በዱባይ የሚገኝ ሆቴል በድሮን ሲመታ የሚያሳይ ቪዲዮ። ተንቀሳቃሽ ምሥሉ የተቀረፀው ከሆቴሉ ማዶ ካለው አፓርታማ በረንዳ ላይ ነው። ከፍተኛ ቦታ ላይ ካለው ሆቴል ግርጌ የሚነሳው ትልቅ ብርቱካናማ የእሳት ኳስ ከሆቴሉ ሕንጻ በረንዳ ላይ ይታያል።

ኢራን በመካከለኛው ምሥራቅ ፍርሃት የፈጠረችበት ርካሹ ድሮን

ዶናልድ ትራምፕ ቅዳሜ ዕለት አሜሪካ በኢራን ላይ የአየር ጥቃትን ስትጀምር የአገሪቱን የሚሳዔሎች እና የሚሳዔል ኢንዱስትሪ "ሙሉ በሙሉ ይደመሰሳል" ብለዋል። ነገር ግን ስለ ኢራን ድሮኖች ያሉት ነገር አልነበረም።

ጦርነቱ ከተጀመረ ሳምንት ያለፈው ሲሆን፣ ኢራን የአገራትን የአየር መከላከያን ለማጨናነቅ እና በቀጣናው ትርምስ ለመፍጠር በማሰብ በመካከለኛው ምሥራቅ በሚገኙ ዒላማዎች ላይ ከሁለት ሺህ በላይ ርካሽ ድሮኖችን አስወንጭፋለች።

እነዚህ አጥፍቶ ጠፊ (ካሚካዚ) ሻሄድ ድሮኖች ከዒላማቸው ጋር በሚጋጩበት ጊዜ የሚፈነዱ ፈንጂዎችን ይዘው ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳሉ። እስካሁን በአሜሪካ ወታደሮች ላይ እጅግ የከፋው ጉዳት የደረሰው አንድ ድሮን በኩዌት የሚገኝ ጦር ሰፈርን መትቶ ስድስት የአሜሪካ ወታደሮች በመገደላቸው ነው።

የመካከለኛው ምሥራቅ አገራትን የሚያሳይ ካርታ
የመካከለኛው ምሥራቅ አገራትን የሚያሳይ ካርታ

አብዛኞቹ ጥቃቶች የተፈጸሙት በባሕረ ሰላጤው በሚገኙ የአሜሪካ አጋሮች ላይ ሲሆን፣ ሁሉም የአሜሪካ ጦር ሠራዊት አባላት እና መሳሪያዎችን በተወሰነ ደረጃ የሚያስተናግዱ ናቸው።

በተጨማሪም ኢምባሲዎችን፣ ቁልፍ የኃይል መሠረተ ልማቶችን፣ የንግድ አውሮፕላን ማረፊያዎችን እና ቅንጡ ሆቴሎችን ዒላማ አድርገዋል።

የመካከለኛው ምሥራቅ አገራትን የሚያሳይ ካርታ

አንዳንድ ጥቃቶች በተጨናነቁ ከተሞች ላይ የደረሱ ሲሆን፣ ይህም በጎዳናዎች እና በባሕረ ሰላጤው አገራት መንግሥታት ላይም ስጋት ፈጥሯል። አንዳንድ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት ይህ “ሽብር ለመፍጠር” እና ግጭቱን በቶሎ እንዲቆም በአሜሪካ ላይ ጫና ለመፍጠር የኢራን ስትራቴጂ አካል ሊሆን ይችላል።

ትክክለኛነቱ በቢቢሲ የተረጋገጠ አንድ ቪዲዮ የኢራን ድሮን በባህሬን ዋና ከተማ ማናማ ወደ ሚገኘው የአሜሪካ የባሕር ኃይል አምስተኛ ምድብ ዋና መሥሪያ ቤት ወዳለ ራዳር ሚመስል ነገር በከፍተኛ ፍጥነት ወደ ታች ተምዘግዝጎ ሲመታ ፍርስራሹ በአየር ላይ ሲበተን እና መዋቅሩ ሲፈርስ ያሳያል።

