ከተጠፋፋን በሚል የልጇ ጀርባ ላይ አድራሻዋን የጻፈችው ዩክሬናዊት መነጋገሪያ ሆነች

ልጇ ጀርባ ላይ የተጻፈው አድራሻ

የፎቶው ባለመብት, SASHA MAKOVIY

በዩክሬን የተፋፋመውን ጦርነት ለመሸሽ ስትዘጋጅ ምና አልባት ከሞትኩኝ በሚል የሁለት ዓመት ልጇ ጀርባ ላይ አድራሻዋን የጸፈችው እናት መነጋገሪያ ሆናለች።

ዩክሬናዊቷ እናት ይህንን ስታደረግ ምን ያህል በተስፋ መቁረጥ ውስጥ እንደነበረች ለቢቢሲ ተናግራለች።

ሳሻ ማኮቪይ ኪየቭን የተባለችውን ከተማ ከጦርነት በሚሸሹበት ወቅት ቢጠፋፉ ወይም ቢገደሉ ልጇ ቪራ እርዳታ እንድታገኝ ስሟን፣ እድሜዋን እና የስልክ ቁጥሮች በጀርባዋ ላይ እንዳሰፈረች ትናገራለች።

ማኮቪይ "ምናልባት እኛ ብንሞት ራሷን ፈልጋ እንድታገኝ እና ማንነቷን እንድታውቅ ይረዳታል በሚል ነው የጻፍኩት" ብላለች።

አሁን ቤተሰቡ ከፈራው አደጋ ተርፎ አሁን በፈረንሳይ ውስጥ "በፍቅር እና እንክብካቤ" ተቀምጧል።

ልክ ፈረንሳይ እንደደረሱ የቪራ እናት ማኮቪይ አድራሻውን የያዘውን የልጇን ጀረባ ፎቶ በማንሳት አጋርታዋለች። ይህንንም ተከትሎ ጉዳዩ በማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች መነጋገሪያ ሆኗል።

"የልጄ ጀርባ ላይ ይህንን ሳደርግ የጦርነቱ የመጀመሪያ ቀን ነበር። ከኪየቭ ለመሸሽ ያለንን ነገር እያዘጋጀን ነበር። ጉዟችን ደህንነቱ የተጠበቀ መሆኑን እርግጠኛ አልነበርኩም" ስትል ለቢቢሲ ራዲዮ 4 ተናግራለች።

ከፍተኛ የፍንዳታ ድምጾች በሚሰሙበት ጊዜ ጓዛቸውን ሸክፈው እና ስለመንገዳቸው በቂ መረጃ ሳይኖራቸው ነበር ስደት የጀመሩት። "ከቤታችን እንደወጣን በሮኬቶች እንደማንመታ እርግጠኛ አልነበርኩም" ስትልም አክላለች።

"እኛ ከሞትን ወይም ቪራ ከጠፋች ማንነቷን ወይም ቤተሰቧቿ ማን እንደሆኑ ላታውቅ ትችላለች የሚለው ትልቁ ፍርሃቴ ነበር" ስትል አስረድታለች ማኮቪይ።

ማኮቪይ ተስፋ ያደረገችው ምናልባት መላው ቤተሰቡ የከፋ ነገር ቢገጥመው እና ቪራ ብትተርፍ ከጀርባዋ ባለው አድራሻ ማን እንደነበረች ለማወቅ ምናልባት አንድ ቀን ቢያንስ የእናቷን የማኅበራዊ ሚዲያ ለማየት ይረዳታል የሚል ነው።

"አንዳንድ መረጃዎችን ከበይነ መረቡ ታገኛለች ብዬ አሰብኩ። ምናልባት ኢንስታግራም ላይ ልታገኝ እና ወላጆቿን ማየት ትችል ይሆናል" ስትልም በዚህ እሳቤ ያንን ማድረጓን ተናግራለች።

ከረጅም፣ አድካሚ እና በፍርሃት ከተሞላ ጉዞ በኋላ ፈረንሳይ መድረሳቸውን የምትናገረው ማኮቪይ የጦርነቱ ሁኔታ በጣም አሰቃቂ እንደሆነ እና በቀላሉ ወደ ውጪ መውጣት አስፈሪ እንደነበር ታስታውሳለች።

"ቪራ ደህና ነች። በጣም ትንሽ ስለሆነች ምን እየተከናወነ እንደሆነ ለመረዳት አልቻለችም። ከኔ የሆነ ስሜት ሊጋባባት ይችላል። አሁን ባለችበት እድሜ በጣም ደስተኛ ነኝ - በጣም!" ብላለች ማኮቪይ።