በሩዋንዳ የቀድሞ ሰራተኞቹን አስሮ የገረፈው ቻይናዊ በእስራት ተቀጣ

ግለሰቦቹን አስሮ የገረፈው ቻይናዊ

የፎቶው ባለመብት, Social Media

በሩዋንዳ አንድ ቻይናዊ የታሰሩ ሰዎችን ሲገርፍ የሚያሳይ ቪዲዮ መውጣቱን ተከትሎ ፍርድ ቤቱ በማሰቃየት ወንጀል የእስር ቅጣት በይኖበታል።

ፍርድ ቤት ማክሰኞ በዋለው ችሎት ሱን ሹጁን ላይ የ20 አመት እስራት መፍረዱን ችሎቱን የተከታተለው ጋዜጠኛ ለቢቢሲ ተናግሯል።

ከቻይናዊው ጋር አብሮም በግርፋቱ ተሳትፏል የተባለ ሩዋንዳዊም የ12 አመታት እስር ተፈርዶበታል።

ታስረው ሲደበደቡ የነበሩት ግለሰቦች በሩትሲሮ ግዛት ውስጥ በሚገኘው በሱን ሹጁን በሚተዳደረው የማዕድን ማውጫ ውስጥ የቀድሞ ሰራተኞች ሲሆኑ ከስርቆት ጋር ንክኪ አላቸው ተብሏል።

ሱን ሹጁን ቀደም ሲል ተደጋጋሚ ዝርፊያ ከተፈጸመበት በኋላ ሌቦችን አስጠንቅቆ እንደነበር ተናግሯል።

ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ ሶስት ደቂቃ ርዝመት ያለው ቪዲዮ በሩዋንዳ ማህበራዊ ትስስር ገጾች በከፍተኛ ሁኔታ መጋራቱን ተከትሎ ሱን ሹጁን በቁጥጥር ስር ውሎ ነበር። ነገር ግን ከጥቂት ጊዜ በኋላም በዋስ መለቀቁ ተዘግቧል።

ቪዲዮውን የቀረጹት ግለሰቦች በተግባሩ የተቆጡ ሰራተኞች ሲሆኑ በማህበራዊ ትስስር ገጾች ከተጋራም በኋላ ቁጣን ቀስቅሷል።

በኪጋሊ የሚገኘው የቻይና ኤምባሲ በቪዲዮው ላይ የተፈጸመውን ድብደባ "ህገ ወጥ ድርጊት" ሲል ማውገዙን የሀገር ውስጥ ሚዲያ ዘግቧል።

የዓይን እማኞች ሱን ሹጁን በስርቆት የጠረጠራቸውን ግለሰቦች እንጨት እንደ መስቀል በመወጠር አስሮ ከሰቀላቸው በኋላ እንደገረፋቸው ለፍርድ ቤቱ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።