ለወራት በሩሲያ ቁጥጥር ስር የምትገኘው አሜሪካዊቷ ቅርጫት ኳስ ተጫዋች በምን ሁኔታ ነው ያለችው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሚቀጥለው ወር አሜሪካ የሴቶች የቅርጫት ኳስ ውድድር ሲጀመር በሊጉ ውስጥ ደምቀው መውጣት ከቻሉት ኮከቦች መካከል አንደኛዋ አትኖርም።
የፊኒክስ ሜርኩሪ ተጨዋቿ ብሪትኒ ግራይነር ካሳለፍነው የካቲት ወር ጀምሮ ሩሲያ ውስጥ ተይዛ የምትገኝ ሲሆን ዋይት ሀውስ እስካሁን በጉዳዩ ላይ ምንም መረጃ መስጠት አልቻለም።
የ31 ዓመቷ ብሪትኒ ገሪነር ሩሲያ ውስጥ ከአደንዛዥ እጽ ጋር በተያያዘ እስር ቤት እንደምትገኝ ይታመናል። ሩሲያ በምትገባበት ወቅት የአየር ማረፊያው ሰራተኞችች ባደረጉባት ምርመራ በቦርሳዋ ውስጥ የእጸ ፋርስ ዘይት ተገኝቷል የሚል ጥርጣሬም አለ።
የተባለው ነገር እውነት ሆኖ ከተገኘና ብሪትኒ ግራይነር ጥፋተኛ የምትባል ከሆነ እስከ 10 ዓመት የሚደርስ እስር እንደሚጠብቃት ተገልጿል።
ብሪትኒ ግራይነር በዓለማችን ምርጧ ሴት የቅርጫት ኳስ እንደሆነች በርካቶች ይስማማሉ። በቅርጫት ኳስ ሕይወቷም የኮሌጅ ቻምፒየንሺፕ፣ የአሜሪካ የሴቶች ቅርጫት ኳስ ውድድር፣ ዩሮሊግ እንዲሁም የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ማሸነፍ የቻለች ድንቅ ስፖርተኛ ነች።
ከአውሮፓውያኑ 2015 ጀምሮ ደግሞ የአሜሪካ የሴቶች ቅርጫት ኳስ ሊግ ለእረፍት ሲቋረጥ ወደ ሩሲያ በመሄድ ለአንድ ቡድን ትጫወታለች።
ምንም እንኳን በርካቶች ብሪትኒ ግራይነር ዓለማችን ካየቻቸው ምርጥ የቅርጫት ኳስ ኮከቦች መካከል አንዷ እንደሆነች ቢስማሙም አሁን ላይ ላይ ግን ስላለችበት ሁኔታ ምንም አለመታወቁ ጥቂት የማይባሉ አሜሪካውያንን አስቆጥቷል።
በሩሲያ ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር ከዋለች ሁለት ወር የሞላት አሜሪካዊቷ ስፖርተኛ ቤተሰቦችም ሆነ የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት እና የአሜሪካ የሴቶች ቅርጫት ኳስ ሊግ በጉዳዩ ላይ ምንም አይነት አስተያየት አለመስጠትን መርጠዋል።
ባሳለፍነው ወር የሞስኮ ፍርድ ቤት እንዳስታወቀው የብሪትኒ ግራይነርን ጉዳይ ለመከታተል ሲባል እስከ ግንቦት አጋማሽ ድረስ እንድትቆይ መወሰኑን አስታውቋል።
የዋይት ሀውስ ፕረስ ሰክረተሪዋ ጄን ሳኪ ሰⶉ ዕለት በጉዳዩ ላይ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ ብዙም መረጃ ከመስጠት የተቆጠቡ ሲሆን ''በሌላ አገር በእስር ላይ ስለሚገኙ አሜሪካውያን ማውራት ብዙም ጠቃሚ አይደለም'' በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።
''ምናልባት ዜጋችንን ለማስመለስ የምናደርገውን ጥረት ሊያደናቅፈው ይችላል'' ብለዋል።
'' በሩሲያ ቁጥጥር ስር የሚገኙ ሁሉም አሜሪካውያንን ቀጣይነት ባለው እና ጊዜውን በጠበቀ መልኩ መጎብኘት እንድንችል በተደጋጋሚ እየጣርን ነው። የብሪትኒ ጉዳይንም በተመለከተ በቅርበት እየተከታተልነው ነው'' ሲሉም አክለዋል።
ብሪትኒ ገራይነር በዘንድሮው የቅርጫት ኳስ ሊግ ብትሳተፍ ኖሮ ለስምነተኛ ተከታታይ ዓመቷ ይሆነ የነበረ ሲሆን በሊጉም ከፍተኛ ድምቀትን ትፈጥር እንደነበር አድናቂዎቿ እና የቡድን አጋሮቿ ገልጸዋል።
ልክ እንደ ብሪትኒ ሁሉ ሌሎች የአሜሪካ የሴቶች ቅርጫት ኳስ ሊጎች ውስጥ የሚሳተፉ ስፖርተኞች ሊጉ ሲዘጋ ወደ ሌሎች አገራት በመሄድ ይጫወታሉ። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ተጨማሪ ገቢን ለማግኘት ነው። ለምሳሌ ሩሲያ አሜሪካ ከሚከፈላቸው አምስት እጥፍ ትከፍላለች።












