አማራ ክልል የአምነስቲ እና የሂውማን ራይትስ ዎች የጋራ ሪፖርትን አጣጣለ

የፎቶው ባለመብት, Amhara Comm Bureau
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ትላንት ሚያዝያ 2/2014 ዓ. ም. በሰጠው መግለጫ አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂውማን ራይትስ ዎች በጋራ ያወጡት ሪፖርት ገለልተኛ አይደለም ሲል አጣጣለ።
ባሳለፍነው ሳምንት ሁለቱ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ቡድኖች ባወጡት የጋራ ሪፖርት በምዕራብ ትግራይ፣ የትግራይ ተወላጆች ላይ በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ተፈጽመዋል ማለታቸው ይታወሳል።
ሁለቱ ዓለም አቀፍ ተቋማት እንደሚሉት ከሆነ ከጦርነቱ መቀስቀስ ጀምሮ የአማራ ኃይሎች እና ባለሥልጣናት በምዕራብ ትግራይ ባሉ የትግራይ ተወላጆች ላይ ከጦር እና በሰብአዊነት ላይ ከሚፈጸሙ ወንጀሎች ጋር የሚስተካከሉ መጠነ ሰፊ ወንጀሎች ፈጽመዋል።
አምነስቲ እና ሂዩማን ራይትስ ዎች በሪፖርታቸው በምዕራብ ትግራይ በአፍሪካ ኅብረት የሚመራ ሰላም አስከባሪ ኃይል እንዲሰማራ እንዲሁም እንደ ፋኖ ያሉ አደረጃጀቶች ከምዕራብ ትግራይ እንዲወጡ ጭምር አሳስበዋል።
የአማራ ክልል በበኩሉ ሪፖርቱ የአማራ ክልል የልዩ ኃይል ፖሊስ አባላትን፣ ሚሊሻዎችን እና የፋኖ አደረጃጀትን በሕገ ወጥ ድርጊቶች መወንጀሉን አጣጥሏል።
ሪፖርቱን "የሕዝባችንን ጩኸት ለመቀማትና የአገራቸውን ሉዓላዊነትና ህልውናቸውን ለማስከበር ብሔራዊ ግዴታቸውን በተወጡት የመንግሥት ኃላፊዎች፣ የፀጥታ መዋቅር አባላትና በሐቀኛ ፋኖዎች መካከል ያለውን ጠንካራ ትስስር በመስበር ወደፊትም በሉዓላዊነታችን ላይ የሚጋረጥ አደጋ ቢመጣ በአንድነት መታገል የማይችል አቅመ ቢስ ኅብረት እንዲኖር የማድረግን ዓላማ ያነገበ ነው" ሲልም ኮንኗል።
በሁለቱ የመብት ተሟጋች ተቋሞች የወጣው ሪፖርት "የአማራ ሕዝብን እንደ ሕዝብ ፍትሕ በመንፈግ በኢትዮጵያዊነቱ እና በዓለም አቀፍ የፍትሕ፤ የሰብአዊ መብት ተከራካሪና የዴሞክራሲ እሴት ግንባታ ባለድርሻ አካላት ላይ ተስፋ እንዲቆርጥ" ያለመ ነው ሲልም ክልሉ ወቅሷል።
ሪፖርቱን "ሚዛናዊነት፣ ገለልተኛነት እና ተአማኒነት የሌለው" ሲል ትላንት በአማራ ክልል የወጣው መግለጫ ይከሳል።
በአፍሪካ ኅብረት የሕዝቦች መብት ጥበቃ ኮሚሽን፣ በተባበሩት መንግሥታት ጽሕፈት ቤት የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ከፍተኛ ኮሚሽን እና በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በጋራ እየተከናወነ የሚገኘውን የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ምርመራ "ዋጋ ያሳጣዋል" ሲልም መግለጫው ይወቅሳል።
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ባወጣው መግለጫ አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂውማን ራይትስ ዋችን "የአገሪቱን ውስጣዊ የፖለቲካ ለውጦችን የማስተጓጎል" እና "በክልሎች መካከል የሚገኙ የወሰን ጉዳዮች ላይ ብያኔ የመስጠት" አላማ ያላቸው ሲልም ኮንኗል።
አያይዞም ሪፖርቱ "ለአንድ ወገን ያደላ" ነው ብሏል መግለጫው።