ሌላ ቪዲዮ ደግሞ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በሚገኘው ሰው ሠራሽ ደሴት ላይ ከሚገኝ ሆቴል ጋር ሲጋጭ በከተዋ ውስጥ ንዝረትን እና ግዙፍ የእሳት ኳስ የፈጠረ ከባድ ፍንዳታ ሲፈጥር አሳይቷል።

በባህሬን ዋና ከተማ ማናማ በሚገኘው የአሜሪካ ጦር ሰፈር ላይ የደረሰውን ጥቃት የሚያሳይ ፎቶ
በባህሬን ማናማ የሚገኘውን የአሜሪካ ጦር ሰፈር ከሚያሳይ ቪዲዮ ላይ የተወሰደ ፎቶ። ራዳር የሚመስለው ነገር በድሮን ጥቃት ከተመታ በኋላ የእሳት ኳስ እና ፍርስራሾች በአየር ላይ ሲበተኑ ያሳያል።
በባህሬን ማናማ የሚገኘውን የአሜሪካ ጦር ሰፈር ከሚያሳይ ቪዲዮ ላይ የተወሰደው ፎቶ ራዳር መሳሪያ የሚመስለው ቁስ በድሮን ከተመታ በኋላ የእሳት ኳስ እና ፍርስራሾች በአየር ላይ ሲበተኑ ያሳያል።

የድሮን ጥቃት በተለይ በቀጣናው የነዳጅ ማምረቻ ዘርፍ ላይ ያደረሰው ተፅእኖ የጎላ ነው። በባሕረ ሰላጤው ዳርቻ ራስ ታኑራ ውስጥ የሚገኘው የሳዑዲ አረቢያ ትልቁ የነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ ላይ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት የእሳት ቃጠሎ በመነሳቱ ምርት አቁሟል።

በዓለም ትልቁ የተፈጥሮ ጋዝ ማስተላለፊያ ማዕከል የሆነው የኳታር ተቋም የኢራን ድሮኖች ጥቃት ዒላማ በመሆኑ ምክንያት ተዘግቷል።

ድሮኖች ባላቸው ቀላል ዲዛይን እና ለማምረት በአንጻራዊነት ርካሽ በመሆናቸው በስፋት ጥቅም ላይ ውለው በቀጣናው ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ ነው። በኢራን የሚመረተው ረዥም ርቀት በመጓዝ ዒላማውን መምታት የሚችለው ሻሂድ 136 ድሮን ከ20,000 እስከ 50,000 ዶላር የሚያስወጣ ነው።

