ለፈረንሳይ ፕሬዝደንትነት ማክሮን እና ማሪን ሌ ፔን ለፍጻሜ ቀረቡ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በፈረንሳይ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እየተደረገ ነው፡፡
12 ተፎካካሪዎች በቀረቡበት የመጀመርያ ድምጽ አሰጣጥ ሁለቱ ከፍተኛ ድምጽ ያገኙት ዕጩዎች ተለይተዋል፡፡
ለ2ኛ ጊዜ ፈረንሳይን ለመምራት የሚወዳደሩት ኢማኑኤል ማክሮን ሁነኛ ተፎካካሪያቸውን ለይተዋል፡፡
የቀኝ አክራሪ ፓርቲ መሪ ማሪን ሌ ፔን የኢማኑኤል ማክሮን ቀንደኛ ተቀናቃኝ ሆነው ቀርበዋል፡፡
ሁለቱ እጩዎች ለፕሬዝዳንትነት እጩ ሆነው ሲቀርቡ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡
ቀኝ አክራሪዋ ማሪን ሌ ፔን ለፕሬዝዳንትነት ሲወዳደሩ ይህ ለ3ኛ ጊዜ ሲሆን ከዚህ በኋላ ከተሸነፉ ምናልባትም የፖለቲካ ሕይወታቸው መጨረሻ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል፡፡
የትናንቱን የድምጽ አሰጣጥ ተከትሎ ከፍተኛ ድምጽ ያገኙት ማክሮን፣ ‹‹በፍጹም እንዳትሳሳቱ፣ ምንም እርግጠኛ የሆነ ነገር የለም፡፡›› ሲሉ ለደጋፊዎቻቸው በስሜት የተሞላ ንግግር አድርገዋል፡፡
በፈረንሳይ ትናንት በተደረገ የመጀመርያ ዙር ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ማክሮን ከፍተኛውን ድምጽ ያገኙ ሲሆን ሌ ፔን 2ኛውን ከፍተኛ ድምጽ በማግኘታቸው ነው ወደ 2ኛ ዙር ምርጫ እየተኬደ ያለው፡፡
ትናንት በተደረገው ድምጽ አሰጣጥ 97 ከመቶ ድምጽ ቆጠራ ተጠናቋል፡፡
በዚህም መሠረት ከጠቅላላ ድምጽ ሰጪዎች 27.35% ለማክሮን ድምጻቸውን ሰጥተዋል፡፡
ስደተኛ-ጠል ናቸው የሚባሉት ቀኝ አክራሪ ፓርቲን የሚመሩት ማሪን ሌ ፔን 23.97% ድምጽ በማግኘት 2ኛ ሆነዋል፡፡
ግራ ዘመም ፓርቲን የሚመሩትና ስሜት የሚኮረኩር ንግግር በማድረግ የተዋጣላቸው ዣን ሉክ ሚሌቾን 21.7% ከመቶ ድምጽ በማግኘት 3ኛ ሆነዋል፡፡
ዣን ሉክ ፈረንሳዊያን በፍጹም ድምጻቸውን ለቀኝ አክራሪዋ ሌ ፔን እንዳይሰጡ አሳስበዋል፡፡
ትናንትና ለፕሬዝዳንትነት እጩ ሆነው የቀረቡት ማክሮንን ጨምሮ 12 ፖለቲከኞች ነበሩ፡፡
ሆኖም የድምጽ ሰጪውን 10 ከመቶ እና ከዚያ በላይ ድምጽ ማግኘት የቻሉት ሦስቱ ፓርቲዎች ብቻ ናቸው፡፡
አሸናፊውን ለመለየት ማክሮን እና ማሪን ሌ ፔን ለፍጻሜ ቀርበዋል፡፡
ሌ ፔን እና ማክሮን ከወዲሁ ከፍተኛ የምረጡኝ ቅስቀሳ ውስጥ ገብተዋል፡፡
የቀኝ አክራሪዋ ላ ፔን ከማክሮን ደጋፊዎች ውጭ ያሉ ፈረንሳዊያን በሙሉ ድምጻቸውን ለሳቸው እንዲሰጡ ተማጽነዋል፡፡
ትንንሽ ድምጽ ያገኙ ፓርቲዎችና ደጋፊዎቻቸው ድጋፋቸውን ለማሪን ሌ ፔን ከሰጡ ማክሮን የማሸነፍ ዕድላቸው አጣብቂኝ ውስጥ ሊገባ እንደሚችል ተገምቷል፡፡
ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በፈረንሳይ ታሪክ በወጣትነት ዕድሜ ፕሬዝዳንትነትን የተቆናጠጡ መሪ ናቸው፡፡
ሥልጣን ሲረከቡ 39 ዓመታቸው ነበር፡፡
ለዚህኛው ምርጫ በቂ ቅስቀሳ እንዳላደረጉ የተነገረ ሲሆን ለምርጫው 8 ቀናት ሲቀሩት ብቻ ነው ሞቅ ወዳለ ቅስቀሳ የገቡት ተብሏል፡፡
ይህም የሆነው በዋናነት በዩክሬን-ሩሲያ ጦርነት ጉዳይ በመጠመዳቸው ነው ተብሏል፡፡
የሁለተኛ ዙር ድምጽ አሰጣጡ የሚደረገው ከሁለት ሳምንት በኋላ በሚያዚያ 24 ነው፡፡
ማዳም ማሪን ሌ ፔን በፈረንሳይ ቀኝ አክራሪ ፓርቲ መሪነት ዘለግ ላለ ጊዜ የቆዩ ናቸው፡፡
ለመጤዎች በጎ አመለካከት የሌላቸው ሲሆን በአደባባይ ኢስላማዊ ሒጃብ እንዳይለበስ ሕግ እደነግጋለሁ ብለዋል፡፡
ከዚህም ሌላ ፈረንሳይ ከአውሮጳ ኅብረት እንድትወጣ ሕዝበ ውሳኔ እንዲደረግ ይፈልጋሉ፡፡
ወደ ፈረንሳይ የሚገቡ ስደተኞችን ቁጥር በእጅጉ ለመቀነስና ድንበርን ለመዝጋትም ፍላጎት አላቸው፡፡












