“የሩሲያ ወታደሮች ደፈሩኝ፣ ባለቤቴንም ገደሉት”

ማሳሰቢያ፡ ይህ ጽሑፍ አንባቢን ሊረብሽ የሚችል የወሲባዊ ጥቃት ይዘት አለው።
ዕለቱ ከዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን አንድ ቀን ቀደም ብሎ ነው።
አና (ስሟ ተቀይሯል) ከኪየቭ 70 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኝ ገጠራማና ፀጥ ያለ አካባቢ ትኖራለች።
የዛን ቀን አና እና ባለቤቷ ቤታቸው ሳሉ የውጭ አገር ወታደሮች ቤታቸውን ሰብረው ገቡ።
"ሽጉጥ ደቅኖብኝ በአቅራቢያ ወዳለ ቤት ወሰደኝ። 'ልብስሽን ካላወለቅሽ እተኩስብሻለሁ' አለኝ። የሚለኝን ካላደረግኩ እንደሚገድለኝ እየደጋገመ ይዝት ነበር። ከዚያም ደፈረኝ" ትላለች።
ጥቃት የፈፀመባት ግለሰብ በሩሲያ ወገን የተሰለፈ ቺቺኒያዊ እንደሆነ ትናገራለች። ቀጭን እና ወጣት እንደሆነም ታስታውሳለች።
"እየደፈረኝ ሳለ አራት ወታደሮች መጡ። በቃ አለቀልኝ ብዬ ፈራሁ። ከዚያ ግን ወታደሩን ወሰዱት። በድጋሚ አላየሁትም።"
ከቺቺኒያዊው ወታደር ያስጣሏት የሩሲያ ወታደሮች እንደሆኑ ታምናለች።
አና ወደ ቤቷ ስትመለስ ባለቤቷ ሆዱን በሽጉጥ ተመቶ አገኘችው።
"እኔን ለማትረፍ ብሎ ተከትሎኝ ለመሮጥ ሲሞክር ነበር። ግን ተኮሱበት።"
እሷና በጥይት የቆሰለው ባለቤቷ በጎረቤት ቤት ተደበቁ። በውጊያው ሳቢያ ባለቤቷን ወደ ሆስፒታል መውሰድ አልቻሉም።
ከሁለት ቀናት በኋላ ባለቤቷ ሕይወቱ አለፈ።
አና የደረሰባትን ስትናገር እንባዋን ማቆም ይሳናታል። ከጎረቤቷ ጋር ሆና ቤቷ ጀርባ ባለቤቷን ቀብራለች።
መቃብሩ አናት ላይ ከእንጨት የተሰራ መስቀል ተተክሏል።
አሁን አና በአቅራቢያዋ ከሚገኝ ሕክምና መስጫ የሥነ ልቦና ድጋፍ እያገኘች ትገኛለች።

ሕይወቷን ያተረፉት ወታደሮች ቤቷ ለቀናት ቆይተዋል። በሽጉጥ እያስፈራሩ የባለቤቷን ንብረት እንድትሰጣቸው እንዳስገደዷት ትናገራለች።
"ቤቱን ጥለው ሲሄዱ አደንዛዥ እፅ እና ቫያግራ አገኘሁ። አደንዛዥ እፅ ከመውሰዳቸው በተጨማሪ ይሰክሩ ነበር። አብዛኞቹ ገዳዮች፣ ደፋሪዎች፣ ዘራፊዎች ናቸው። መልካም የሚባሉት ጥቂት ናቸው።"
ከአና ቤት አቅራቢያ አንዲት ሴት ተደፍራ እንደተገደለች ቢቢሲ ሰምቷል።
አናን የደፈራት ወታደር አና ቤት ከመሄዱ በፊት ይህችን ሴትም እንደደፈራት የዓይን እማኞች ይናገራሉ።
ይህች ሴት በ40ዎቹ ዕድሜ ክልል ነበረች። ከቤቷ ወስደው በአቅራቢያቸው የሚገኝ ቤት መኝታ ክፍል ውስጥ ተይዛ ነበር።
የቤቱ ባለቤቶች ጦርነቱ ሲጀመር ነበር የሸሹት።
ለኑሮ ውብ ሆኖ የተሠራው ይህ ቤት አሁን አሰቃቂ ድርጊት የተፈፀመበት ሆኗል።
መኝታ ቤቱ ውስጥ ያለው ፍራሽ እና አልጋ ልብስ በደም ጨቅይቷል።
በክፍሉ የሚገኝ መስታወት ላይ ይህች ሴት የት እንደተቀበረች በከንፈር ቀለም ተጽፏል።
ኦክሳና የተባለች ጎረቤት ለቢቢሲ እንደገለጸችው መስታወት ላይ የጻፉት የሴቲቷን አስክሬን አግኝተው የቀበሩ ወታደሮች ናቸው።

