ከ600 በላይ የሩሲያ ታንኮች እንዴት በዩክሬን ወታደሮች በቀላሉ ሊወድሙ ቻሉ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት 2ኛ ወሩን ሊሻገር ነው፡፡
በፈጣንና መብረቃዊ ግስጋሴ ኪየቭን ለመያዝ የሞከረችው ሩሲያ፣ ከዩክሬን በኩል ያልጠበቀችው መከላከል ገጥሟታል፡፡
አሁን ከኪየቭ ከበባ ወታደሮቿን አስወጥታለች፡፡
በቀጣይ ሳምንታት በምሥራቅ የዩክሬን ክፍል ዶንባስ የለየለት ደም አፋሳሽ ጦርነት እንደሚደረግ እየተጠበቀ ነው፡፡
የሳተለያይት ምሥሎች ሩሲያ ወታደሮቿን ወደዚያው እያስጠጋች እንደሆነ ያሳያሉ፡፡
የወደብ ከተማ ማሪዮፖል አሁንም ሙሉ በሙሉ በሩሲያ እጅ አልወደቀችም፡፡ ዩክሬናዊያን እየተፋለሙ ነው፡፡

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዚህ ጦርነት አንድ ያልተመደ ነገር ተከስቷል፡፡
የሩሲያ ታንኮች እዚያም እዚም ጋይተው ከጥቅም ውጭ ሆነው ይታያሉ፡፡
የወታደራዊ ሳይንስ ተንታኞች ሩሲያ እንዴት ይህን ሁሉ ታንክ በአጭር ጊዜ ልታጣ ቻለች ሲሉ መጠየቅ ጀምረዋል፡፡
ከ600 በላይ ታንክ ማጣት እንዲሁ እንደዋዛ የሚታይ አይደለም፡፡ በርካታ የዓለም አገራት እንደ አገር ይህ የታንክ ብዛት እንኳ የላቸውም፡፡ለዚህም ነው አንድ ታንክ ራሱ ብዙ ነው የሚባለው፡፡
በተለይ ለድሃ አገራት የታንክ መማረክ ውድ ዋጋን የሚያስከፍል ነው፡፡
በወታደራዊ ቁሳቁሶች ምርት ገናናዋ ሩሲያ ራሱ በድምሩ 3ሺህ የጦር ታንኮች እንዳሏት ይገመታል፡፡
ታዲያ ለ2 ወር በዘለቀ ጦርነት ብቻ ከ600 በላይ ታንኮች ወድመውባታል፡፡ ይህ ቁጥር ለማንም አስደንጋጭ ነው፡፡
ኦሪይክ የሚባል የወታደርና ደኅንነት አጥኚ ተቋም በ2 ወራት የወደሙት የሩሲያ ታንኮች 460 ሲሆኑ ቀሪዎቹ 2 ሺህ የሚሆኑት ብረት ለበስ ተሸከርካሪዎ ናቸው ሲል አዲስ መረጃ አውጥቷል፡፡
አሁንም ጥያቄው ሩሲያ እንዴት ይህን ሁሉ ታንክ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ አጣች የሚለው ነው፡፡
ጃቨሊን- ኢላማውን የማይስተው አሜሪካ ጸረ ታንክ
አሜሪካ ለዩክሬን ገንዘብም መሣሪያም ሞራልም እያስታጠቀች ነው፡፡
ከአሜሪካ ለዩክሬን ከተሰጡ ስጦታዎች ሁሉ ውዱ ስጦታ ጃቨሊንን ይባላል፡፡
ጃቨሊን አስገራሚ ጸረ ታንክ ሚሳኤል ነው፡፡ ይህ መሣሪያ አስገራሚነቱ በጣም ቀላል መሆኑ ነው፡፡
አንድ ማንኛውም ወታደር ከትከሻው ሊተኩሰው ይችላል፡፡ ከአንድ ፎቅ ላይ ሆኖ ሊተኩሰው ይችላል፡፡ ከመኝታ ቤት መስኮት ሊተኮስ ይችላል፡፡ ከምሽግ ተኩኖም ሊተኮስ ይችላል፡፡
በተንቀሳቃሽ የወታደር ካሚዮን ላይ ሆነው ሊተኩሱትም ይችላሉ፡፡ እንቅስቃሴ ላይ ሆኖ መተኮስ መቻሉ ሌላው አቅሙ ነው፡፡
ከተኮሱት በኋላ ታዲያ ቶሎ ቦታ መቀየር ይቻላል፡፡ ይህም ለጠላት ሌላ ራስ ምታት ነው፡፡
ጃቨሊን ግን ኢላማውን አይስትም፡፡
