ብሊንከን እና ዜሌንስኪ በኪዬቭ መገናኘታቸውን አሜሪካ አስታወቀች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በዩክሬን መዲና ተገኝተው ከፕሬዝደንት ዜለንስኪ ጋር መነጋገራቸውን ዋይት ሐውስ አስታወቀ።
ብሊንከን ወደ ኪዬቭ ያቀኑት ከአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስቲን ጋር መሆኑም ተገልጸዋል።
ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች ወዲህ አንቶኒ ብሊንከን ወደ ኪዬቭ ያመሩ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣን ናቸው።
ሁለቱ ከፍተኛ የአሜሪካ መንግሥት ባለስልጣናት ከፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜለንስኪ ጋር ውይይት ማድረጋቸውን የፕሬዝዳንቱ አመካሪዎች ቀደም ሲል ገልጸው ነበር።
ምንም እንኳን የዩክሬን ባለስልጣናት ጉብኝቱን ቀድመው ይፋ ቢያደርጉም በጉዳዩ ላይ አሜሪካ አስተያየት ከመስጠጥ ተቆጥባ ቆይታ ከደቂቃዎች በፊት ትናንት እሁድ ብሊንከን እና መከላከያ ሚኒስትሩ ወደ ኪዬቭ እንዳቀኑና ከፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ጋር መነጋገራቸው ይፋ አድርጋለች።
ዋሽንግተን እንዳስታወቀችው ሁለቱ ባለስልጣናት ውይይታቸውን ጨርሰው ከዩክሬን ግዛት ወጥተዋል።
ይህንን ውይይት ተከትሎ አሜሪካ ለዩክሬንና ለሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) 713 ሚሊየን ዶላር የሚያወጣ ወታደራዊ ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባቷ ይፋ ተደገርጓል።
ከዚህ ድጋፍ ውስጥ ግማሹ ለዩክሬን የሚሰጥ ሲሆን ቀሪው ግማሽ ደግሞ የኔቶ አባል አገራት እንዲሁም ለዩክሬን ድጋፍ እያደረጉ ያሉ አገራት እንደሚከፋፈሉት አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል።
ከዚህ በተጨማሪ አሜሪካ 165 ሚሊየን ዶላር የሚያወጡ ተተኳሾችን ለዩክሬን ለመሸጥ ዝግጁ ነች ተብሏል።
በሌላ በኩል የጀርመን ምክትል ቻንስለር አገራቸው ቀደም ብላ ለዩክሬን ወታደራዊ ድጋፍ ማድረግ አለመጀመሯ ስህተት እንደሆነ ተናግረዋል።
ሮበርት ሃቤክ ከአንድ የጀርመን የዜና ወኪል ጋር ባደረጉት ቆይታ ጀርመን ለዩክሬን የምታደርገው ድጋፍ ከዓመታት በፊት መጀመር ነበረበት ሲሉ ተደምጠዋል።
''በእርግጠኝነት በጣም ቀደም ብለን ዩክሬንን መደገፍ ነበረብን። ይህንን ስል ከቀናት፣ ሳምንታት አልያም ወራት በፊት እያልኩ አይደለም። ከዓመታት በፊት ነበር የድጋፍ እጃንን መዘርጋት የነበረብን'' ብለዋል።
በአንጌላ መርክል ይመራ የነበረው የቀድሞው የጀርመን መንግሥት አስተዳደር ከሩሲያ ጋር ባለው ጠበቅ ያለ ግንኙነትና የጋዝ ግዢ ስምምነት ምክንያት ከፍተኛ ትችት ይሰነዘርበት ነበር።
ሮበርት ሃቤክ እንደሚሉት አገሪቱ የኔቶን ወታደራዊ አቅም ከፍ ለማድረግና አስተዋጽኦዋን ለመጨመር ቃል በገባችው መሰረት ጀርመን አሁን ላይ ለዩክሬን ከፍተኛ መሳሪያዎችን በማቅረብ ላይ ናት።












