ሩሲያ እና ዩክሬን፡ ሌላ የሩሲያ ጄነራል ዩክሬን ውስጥ ተገደሉ፣ የጄነራሎች ኢላማ መሆን እያነጋገረ ነው

ያኮቭ ሬዛንትሴቭ

የፎቶው ባለመብት, Denis NASik/WikimediaCommons

የምስሉ መግለጫ, ያኮቭ ሬዛንትሴቭ

የዩክሬን መከላከያ ሚኒስቴር በአገሪቱ ደቡባዊ ከተማ ኬርሶን ውስጥ በተፈጸመ ጥቃት ያኮቭ ሬዛንትሴቭ የተባሉት የሩሲያ ጄነራል መገደላቸውን አስታወቀ።

ጄነራል ሬዛንትሴቭ የሩሲያ 49ኛው ጥምር ሠራዊት አዛዥ እንደነበሩ ተነግሯል።

አንድ ምዕራባዊ ባለሥልጣን እንዳሉት የጄነራሉ መሞት ዩክሬን ውስጥ የተገደሉ የሩሲያ ጄነራሎች ቁጥርን ወደ ሰባት ያደርሰዋል። የጄነራል ሬዛንትሴቭ መገደል በሩሲያ ሠራዊት ውስጥ በከፍተኛ ቦታ ላይ ከሚገኙ ጄነራሎች ሁለተኛው ያደርጋቸዋል።

በሩሲያ ሠራዊት ውስጥ ያለው ዝቅተኛ የመዋጋት ፍላጎት ከፍተኛ መኮንኖች ወደ ጦር ግንባር ቀርበው ጦሩን እንዲመሩ እንዳስገደዳቸው ይነገራል።

የዩክሬን መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ጄነራሉ የተገደሉት የሩሲያ ጦር እንደ ማዘዣ ማዕከል በሚጠቀምበት ኬርሶን አቅራቢያ በሚገኘው ቾርኖባይቫካ የአየር ኃይል ሠፈር ላይ በዩክሬን ሠራዊት በተፈጸመ ተደጋጋሚ ጥቃት ነው።

አንድሬ ሞርድቪቼቭ የተባሉት ሌላ ጄነራልም በተመሳሳይ ስፍራ ላይ በተፈጸመ ጥቃት መገደላቸው ተዘግቧል።

ምንም እንኳን በየዕለቱ የሩሲያን ወረራ በመቃወም ተቃውሞዎች በከተማዋ ቢካሄዱም፣ ኬርሶን በሩሲያ ኃይሎች ቁጥጥር ስር የገባች የመጀመሪያዋ የዩክሬን ከተማ ናት።

ሩሲያ አስካሁን በጦርነቱ አንድ ብቻ ጄነራል እንደተገደሉባት ብታረጋግጥም፣ የዩክሬንና የምዕራብ አገራት ባለሥልጣናት ግን ከጦርነቱ መጀመር በኋላ አስከ ሰባት የሚደርሱ ጄነራሎች ተገድለውባታል ብለው ያምናሉ።

የቼቺኒያ ብሔራዊ ዘብ አዛዥ የሆኑት የሜጀር ጄነራልማጎሜድ ቱሻዬቭ መገደል ግን የተረጋገጠ አይደለም።

ምክንያቱም እንዲህ ያሉት ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ወደ ጦር ግንባሮች የሚቀርቡበት ሁኔታ ብዙም የተለመደ አይደለም። ነገር ግን ምዕራባውያን ባለሥልጣናት በሩሲያ ጦር ውስጥ ያለው ዝቅተኛ ሞራል ጄነራሎቹ ግንባር ድረስ እንዲዘልቁ ሳያስገድዳቸው እንዳልቀረ ይናገራሉ።

በተጨማሪም የሩሲያ ኃይሎች የሞባይል ስልክና በቀላሉ ሊጠለፉ የሚችሉ የመገናኛ ሬዲዮዎችን ለግንኙነት ስለሚጠቀሙ፣ የዩክሬን ኃይሎች ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ያሉበትን ቦታ በበቀላሉ በመለየት ጥቃት እንዲፈጽሙባቸው አጋልጧቸው ሊሆን ይችላል ተብሎ ይታመናል።

