የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾቹ ምዕራብ ትግራይን አስመልክቶ ያወጡት ሪፖርት ምን ይላል?

የፎቶው ባለመብት, AFP
በምዕራብ ትግራይ በሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ላይ በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል እና የዘር ማጽዳት እንደተፈጸመባቸው አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂዩማን ራይትስ ዋች ትናንት ባወጡት ጥምር የምርመራ ሪፖርት አመላክተዋል።
ሁለቱ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድኖች ቡድኖች ባወጡት ሪፖርት ላይ ከአጎራባች የአማራ ክልል አካባቢዎች የሚመጡ የጸጥታ ኃይሎችና ኃላፊዎች ንጹሀን ዜጎች ላይ ጥቃት እያደረሱ ስለመሆኑና በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችና የጦር ወንጀሎችን እየፈጸሙ እንደሆነ አመልክተዋል። የአማራ ክልል መንግስት ግን ውንጀላውን እንደማይቀበለው አስታውቋል።
የዚህን ሪፖርት መውጣት ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት በሰጠው ምላሽ ሪፖርቱ ፍጹም ተቀባይነት የሌለው ነው ብሏል።
የፌደራሉ መንግሥት ሁለቱ ተቋማት ጉዳዩን ለመመርመር የተጠቀሟቸውን ፖለቲካዊ ጉዳዮች ትክክለኛነት ላይ ጥያቄ አቅርቧል።
የውስጥ ወሰን ጉዳዮች ሊታዩ የሚገባቸዉ ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን ባላቸው አካላት ነው ያለው መንግሥት፤ "እንዲህ አይነቱ ሪፖርታቸው ለፖለቲካ ፍጆታ እንደሚውልም የታወቀ ነው። ይህ አመለካከት ምርመራው በተገቢው ጥንቃቄ አለመፈፀሙን ከማሳየቱም በላይ በፍፁም ተቀባይነት የሌለው ነው።" ብሏል።

በሪፖርቱ የተጠቀሰ አንድ የ23 ዓመት የትግራይ ተወላጅ ለመርማሪዎች በሰጠው ቃል በአማራ ልዩ ኃይል አባላት የሞት አፋፍ ላይ እስከሚደርስ ድረስ ድብደባ እንደተፈጸመበት ገልጿል።
''ከዚህች ምድር እናጠፋችኋለን። ይሄ መሬት የኛ ነው። እዚህ አካባቢ የትግራይ ተወላጅ የሚኖረው ለመጨረሻ ጊዜ ነው'' የሚሉ ቃላትን ይናገሩ እንደነበርም ገልጿል።
የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ምዕራባዊ ትግራይ በተለይ ለጋዜጠኞችና ለእርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች መድረስ የማይቻል አካባቢ ከሆነ ሰነባብቷል። ማንኛውም አይነት መገናኛ መንገዶችም ተቋርጠዋል።
ይህ ምዕራባዊ የትግራይ ክፍል በርካታ የመሬት ይገባኛል ጥያቄዎች የሚነሱባቸው አካባቢዎችን የሚያካትት ሲሆን ለረጅም ዓመታት ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጭቅጭቆችን ሲያስነሳ ነበር። ይህንን ተከትሎም በአዋሳኝ አካባቢዎች በሚኖሩ ሰዎች መካከል ግጭትና ውጥረት ሁሌም አለ።
በጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ መንግስት እና በትግራይ አውራ የፖለቲካ ፓርቲ መካከል የተፈጠረውን ውዝግብ ተከትሎ በተፈጠረው ግጭት ሲንከባለሉ የቆዩ ችግሮችን ለመፍገታት ሰዎች የራሳቸውን አማራጭ መከተል ጀምረዋል።
ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ የአማራ ኃይሎች ከመከላከያ ጋር በመጣመር ወደ ምዕራባዊ ትግራይ ግስጋሴ በማድረግ አዲስ አስተዳደራዊ መዋቅርም ዘርግተዋል።
ሁለቱ ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ይፋ ባደረጉት ባለ 207 ገጽ የጋራ የምርመራ ውጤት 423 ሰዎች ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው ሲሆን አብዛኛዎቹ ከመሰል ጥቃቶች መትረፍ የቻሉ ናቸው። ከዚህም በተጨማሪ ምርመራው እንደ ማስረጃ እንዲሆን የሳተላይት ምስሎችንም አካቷል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂዩማን ራይትስ ዋች ጦርነቱን ተከትሎ ከአንድ ዓመት በላይ በፈጀ ምርመራቸውና መረጃ የማሰባሰብ ስራቸው ወቅት በተለይ ምዕራባዊ ትግራይ በእጅጉ ከተጎዱትና በርካታ የመብት ጥሰቶችና ግድያዎች የተፈጸሙበት ነው። ትኩረትም አግኝቶ እንዳልነበር ተቋማቱ በጋራ ያወጠት ሪፖርት ያመለክታል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል የማጥቃት ዘመቻውን በጀመረበት ወቅት ማይካድራ ውስጥ 229 ሰዎች በሁለቱም ወገን በኩል የተገደሉ ሲሆን በወቅቱም በርካታ ዘግናኝ ግድያዎች ተፈጽመዋል።
ይህንንም ተከትሎ ሪፖርቱ እንደሚለው በበቀል የአማራ የጸጥታ ኃይሎች የትግራይ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ሰንዝረዋል። የትግራይ ተወላጆች ቤትና ንብረቶች ተዘርፈዋል እንዲሁም ተወርሰዋል።
