ስዊድን እና ፊንላንድ ኔቶን ከመቀላቀል እንዲቆጠቡ ሩሲያ አስጠነቀቀች

የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ

ሩሲያ ኔቶን መቀላቀል ትርፉ በአውሮፓ አለመረጋጋትን መፍጠር ነው በሚል ምክንያት ስዊድን እና ፊንላንድ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅቱን ከመቀላቀል እንዲቆጠቡ አሳሰበች።

የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ)፤ ፍጥጫን የሚፈጥር ጥምረት መሆኑ እንደቀጠለ ነው ብለዋል።

የቃል አቀባዩ አስተያየት የተሰማው፤ ስዊድን እና ፊንላንድ ከጥቂት ወራት በኋላ ኔቶን ለመቀላቀል ይፋዊ ጥያቄ ያቀርባሉ መባሉን ተከትሎ ነው።

የሁለቱ አገራትን የኔቶ አባልነት ጥያቄን አሜሪካ ትደግፋለች ተብሎ ይጠበቃል። ስዊድን እና ፊንላንድ ኔቶን ከተቀላቀሉ የሕብረቱ አባላት ቁጥር ወደ 32 ከፍ ይላል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ ባሳለፍነው ሳምንት የኔቶ አመራሮች ከሄልሲንኪ እንዲሁም ከስቶኮልም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ውይይት አድርገዋል ብሏል።

ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ ከመፈጸሟ በፊት ኔቶ ተጨማሪ አገራትን በአባልነት ከመያዝ እንዲቆጠብ ስትጠይቅ ነበር።

በወረራው ማግስት በርካታ የኔቶ ጦር በምስራቅ አውሮፓ የተሰማራ ሲሆን ፊንላንድ እና ስዊድን የኔቶ አባል አገራት እንዲሆኑ ድጋፎችም ጨምረዋል።

የፊንላንድ የምክር ቤት አባላት በዚህ ሳምንት አገሪቱ የሕብረቱ አባል ትሁን አትሁን በሚለው ላይ ከደኅንነት ተቋማት ሪፖርት ይቀርብላቸዋል ተብሏል። የፊንላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳና ማሪን አስተዳዳራቸው ሕብረቱን ለመቀላቀል የአባልነት ማመልከቻ ለማስገባት የሚያደርገውን ውይይት በጥቂት ወራት ውስጥ ያጠናቅቃል ብለዋል።

ከሩሲያ ጋር 1340 ኪሎ ሜትር የምትጋራው ፊንላንድ የሞስኮ የዩክሬን ወረራ ብዙ ካሳሰባት አገራት መካከል አንዷ ነች።

ለረጅም ዓመታት የኔቶን መስፋፋት ስትቃወም የኖረችው ሞስኮ፤ የኔቶ አባል አገራት መብዛት በቀጠናው አለመረጋጋትን ያመጣል ስትል ትሞግታለች።

ባለፈው ሳምንት የክሬምሊን ቃል አቀባይ ሁለቱ አገራት ኔቶን የሚቀላቀሉ ከሆነ ሩሲያ የኃይል ሚዛኑን ለመጠበቅ የራሷን እርምጃ ትወስዳለች ብለው ነበር።

ይሁን እንጂ ሁለቱ አገራት ደኅንነታቸውን ለማረጋገጥ ተጨማሪ በጀት ለጦራቸው እያስተዋወቁ ነው።

ሄልሲንኪ ለአገሪቱ ጦር ሰል አልባ አውሮፕላኖችን ለመግዛት 14 ሚሊዮን ዩሮ መድባለች። ስዊድን ደግሞ ለአገሪቱ ጦር የምታደርገውን ወጪ በ317 ሚሊዮን ዶላር እንደምትጨምር አስታውቃለች።

ኔቶ ምንድን ነው?

የሰሜን አትላቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት ወይም ኔቶ በአውሮፓውያኑ 1949 ላይ በ12 አገራት ነበር የተመሰረተው። በወቅቱ አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ፈረንሳይን ያካትት ነበር።

አባል አገራት ወታደራዊ ጥቃት ከደረሰባቸው እርስ በርሳቸው ለመደጋገፍ ነው ይህንን ስምምነት የተፈራረሙት።

አባል አገራት ከዚህ ስምምነት የደረሱት የሶቪየት ሕብረት አውሮፓ ውስጥ የመስፋፋት እቅድን ለመከላከል ያለመ ነበር።

እአአ 1955 ላይ ሶቪየት ደግሞ ለዚህ ስምምነት ምላሽ በሚመስል መልኩ የምሥራቅ አውሮፓ ኮምዩኒስት አገራት ጥምረት የሆነውን 'የዋርሶ ስምምነት' የተሰኘ ስብስብ አቋቋመች።

ነገር ግን እአአ 1991 ላይ የሲቪየት ሕብረት መፍረስን ተከትሎ በርካታ የዋርሶ ስምምነትን የፈረሙ አገራት ድርጅቱን እየለቀቁ ኔቶን መቀላቀል ጀመሩ።

በአሁኑ ወቅት ኔቶ 30 አባል አገራት አሉት። እነዚም፦

አልባኒያ፣ ቤልጂየም፣ ቡልጋሪያ፣ ካናዳ፣ ክሮሺያ፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ዴንማርክ፣ ኢስቶኒያ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ግሪክ፣ ሃንጋሪ፣ አይስላንድ፣ ጣሊያን፣ ላቲቪያ፣ ሊቱዌኒያ፣ ላክሰዘምበርግ፣ ሞንቴኔግሮ፣ ኔዘርላንድስ፣ ሰሜን መቄዶኒያ፣ ኖርዌይ፣ ፖላንድ፣ ፖርቹጋል፣ ሩሜኒያ፣ ስሎቫኪያ፣ ስሎቬኒያ፣ ስፔን፣ ቱርክ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ዩናይትድ ስቴትስ ናቸው።