመዘገበ የትናንቱ ድምጽ አሰጣት፣ 3 ሚሊዮን የሚሆኑ መራጮች ባዶ ወረቀት ምርጫ ኮሮጆ ውስጥ ዶለዋል ተብሏል፡፡
ይህም የሚያመላክተው በርካታ መራጮች በሁለቱም እጩዎች ደስተኛ እንዳልነበረ ነው ይላሉ ተንታኞች፡፡
ማክሮን በ20 ዓመታት የፈረንሳይ የቅርብ ታሪክ ለ2ኛ ጊዜ የተመረጡ የመጀመርያው ፕሬዝዳንት ናቸው፡፡