አንድ ለዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ቅርብ የሆነ ግለሰብ ለዎል ስትሪት ጆርናል እንደታናገረው ደግሞ፣ ዩክሬን የሩሲያ ጦር መኮንኖችን በተለየ ሁኔታ ኢላማ ያደረገ የወታደራዊ ደኅንነት ቡድን አላት።

አስካሁን ድረስ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ ባደረጉት ንግግር አንድ ጄነራል ብቻ እንደተገደለባቸው የጠቆሙ ሲሆን፣ ይህም ሜጀር ጄነራል አንድሬይ ሱክሆቬትስካይን ሊሆን እንደሚችል ይታሰባል።

ሩሲያ ዩክሬን ውስጥ ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ ጀምሮ 1,351 ወታደሮቿ እንደሞቱባት ያመነች ሲሆን፣ የዩክሬንና የምዕራብ ባለሥልጣናት ግን ቁጥሩ ከተጠቀሰው በእጅጉ የበለጠ ነው ይላሉ።

ሌተናንት ጄነራል ያኮቭ ሬዛንትሴቭ
የምስሉ መግለጫ, ሌተናንት ጄነራል ያኮቭ ሬዛንትሴቭ

ሌተናንት ጄነራል ያኮቭ ሬዛንትሴቭ

ሌተናንት ጄነራል ያኮቭ ሬዛንትሴቭ ከኬርሶን ከተማ አቅራቢያ ቾርኖባይቫካ የአየር ኃይል ሠፈር ላይ በዩክሬን ኃይሎች በተፈጸመ ጥቃት መገደላቸው ተነግሯል።

ያኮቭ ሬዛንትሴቭ ወደ ሌተናንት ጄነራልነት ያደጉት ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ሲሆን፣ የሩሲያ ደቡባዊ ወታደራዊ ክፍል የ49ኛው ጥምር ሠራዊት አዛዥ ነበሩ።

ጄነራሉ ሩሲያ ሶሪያ ውስጥ ባካሄደችው ወታደራዊ ዘመቻ ውስጥ ተሳታፊ እንደነበሩ ይነገራል።

ሌተናንት ጄነራል አንድሬ ሞርድቪቼቭ
የምስሉ መግለጫ, ሌተናንት ጄነራል አንድሬ ሞርድቪቼቭ

ሌተናንት ጄነራል አንድሬ ሞርድቪቼቭ

የዩክሬን ባለሥልጣናት እንደሚሉት ሌተናንት ጄነራል አንድሬ ሞርድቪቼቭ ከሌተናንት ጄነራል ያኮቭ ጋር ኬርሶን ከተማ አቅራቢያ ቾርኖባይቫካ የአየር ኃይል ሠፈር በተፈጸመ ጥቃት ነው የተገደሉት።

አንድሬ በሩሲያ ደቡባዊ ወታደራዊ ክፍል የ8ኛው ጥምር ሠራዊት አዛዥ ነበሩ።

ሜጀር ጄነራል ኦሌግ ሚቲዬቭ
የምስሉ መግለጫ, ሜጀር ጄነራል ኦሌግ ሚቲዬቭ

ሜጀር ጄነራል ኦሌግ ሚቲዬቭ

ሜጀር ጄነራል ኦሌግ ሚቲዬቭ በዩክሬን ውስጥ ጦርነቱ ከተጀመረ አንስቶ ከባድ ውጊያ ተካሂዶባታል በምትባለው ደቡብ ምሥራቅ በምትገኘው የማሪዩፑል ከተማ አቅራቢያ እንደተገደሉ ተዘግቧል።

'አዞቭ' የተባለው የዩክሬን ብሔረተኛ ቡድን ጄነራሉን እንደገደለ ይናገራል።

ጄነራሉ ከስድስት ዓመት በፊት የተቋቋመውና በአንጻናዊነት አዲስ እንደሆነ የሚነገርለት የሩሲያ ጦር 150ኛ ሞተራይዝድ የከባድ መሳሪያ ክፍለ ጦር አዛዥ ነበሩ። ሠራዊቱ መነሻውን ከዩክሬን ድንበር አቅራቢያ ከሚገኘው የሮስቶቭ ክልል ያደረገ ነው።

ዩክሬን ይህ ጦር በምሥራቃዊ ክፍሏ ውስጥ በተገንጣዮች ቁጥጥር ስር በሚገኘው አካባቢ እንዲዋጋ የተመሰረተ መሆኑን ብትገልጽም፣ ሩሲያ ግን ጦሯ በዚያ አካባቢ ምንም አይነት ተሳትፎ እንደሌለው ታስተባብላለች።