የመብት ተሟጋች ተቋማቱ ያወጡትን ሪፖርት ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት ባወጣው መግለጫ ሪፖርቱ "ለፖለቲካዊ አላማ ሊውል ይችላል" የሚል ስጋት እንዳለው መግለጹ ይታወሳል።
በተጨማሪም "ሪፖርቱ አንድን ቡድን ባልተመጣጠነ ሁኔታ የሚኮንን እና የእርቅ ሂደትን ፈታኝ የሚያደርግ" ሲል የኢትዮጵያ መንግሥት አቋሙን አስታውቋል።
የአምነስቲ እና ሂውማን ራይትስ ዋች የጋራ ሪፖርት፣ በምዕራብ ትግራይ በሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ላይ በሰብሽዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል እና የዘር ማጽዳት እንደተፈጸመባቸው ያመለክታል።
ሁለቱ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ቡድኖች ባወጡት ሪፖርት ላይ ከአጎራባች የአማራ ክልል አካባቢዎች የሚሄዱ የፀጥታ ኃይሎችና ኃላፊዎች ንጹሀን ዜጎች ላይ ጥቃት እያደረሱ እንደሆነና በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችና የጦር ወንጀሎችን እየፈጸሙ እንደሆነ አመልክተዋል።
የአማራ ክልል በበኩሉ የፀጥታ ኃይሉ እንዲሁም ፋኖ አደረጃጀት 'በንብረት ዝርፊያ'፣ 'በአፈናቃይነት'፣ 'በመድፈር'፣ 'በዘር ማጥፋት'፣ 'በጦር ወንጀልና እና በከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰት' መወንጀሉን ተቃውሟል።
ክልሉ በማንኛውም የሰው ልጅ ላይ የሚፈፀም የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን፣ የዘር ማጥፋትንም ሆነ የጦር ወንጀሎችን እንደሚያወግዝ እና ጥፋተኞችን ለሕግ ለማቅረብ የሚደረግ ምርመራን እንደሚደግፍ ጠቅሷል።
የመብት ተሟጋች ተቋማቱ ባወጡት ሪፖርት ላይ "427 ተጠቂዎችን በአካልና በስልክ ቃለ መጠይቅ በማድረግ ሪፖርቱን አዘጋጅተናል" ማለታቸውን የአማራ ክልል ጠቅሶ "በስልክ ቃለ መጠይቅ አደረግንላቸው ያሏቸው አንዳንዶቹ 'የዘር ማጥፋት ወንጀል ሰለባ ናቸው' የተባሉ የሕብረተሰብ ክፍሎች በአማራ ክልል ውስጥ የሚኖሩ በመሆናቸው በስልክ ለማግኘት መቻላቸውን መግለጻቸው እርስ በእርሱ ይጣረሳል" ሲል አጣጥሏል።
በተጨማሪም ሱዳን ከሚገኙ ስደተኞች ተሰበሰበ የተባለውን መረጃ በመተመለከተ "በ30፣ 2013 ዓ. ም. የማይካድራ ጭፍጨፋን ከትግራይ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ጋር ሆኖ ከመራውና ‹ሳምሪ› ከተሰኘው ኢ-መደበኛ አደረጃጀት እንደሆነ እናምናለን" ሲል የአማራ ክልል ገልጿል።
ሪፖርቱን ያወጡትን ተቋማት "በፖለቲካዊ ወገንተኝነት" የአማራ ክልል ከሷል። መረጃ የተሰበሰበበትን መንገድም "አንድን ማኅበረሰብ ብቻ የሚወክሉ" ሲል አጣጥሏል።
የሪፖርቱ ውጤት "ለሰብአዊ መብቶች መከበር አወንታዊ ሚና ከመጫወት ይልቅ ችግሮችን የሚያወሳስብ፣ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን የሚደረጉ ጥረቶችን የሚያጨናግፍ" ሲልም መግለጫው ያክላል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂውማን ራይትስ ዋችን "በፖለቲካ ወገንተኝነት" የወነጀለው የአማራ ክልል አያይዞም "በአሸባሪነት የተፈረጀውን የህወሓትን የፖለቲካ አቋም በሚጋራና የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ሕዝብን የዘመናት በደል በሚክድ ሁኔታ በሪፖርታቸው ወገንተኛ ሆነው መገኘታቸው የቆሙለትን አላማ እንደካዱ ይቆጠራል" ሲል ወቅሷል።