"ጉሮሮዋ ላይ እንደተወጋች ወይም ጉሮሮዋ በስለት እንደተሰነጠቀ የሩሲያ ወታደሮች ነግረውኛል። በጣም ብዙ ደም ነው የፈሰሳት" ትላለች።
በቤቱ በሚገኝ የአትክልት ስፍራ ሴቲቷ ተቀብራለች።
ፖሊሶች አስክሬኗን ለምርመራ ቆፍረው አውጥተዋል።
አስክሬኗ የተገኘው ያለ አንዳች ልብስ ነበር። አንገቷ ላይ ስለት የገባበት ጥልቅ ጠባሳም ይታያል።
የኪየቭ የፖሊስ መሪ አንድሪ ነብያቶቭ ከኪየቭ በስተምዕራብ 50 ኪሎ ሜትር ርቆ የተፈፀመ ወንጀልን ነግረውናል።
በዚህ አካባቢ ታዳጊ ልጅ ያላቸው በ30ዎቹ ዕድሜ ክልል የሚገኙ ጥንዶች ይኖሩ ነበር።
"መጋቢት 9 ብዙ የሩሲያ ወታደሮች ወደ ጥንዶቹ ቤት ገቡ። ባልየው ሚስትና ልጁን ለማዳን ሲሞክር ገደሉት። ከዚያም ሁለት ወታደሮች በተደጋጋሚ ሚስቱን ደፈሯት" ይላሉ።
የፖሊስ መሪው እንደሚሉት ወታደሮቹ ሦስት ጊዜ እየተመላለሱ ይቺን ሴት ደፍረዋታል። ራሷን ለመከላከል ከሞከረች ታዳጊ ልጇን እንደሚያጠቁ እያስፈራሩዋት ነበር።
ልጇን ለማዳን ስትል ወታደሮቹን አልተከላከለቻቸውም።
ወታደሮቹ ሲሄዱ ቤቱን አቃጥለው የጥንዶቹን ውሾችተኩሰውባቸው ነበር።
ይህች ሴት ከታዳጊ ልጇ ጋር አምልጣ ፖሊስ ዘንድ ሄዳለች።
ፖሊሶች መረጃ ለመሰብሰብ ወደቤቷ ሲሄዱ ያገኙት የቀድሞውን የሞቀ የደመቀ መኖሪያ አልነበረም።

የታዳጊ መጫወቻ፣ ሳይክል ወድቋል። ለቅዝቃዜ የሚለበስ ጫማ ተጥሏል።
ባልየው የተቀበረው ግቢው ውስጥ ነው። ፖሊሶች አስክሬኑን መርምረዋል። ጉዳዩን ወደ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ለመውሰድም አስበዋል።
የዩክሬን እምባ ጠባቂ ኃላፊ ሊዩዳምያላ ዴኒሶቫ ብዙ የወንጀል ድርጊቶች እየመዘገቡ እንደሆነ ይናገራሉ።
"ቡቻ ግዛት ውስጥ በአንድ መጠለያ ቤት ውስጥ ዕድሜያቸው ከ14 እስከ 24 የሆኑ ታዳጊዎች እና ሴቶች ተደፍረዋል። ዘጠኙ አርግዘዋል" ብለዋል።
"የሩሲያ ወታደሮች ሴቶቹን ሲደፍሯቸው ከሌላ ሰው ጋር ወሲብ መፈፀም እስከሚያስጠላቸው ድረስ እንደሚደፍሯቸው ይነግሯቸዋል። ዩክሬናዊ ልጅ እንደማይወልዱም ጭምር።"
ለአደጋ ጊዜ በተዘጋጀ የስልክ መስመር፣ በዋትስአፕ እና በቴሌግራም ብዙ ጥቆማ እየደረሳቸው ነው።
"የ25 ዓመት ሴት የ16 ዓመት እህቷ መንገድ ላይ ፊት ለፊቷ እንደተደፈረች ነግራናለች። 'ይሄ በሁሉም የናዚ ሴተኛ አዳሪዎች ላይ የሚደርስ ነው' እያሉ እየጮሁ ነበር እህቷን የደፈሯት።"
አሁን ላይ ወሲባዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ባጠቃላይ የደረሰባቸውን ሰቆቃ ለመናገር ፈቃደኛ ስላልሆኑ በሩሲያውያን ወታደሮች የተፈፀመውን ጥቃት ለመለካት እንደሚያስቸግር ሊዩዳምያላ ዴኒሶቫ ይናገራሉ።
ወሲባዊ ጥቃት ከደረሰባቸው መካከል በስልክ ሥነ ልቦናዊ ድጋፍ የሚጠይቁ አሉ።
የተባበሩት መንግሥታት የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን መድፈርን ጨምሮ በሌሎችም የጦር ወንጀሎች ተጠያቂ የሚያደርግበት ልዩ ችሎት እንዲያቋቁም ይፈልጋሉ።
አና "ይህ ሁሉ የሚሆነው ለምንድን እንደሆነ ፑቲንን መጠየቅ እፈልጋለሁ። የምኖረው በድንጋይ ዘመን አይደለም። ለምን አይደራደርም? ለምን ይወረናል? ለምንስ ይገድለናል?" ስትል ትጠይቃለች።