በምርመራው ቃለ መጠይቅ ካደረጉት ተጎጂዎች መካከል አንዷ የሆነችው ጀሚላ ዳንሻ በምትባለው ከተማ ውስጥ የጸጉር ቤት ንግድ ላይ ተሰማርታ ነበር ኑሮዋን የምትገፋው።
አንድ ቀን ጠዋት ላይ ወደምትሰራበት ሱቅ ወታደሮች መጥተው የሰባትና የሁለት አመት ልጆቿ ፊት እንደደፈሯት የ27 ዓመቷ ጀሚላ ገልጻለች።
''እናንተ ትግሬዎች ከዚህ አካባቢ መጥፋት አለባችሁ'' ይሉ ነበር በማለት ሁኔታውን ታስታውሳለች።
ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው ሌሎች ሰዎች ደግሞ በርካታ የምዕራብ ትግራይ አካባቢዎች በአማራ የጸጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ትግርኛ መናገር መከልከሉንና ከአካባቢው ለቅቀው እንዲሄዱ ጫና ይደረግባቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። በየቀኑም በ24 አልያም በ72 ሰአታት ውስጥ አካባቢውን ለቅቀው ካልወጡ እንደሚገደሉ መልዕክት ይደርሳቸው እንደበርም ገልጸዋል።
ከጥቃቶቹ የተረፉ እንደሚገልጹት ጥር 9/ 2013 ዓ.ም. ላይ አዲ ጎሹ በተባለችው ከተማ ታጣቂዎች 60 የሚሆኑ የትግራይ ተወላጆችን ተከዜ ወንዝ አቅራቢ በመውሰድ ተኩሰው እንደገደሏቸውና ይህ ክስተት ደግሞ በርካቶች ለህይወታቸው በመስጋት እንዲሸሹ ማድረጉን ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, AFP
ከዚህ ግድያ ከተረፉት መካከል መስፍን አንደኛው ናቸው። '' አሰልፈውን ሁላችን ላይ ተኩስ ከፈቱ። የቀኝ ትከሻዬ እና የቀኝ እጄ ላይ ተመትቻለው። አጠገቤ የነበሩ ሰዎች ይረግፉ ነበር። ድንገት ከወደቅኩበት ስነቃ በሬሳዎች ተከብቤ እራሴን በአስከሬን ተከብቤ አገኘሁት'' በማለት ያስታውሳሉ የ57 ዓመቱ መስፍን።
አቶ መስፍን ከወደቁበት ተነስተው ወደ ጫካ ውስጥ ሲገቡ ባካባቢው የነበሩ ከብት ጠባቂዎች እንዳገኟቸውና ደብቀው እንዲያገግሙ ማድረጋቸውን ለመርማሪዎች ገልጸዋል። ምንም እንኳን እሳቸው ከሞት ቢተርፉም ወንድ ልጃቸውና የሴት ልጃቸው ባለቤት ግን ተገድለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ሪፖርቱ እንደሚያመለክተው የትግራይ ተወላጆች ከብቶች፣ እርሻ እንዲሁም መኖሪያ ቤቶች በጸጥታ ኃይሎች ኢላማ ተደርገው የአካባቢው ነዋሪዎች ምግብ እንዳያገኙ መደረጉንም አመላክቷል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂዩማን ራይትስ ዋች እንደሚሉት በመቶዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች ያለ ሕግ አግባብ በቁጥጥር ስር የሚገኙ ሲሆን በአፋጣኝ እንዲፈቱም ጠይቀዋል።
"ይህ ዘር የማጽዳት ዘመቻ የተካሄደው በጅምላ እስራት እና ሰቆቃ፣ ወሲባዊ ጥቃት፣ ከህግ አግባብ ግድያ፣ ሰብአዊ እርዳታ በመከልከል እና የትግራይ ተወላጆችን በግዳጅ በማፈናቀል በተፈጸሙ ተከታታይ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ነው።" በማለት በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምስራቅ አፍሪካ አጥኚ አቶ ፍስሃ ተክሌ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ሁለቱ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች በመቶዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች በህገወጥ መንገድ ታስረው እንደሚገኙና በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጠይቀዋል።
በተጨማሪም እንደ ፋኖ ያሉ ኢ-መደበኛ አደረጃጀቶችና ሚሊሻዎች ትጥቅ እንዲፈቱና ከደረሱት ጥሰቶች ጋር ግንኙነት ያላቸው ባለስልጣናት ታግደው በአፍሪካ ህብረት የሚመራ አለም አቀፍ ሰላም አስከባሪ ሃይል በምዕራብ ትግራይ እንዲሰማራ ጠይቀዋል።
ጦርነቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩትንም ለረሃብ ዳርጓል።
ምንም እንኳን ከሁለት ሳምንት በፊት የሰብአዊ ተኩስ አቁም ታውጆ ብዙ የጭነት መኪናዎች ከወራት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ትግራይ ዋና ከተማ ቢደርሱም ጦርነቱ ቀጥሏል።
ነገር ግን አምነስቲ እንደሙለው ምዕራብ ትግራይ ክልል አሁንም የሚፈልገውን እርዳታ እያገኘ አይደለም ብሏል።
በጦርነቱ ሁለቱም ተሳታፊ አካላት በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተወንጅለዋል።
በተለይም የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ ቅድስት ተብላ በምትጠራው አክሱም ከተማ ላይ የጅምላ ጭፍጨፋ ፈጽመዋል እንዲሁም ሰፊ ወሲባዊ ጥቃትን መፈጸመባቸው የተገለጸ ሲሆን እንዲሁም የትግራይ ሃይሎች ባለፈው አመት አማራን በወረሩበት ወቅት የጦር ወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል።