ሻሂድ 136 ድሮን ሰው የሚያሳይ ግራፊክስ። ከላይ በግራ በኩል 1.75 ሜትር ቁመት ያለው አንድ ትንሽ የመዝናኛ ድሮን በእጁ የያዘ ሰው ምሥል ይታያል። በቀኝ በኩል የሻሂድ ድሮንን የሚያሳይ ምሥል እና 3.5 ሜትር ርዝመት እና 2.5 ሜትር ክንፍ ያለው መሆኑን ያሳያል። ተጨማሪ ጽሑፍ ይነበባል፡ ሰዎች ስለ ድሮን ሲያስቡ ብዙውን ጊዜ ለፎቶግራፍ የሚያገለግሉ ትናንሽ ሞዴሎች ይጠቀሳሉ። ሻሂድ 136 ግን በጣም ትልቅ ሲሆን፣ ርዝመቱ 3.5 ሜትር እና ክንፉ 2.5 ሜትር ነው።
የአፍንጫውን ሾጣጣ ክፍል የሚያጎላ የሻሂድ ድሮን ቴክኒካዊ ምሥል የሚያሳይ ግራፊክ። ወደ አፍንጫ የሚያመለክት ጽሑፍ እንዲህ ይነበባል፡- አፍንጫው በውስጡ 50 ኪሎ ግራም የሚመዝን ፈንጂ ያለው አረር ይዟል፣ 500 ኪሎ ግራም የሚመዝን አረር ካላቸው ከአንዳንድ ባለስቲክ ሚሳኤሎች በጣም ያነሰ ቢሆንም ከፍተኛ ጉዳት ለማድረስ በቂ ነው።
በክንፉ ላይ ያለውን ዝርግ ክፍልን የሚያጎላ የሻሂድ ድሮን ቴክኒካዊ መግለጫን የሚያሳይ ግራፊክ። ወደ ዝርግ ክፍሉን የሚያመለክት ጽሑፍ ይነበባል፡- አብሮ በተሠራ አንቴና በኩል የሳተላይት የቅኝት ሥርዓት አንቴና ይጠቀማል
የሻሂድ ድሮን ቴክኒካዊ ገለፃ የሚያሳይ ግራፊክስ፡ ሞተሩን እና የሚሽከረከር ከኋላ ያለው ክፍል ጎልቶ ይታያል። የደመቀውን ቦታ የሚያመለክት ጽሑፍ እንዲህ ይነበባል፡ ተሽከርካሪ ሞተር የተገጠመለት ሲሆን ይህም ከፍተኛ ድምጽ ያወጣል።

ልዩ የሆነው የሻሂድ ከፍተኛ የንዝረት ድምጽ ከቅርብ ቀናት ወዲህ በቀጣናው በስልኮች በተቀረጹ ቪዲዮዎች ላይ ተሰምቷል። አስገራሚው ድምጽ ከታች ባለው ቪዲዮ ላይ በግልፅ ይሰማል፣ ይህም አንድ ድሮን በባህሬን ዋና ከተማ ማናና ቅዳሜ እና እሁድ አንድ ሕንጻን ሲመታ ያሳያል።

https://ichef.bbc.co.uk/images/ic/raw/p0n4rdcz.png

ከብዙ ተራ ድሮኖች በተለየ ሻሂድ ድሮን በአየር ላይ እያለ በርቀት መቆጣጠሪያ የሚሠራ አይደለም። ይልቁንም የሳተላይት ቅኝት አንቴና ዘዴን በመጠቀም ወደ ሚመታው ዒላማ የተቀመጠለትን መንገድ ለመከተል እንዲችል አስቀድሞ ፕሮግራም ይደረጋል። በዚህም ሲነሳ የታለመለትን መንገድ ተከትሎ ወደ ሚመታው ዒላማ በቀጥታ ያቀናል። ድሮኑ 2500 ኪሜ ርቀት መጓዝ የሚችል ሲሆን፣ ከቴህራን ተነስቶ እስከ ግሪክ አቴንስ መብረር ይችላል።

በተለይ ከባላስቲክ ሚሳዔሎች ጋር ሲነጻጸር ፈጣን ባይሆንም፤ ድሮኑ ባለው አነስ ያለ መጠን እና በዝቅተኛ ከፍታ ላይ በመብረር በሚሳዔል ላይ በሚያተኩሩ ራዳሮች እንዲሁም በሌሎች የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓቶች ሳይታይ ማለፍ ይችላል።

ሻሂድ 136 ድሮን እንዴት እንደሚሠራ ሲነሳ፣ በሰማይ ላይ እየበረረ ከዚያም ወደ ሕንጻ ተጠግቶ ሲያጠቃ የሚያሳይ ግራፊክስ ምሥል። ድሮኑ በሮኬት ማስወንጨፊያ በመታገዝ ከመሬት ተነስቶ በዝቅተኛ ከፍታ ላይ እስከ 2500 ኪሜ ሊጓዝ ይችላል; ብዙውን ጊዜ የጠላት መከላከያዎችን ለማለፍ በርካታ መጠን ያላቸው ድሮኖች በአንድ ላይ ይሰማራሉ። ከዚያም ወደ ዒላማው ላይ በፍጥነት በመምዘግዘግ ተጋጭቶ ይፈነዳል።

