የሶማሌ ክልል የክልሉ ኃይል በኦሮሚያ ተሰማርቷል መባሉን አስተባበለ

[ፋይል ፎቶ] የኦሮሚያ ፖሊስ 'በሸኔ' ቡድን ላይ ኦፕሬሽን ማካሄድ ጀምሪያለሁ ባለበት ወቅት የተጋራ ምስል።

የፎቶው ባለመብት, Oromia Police

የምስሉ መግለጫ, [ፋይል ፎቶ] የኦሮሚያ ፖሊስ 'በሸኔ' ቡድን ላይ ኦፕሬሽን ማካሄድ ጀምሪያለሁ ባለበት ወቅት የተጋራ ምስል።

የሶማሌ ክልል የክልሉ ኃይል እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ ከሚጠራው ቡድን ጋር ለመዋጋት በኦሮሚያ ክልል ተሰማርቷል መባሉን አስተባበለ።

የሶማሌ ክልል መንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣን የሆኑት አብፊካድር ራሺድ መንግሥት ለቢቢሲ እንደተናገሩት ሸኔ ብሎ ከሚጠራው ቡድን ጋር ለመዋጋት ወደ ኦሮሚያ ክልል የተሰማራ የሶማሌ ክልል ኃይል የለም ብለዋል።

ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጠራው ቡድን ቃል አቀባይ የሆኑት ኦዳ ተርቢ፤ በደቡባዊ የኦሮሚያ ክፍል ከፌደራሉ መንግሥት ጎን የሶማሌ ክልል ኃይል ተሰማርቶ እየተዋጋ ነው ብለው ነበር።

የሶማሌ ክልል መንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣን የሆኑት አብፊካድር ራሺድ ምንም እንኳ እስካሁን ድረስ የክልላቸው ጦር በኦሮሚያ ክልል ባይሰማራም እንዲሰማራ ጥያቄ ከቀረበለት ግን ወደ ክልሉ ሊገባ ይችላል ብለዋል።

ይህ የተሰማው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ሲል የፈረጀውን እና መንግሥት 'ሸኔ' ሲል የሚጠራውን ቡድን በ30 ቀናት ውስጥ የማስወገድ ኦፕሬሽን ጀምሬያለሁ ካለ በኋላ ነው።

የኦሮሚያ ክልል ከሁለት ቀናት በፊት በብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ባስነገረው መግለጫ "የሽብር ቡድኑን ሙሉ በሙሉ ለመደምሰስ የሚያስችል ጠንካራ ዘመቻ" ተጀምሯል ብሏል።

መግለጫው አክሎም የፌደራሉ እና የክልል ኃይሎች በተቀናጀ መልክ በወለጋ፣ በጉጂ፣ በምዕራብ እና ሰሜን ሸዋ በሚንቀሳቀሱ የቡድኑ አባላት ላይ እርምጃ እየወሰዱ ነው ብሏል።

የክልሉ መንግሥት መግለጫ ጨምሮም "እስካሁን በተወሰደው የተቀናጀ እርምጃ በርካታ የቡድኑ አባላት ተደምስሰዋል" ብሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፉት ጥቂት ቀናት በመንግሥት ኃይሎች እና በታጣቂ ቡድኑ መካከል ከፍተኛ ውጊያ እየተካሄደ መሆኑን የታጣቂ ቡድኑ ቃል አቀባይ ኦዳ ተርቢ በትዊተር ገጻቸው ላይ ገልጸዋል።

እንደ ቃል አቀባዩ ከሆነ ከፍተኛ ውጊያ እየተካሄደባቸው ከሚገኝባቻው አካባቢዎች መካከል፤ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ፣ ምዕራብ ሸዋ፣ ደቡብ ኦሮሚያ እንዲሁም ምስራቅ እና ምዕራብ ወለጋ ይገኙበታል።

ከአንድ ሳምንት በፊት ደግሞ በደቡብ ኢትዮጵያ ሞያሌ ከተማ አካባቢ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ በሚጠራው ቡድን መካከል ግጭት ተከስቶ እንደነበረ ተገልጿል።

በሁለቱ ኃይሎች መካከል ግጭት ከመቀስቀሱ ከቀናት በፊት የአገር መከላከያ ሠራዊት "በአሸባሪው የሸኔ ቡድን ላይ የማያዳግም እርምጃ እየተወሰደ ነው" ሲል በፌስቡክ ገፁ ጽፏል።

የመከላከያ ሠራዊት የደቡብ ዕዝ የኋላ ደጀን አስተባባሪ ኮሎኔል ግርማ አየለን ዋቢ አድርጎ "የሽብር ቡድኑ ሲጠቀምባቸው የነበሩ የተለያዩ ዓይነት የጦር መሣሪያዎች እና ተተኳሽችን ጨምሮ ለሽብር ቡድኑ አመራሮች ሲጓጓዝ የነበረ መድሃኒት በቁጥጥር ስር ውለዋል" ብሏል።

መንግሥት 'ሸኔ' በሚለው ቡድን እና በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች መካከል በተለይ በደቡብና በምዕራብ ሸዋ እና በወለጋ ዞኖች ግጭት ሲቀሰቀስ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

መንግሥት በታጣቂ ቡድኑ ላይ ድል እየተቀዳጀሁ ነው በማለት በተለያዩ ጊዜያት ቢገልጥም ታጣቂውም ቡድን በበኩሉ በመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች ላይ ኪሳራ እያስከተልኩ ነው ይላል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በደቡብ ምዕራብ አካባቢዎች ሰላማዊ ሰዎች ላይ ለሚደርስ ጥቃት ተጠያቂው 'ኦነግ ሸኔ' ነው ሲል መንግሥት ይኮንናል።