ሜጀር ጄነራል አንድሬ ኮሌስኒኮቭ
የምስሉ መግለጫ, ሜጀር ጄነራል አንድሬ ኮሌስኒኮቭ

ሜጀር ጄነራል አንድሬ ኮሌስኒኮቭ

የዩክሬን መንግሥት ምንጮች እንደሚሉት የ29ኛው ጥምር ጦር አዛዥ የሆኑት ሜጀር ጄነራል አንድሬ ኮሌስኒኮቭ የተገደሉት በመጋቢት ውስጥ በተካሄደ ውጊያ ነው።

ጄነራሉ ስለተገደሉበት ሁኔታ የሚገልጽ ዝርዝር መረጃ አልወጣም።

ሜጀር ጄነራል ቪታሊ ጌራሲሞቭ
የምስሉ መግለጫ, ሜጀር ጄነራል ቪታሊ ጌራሲሞቭ

ሜጀር ጄነራል ቪታሊ ጌራሲሞቭ

የዩክሬን የመከላከያ ሚኒስቴር እንደሚለው የሩሲያ 41ኛው ጥምር ሠራዊት ጠቅላይ አዛዥ የሆኑት ሜጀር ጄነራል ቪታሊ ጌራሲሞቭ የተገደሉት ከምሥራቃዊቷ ካርኪቭ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኝ ስፍራ በመጋቢት ወር የመጀመሪያ ሳምንት ነው።

ለሩሲያ ድንበር በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኘው ካርኪቭ ከሩሲያ ኃይሎች ተከታታይ ከባድ ጥቃት ደርሶባታል።

የዩክሬን ጦር ኃይል ይፋ ባደረገው የተጠለፈ የድምጽ ቅጂ ላይ፣ ሁለት የሩሲያ የደኅንነት ባለሥልጣናት ስለጄነራሉ መሞትና ዩክሬን ውስጥ ያላቸው የመረጃ መለዋወጫ መስመር አስተማማኝ ስላለመሆኑ ሲናገሩ ተደምጠዋል።

ጄነራል ጌራሲሞቭ በሁለተኛው የቼቺኒያ ጦርነት፣ ሶሪያ ውስጥ ሩሲያ ባካሄደችው ወታደራዊ ዘመቻ እና ሩሲያ ክራይሚያን ወርራ ስትይዝ በተካሄዱ ዘመቻዎች ውስጥ ተሳትፈዋል።

ሜጀር ጄነራል አንድሬይ ሱክሆቬትስካይ
የምስሉ መግለጫ, ሜጀር ጄነራል አንድሬይ ሱክሆቬትስካይ

ሜጀር ጄነራል አንድሬይ ሱክሆቬትስካይ

ሜጀር ጄነራል አንድሬይ ሱክሆቬትስካይ የሜጀር ጄነራል ቪታሊ ጌራሲሞቭ ምክትል በመሆን የሩሲያ 41ኛው ጥምር ሠራዊት ከፍተኛ መኮንን ነበሩ።

ጄነራሉ በመጋቢት ወር የመጀመሪያ ቀናት ውስጥ በአንዱ ቀን በአነጣጥሮ ተኳሽ መገደላቸው ተዘግቧል።

እንደ ጄነራል ቪታሊ ጌራሲሞቭ፣ አንድሬይ ሱክሆቬትስካይ ሩሲያ ሶሪያና ክራይሚያ ውስጥ ባካሄደቻቸው ወታደራዊ ዘመቻዎች ውስጥ ተሳታፊ የነበሩ የጦር መኮንን ናቸው።

ዩክሬን ውስጥ ተገድለዋል ከሚባሉት ከሌሎቹ ከፍተኛ የሩሲያ የጦር መኮንኖች በተለየ የሜጀር ጄነራል አንድሬይ ሱክሆቬትስካይ ሞት በአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ተዘግቧል።

በተጨማሪም የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ባደረጉት ንግግር ላይ ጄነራሉ ዩክሬን ውስጥ መሞታቸውን አረጋግጠዋል።

line

ሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ዙሪያ ሊያነቧቸው የሚገቡ ዘገባዎች፡

line
የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, ከፍተኛ መጠን ያለው የኒውክሌር ጦር መሳሪያ በማን እጅ ነው ያለው?