ሻሄድ ድሮኖች በዩክሬን ጦርነት ውስጥ ብዙ ሕዝብ በሚበዛባቸው ከተሞች እና የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ለማድረስ ሩሲያ ተጠቅማባቸዋለች። ኢራን ሻሂድ ድሮኖችን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለአጋሯ ሩሲያ ሰጥታለች፤ አሁን ደግሞ ሩሲያ በኢራን ዲዛይን ላይ በመመሥረት የራሷን ድሮን እያመረተች ነው።

የቀድሞ የአሜሪካ የባሕር ኃይል፣ የሲአይኤ ወታደራዊ መኮንን እና የመካከለኛው ምሥራቅ መከላከያ የተባለው ተቋም ምክትል ረዳት ፀሐፊ የሆኑት ሚክ ሙልሮይ ድሮኖቹ ቀደም ሲል በተከሰቱ ግጭቶች ውስጥ “በከፍተኛ ሁኔታ ውጤታማ መሆናቸውን” በማረጋገጥ፣ አሜሪካም የራሷን ዓይነት መሥራቷን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሉካስ ተብሎ የሚታወቀው በዝቅተኛ ወጪ የተሠራ እና ያለአንቀሳቃሽ የሚበር የጥቃት ድሮንን አሜሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ ባለፉት ቀናት ጥቅም ላይ አውላለች። በመካከለኛው ምሥራቅ የአሜሪካ ጦር ኃይሎች አዛዥ አድሚራል ብራድ ኩፐር የኢራንን ዲዛይን በመውሰድ "በማሻሻል ተመልሰው በኢራን ላይ ጥቅም ላይ ውለዋል" ብለዋል።

ከሳምንት በፊት በባሕረ ሰላጤው ከተሰማራችው ዩኤስኤስኤስ ሳንታ ባርባራ የጦር መርከብ ላይ የአሜሪካ ቴክኒሻኖች ሉካስ የተባለውን ድሮን ሙከራ ሲያደርጉ የሚያሳይ ፎቶግራፍ።
የአሜሪካ ጦር በቅርቡ የሉካስ ድሮኖች ቡድን በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ አቋቁሟል

አሜሪካ ምን ያህል ድሮኖች እንዳሰማራች ባይገልጽም፤ ኢራን ምን ያህል እያስወነጨፈች እንደሆነ መረጃዎች እየወጡ ነው። የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እስካሁን ከ1,000 በላይ የኢራን ድሮኖች ወደ ግዛቷ መወንጨፋቸውን፣ ነገር ግን 71ቱ ብቻ የመከላከያ ሥርዓቷን አልፈው መግባታቸውን አሳውቃለች። እንዲከሽፉ የተደረጉትን አየር ላይ ለማምከን ከፍተኛ ዋጋን የሚያስከፍል ነው።

ልዩ የጂፒኤስ ማፈኛ መሳሪያዎችን እና የጨረር ጦር መሳሪያ ዘዴዎችን መጠቀምን ጨምሮ ሻሂድ ድሮኖችን በተለያዩ መንገዶች ማምከን ይቻላል። ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ ብዙዎቹ በተዋጊ ጄቶች ወይም ውድ በሆኑት ከመሬት ወደ አየር በሚተኮሱ ሚሳዔሎች እየተመቱ እየወደቁ ይገኛሉ።

ኢራን በ2024 በመቶዎች በሚቆጠሩ ድሮኖች እስራኤልን ስታጠቃ የዩናይትድ ኪንግደም አየር ኃይል ተዋጊ ጄቶች እያንዳንዳቸው 200 ሺህ ፓውንድ የሚያወጡ ሚሳዔሎችን በመተኮስ መትቶ መጣሉ ተዘግቧል። ከታች ያለው ቪዲዮ ባለፈው ሳምንት በዮርዳኖስ አየር ክልል ውስጥ በዩናይትድ ኪንግደም አየር ኃይል ጄት የተወሰደ ተመሳሳይ እርምጃን ያሳያል።