የሚደንቀው ደግሞ ኢላማ ባደረገው የብረት ተሸከርካሪ ላይ የሚያርፈው መጀመርያ ወደ ሰማይ አቅጣጫ ከሄደ በኋላ ታንኩ የሚገኝበት ቦታ ሲደርስ ግን ቁልቁል እንደ ጆፌ አሞራ በመምዘግዘግ ነው፡፡
ስለዚህ ጃቨሊን ታንኩን የሚመታው ሁልጊዜም ከላይ ወደታች እንጂ ከጎን አይደለም፡፡ ከታንኩ ክፍል ሳሳ ያለውን የብረት ዘንግ መርጦ መምታት ይችላል፡፡
ብዙዎቹ የሩሲያ ታንኮች ጸረ ሚሳኤል ተከላካይ ልባስ ቢኖራቸውም ይህን ጃቨሊን ግን ሊያቆሙት አልቻሉም፡፡ በ4ሺህ ሜትር ራዲየስ የሚወነጨፍ ነው፡፡
ምክንያቱም ጃቨሊን አናቱ ላይ ሁለት አረሮች አሉት፡፡ አንዱ ጸረ ሚሳኤል የሆነውን የታንኩን ክፍል ከጥቅም ውጭ ያደርጋል፡፡ ሌላኛው በቅጽበት ታንኩን ብትንትኑን ያወጣዋል፡፡
ከዚህ አሜሪካ ሰራሽ ጃቫሊን ሌላ ዩኬ ለዩክሬን 3ሺህ 600 የሚሆኑ ኤንኤልኤደብሊው (NLAW) ሚሳኤሎችን ሰጥታለች፡፡
እነዚህ ጸረ ታንክ ሚሳኤሎችም ለሩሲያ ታንኮች መውደም ትልቅ ሚናን ተጫውተዋል እየተባለ ነው፡፡
በሦስተኛነት የሚጠቀሱት ‹ካሚካዚ› የሚል ቅጽል ስም የተሰጣቸው የአሜሪካ ጸረ ታንኮች ናቸው፡፡ እነዚህን ውድ መሣሪያዎች አሜሪካ ለዩክሬን ሰጥታለች፡፡ በቁጥር መቶ ይሆናሉ፡፡
በብዙ ሺህ ሜትር ርቀት ሆነው ሲወነጨፉ ከሰማይ ሆነው ታንክ ላይ ቁልቁል በመውደቅ ታንክን ከአፈር የሚደባልቁ ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሩሲያ ወታደሮች ሞራል መውደቅ
ኦሪክስ የወታደራዊ ደኅንነት አጥኚ ተቋም እንደሚለው ከላይ ከተዘረዘሩት ጸረ ታንክ ሚሳኤሎች ውጭ ለበርካታ የሩሲያ ታንኮች መውደቅ ሌላው ምክንያት የሩሲያ ወታደሮች የውጊያ ሞራል መሳሳት ነው፡፡
ለዚህም እንደማሳያ ያቀረበው በዩክሬን ወታደሮች እጅ ከገቡት የሩሲያ ታንኮች ከግማሽ በላይ የሚሆኑት አንድም ጉዳት ያልደረሰባቸው መሆናቸው ነው፡፡
በሌላ አነጋገር የሩሲያ ወታደሮች ጥለዋቸው ሸሽተዋል፡፡
አንዳንዶቹ ደግሞ ድልድይ ለመሻገር ሲሞክሩ ፍግም ብለው የወደቁ ናቸው፡፡ የመንገድ ትቦ ውስጥ ተቀርቅረው የቀሩም አሉ፡፡
ይህም የሆነው በአዲስ ምልምል ወታደሮች ይዘወሩ ስለነበረ ነው የሚል ግምት አሳድሯል፡፡
አንዳንዶቹ ደግሞ በቂ ነዳጅ ባለመያዛቸው ነው፡፡ በሩሲያ በኩል የሎጂስቲክ አቅርቦት የተቀናጀ እንዳልነበረ በርካታ የወታደራዊ ሳይንስ ጠበብቶች የተስማሙበት ጉዳይ ነው፡፡
ሩሲያ በዚህ አጭር ጊዜ ከ6 በላይ ጄኔራሎችና በሺህ የሚቆጠሩ ወታደሮች ተገድለውባታል ይላሉ ተንታኞች፡፡
አሁን ፑቲን በ2 ወራት የገጠማቸውን ያልተጠበቀ መከላከልና ሽንፈት በምሥራቁ እንዳይደገም አዲስ ጄኔራል ሾመዋል፡፡ ጄኔራል አሌክሳደር ድሩኒኮቭ፡፡
እኒህ ጄኔራል ባሻር አልአሳድን የታደጉ ናቸው፤ ሶሪያን ከተቀናቃኞቻቸው ያጸዱ ናቸው፡፡ አሌፖን ያፈረሱ ናቸው፡፡ ርህራሄ የሌላቸው ናቸው ይባላል፡፡
ከትናንት ጀምሮ የሩሲያ ወታደሮች ዶንባስ አካባቢ እየሰፈሩ ነው፡፡
በቀጣይ ቀናትና ሳምንታት ሊከሰት የሚችለው ነገር እጅግ ከወዲሁ ዓለምን አስጨንቋል፡፡