ከዩኬ አየር ኃይል ተዋጊ ጄት የተተኮሰ ሚሳዔል የኢራን ድሮንን በዮርዳኖስ አየር ክልል ውስጥ ሲመታ የሚያሳይ ከቪዲዮ ላይ የተወሰደ ፎቶ። ጥራት በሌለው ምሥል ላይ አንድ ድሮን በሰማይ ላይ የሚታይ ሲሆን፣ የተተኮስበት ሚሳዔል የፈጠረው ድንገተኛ ፍንዳታ ደማቅ ብርሃን እና ስብርባሪ በሰማይ ላይ ሲበተን ያሳያል።

አሜሪካን ኢንተርፕራይዝ በተባለው የባለሙያዎች ተቋም ውስጥ ባልደረባ የሆኑት ኒኮላስ ካርል እንደሚሉት ኢራን ድሮኖች እና ሚሳዔሎችን ጥቅም ላይ ማዋሏ አሜሪካ እና አጋሮቿ የሚሳዔል መከላከያ ክምችታቸውን እንዲጠቀሙ አስገድዷቸዋል።

በተጨማሪም የኢራን መንግሥት በአሜሪካ እና በአካባቢው አጋሮቿ ላይ "ሽብር እና የሥነ ልቦና ጫና ለመፍጠር" በመሞከር ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ለማስገደድ የሚያደርገው ጥረት ነው ይላሉ ካርል።

ኢራን ለምን ያህል ጊዜ ይህንን ጫና በማሳረፍ መቀጠል እንደምትችል ግልጽ አይደለም። ኢራን ከጦርነቱ በፊት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የሻሂድ ድሮኖችን በጅምላ ታመርት ነበር ተብሎ ይታመናል፤ ነገር ግን አሜሪካ እና እስራኤል ለቀናት ከፈጸሙባት ጥቃት በኋላ ምን ያህሉ ክምችቷ ሳይነካ እንዳለ አይታወቅም።

ከኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ጋር ግንኙነት ያለው ፋርስ የዜና ወኪል ባለፈው ሳምንት ያሠራጨው ቪዲዮ ከመሬት በታች ያለ ምሽግ በሚመስል ስፍራ የተደረደሩ ድሮኖችን ያሳያል፤ ቪዲዮው ግን መቼ እንደተቀረጸ አይታወቅም።

ኢራን ድሮኖችን ለማከማቸት የምትጠቀመውን ከመሬት በታች የሚገኝ ማከማቻን ያሳያል የተባለ የቪዲዮ ምሥል። በዋሻው ግድግዳ ዙሪያ በርካታ ቁጥር ያላቸው ድሮኖች ተሰልፈው ይታያሉ።

ባለፈው ሐሙስ አድሚራል ኩፐር በኢራን የተወነጨፉ ድሮኖች ቁጥር ከጦርነቱ የመጀመሪያ ቀን ጀምሮ በ83 በመቶ የቀነሰ ሲሆን፣ ያስወነጨፈቻቸው ባለስቲክ ሚሳዔሎች ደግሞ በ90 በመቶ ቀንሷል ብለዋል።

ካርል ደግሞ “ኢራን የሚሳዔል እና የድሮን ጥቃቷን ለማስቀጠል እየጣረች ሲሆን፣ ይህ ደግሞ በቀጣዮቹ ቀናት የአሜሪካ እና የእስራኤል ወታደራዊ ጫና እየቀጠለ ሲሄድ የበለጠ ከባድ ሊሆንባት ይችላል" ይላሉ።

ምሥል እና ቪዲዮ

የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር፣ የዩኬ መከላከያ ሚኒስቴር፣ ፋርስ የዜና ወኪል