ሮማን አብራሞቪች ቼልሲን ለመሸጥ ወሰኑ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቼልሲው ባለቤት ሮማን አብራሞቪች ክለቡን ለመሸጥ ማቀዳቸውን ገለጹ።
ባለሃብቱ አብራሞቪች በፕሪሚየር ሊጉ ክለብ ድረ-ገጽ ላይ ባወጡት መግለጫ "በጣም ከባዱን እና የሚያመውን ውሳኔ" መወሰናቸውን ተናግረዋል።
ሩሲያዊው "ምንም ዓይነት ብድር እንዲመለስ" ያልጠየቁ ሲሆን የሽያጩ ገቢም ለጦርነት ተጎጂዎች ይውላል ብለዋል።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ ከፈጸመችው ወረራ በኋላ አብራሞቪች ቅዳሜ ዕለት እንዳስታወቁት የቼልሲን "ኃላፊነት እና ተጠሪነት" ለፋውንዴሽኑ እንደሚሰጡ ተናግረው ነበር።
ይህም ክለቡን ከ 1.5 ቢሊየን ፓውንድ በላይ ብድር ውስጥ የዘፈቁት አብራሞቪች ቼልሲን ለሽያጭ ያቀርባሉ የሚል ግምት ፈጠረ።
ይህንን ተከትሎም ቢሊየነሩ ሃንስ ጆርጅ ዊስ ክለቡን የመግዛት ዕድል እንደቀረበላቸው ረቡዕ ዕለት ለስዊዘርላንዱ ብሊክ ጋዜጣ ተናግረዋል።
ዊስ እንዳስታወቁት አብራሞቪች በፓርላማው የማዕቀብ ስጋት "ቼልሲን በፍጥነት ለመሸጥ" እንደፈለጉ ተናግረዋል።
የ55 ዓመቱ አብራሞቪች ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸው ቢነገርም እሳቸው ግን አስተባብለዋል።
"ከሽያጩ የሚገኘው የተጣራ ገንዘብ በሙሉ ለዩክሬን ጦርነት ተገጎጂዎች" እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
ቼልሲን ለመግዛት ለአብራሞቪች ጥያቄ እንደቀረበላቸው ቢቢሲ ስፖርት የተረዳ ሲሆን ክለቡም እስከ ሦስት ቢሊዮን ፓውንድ ይገመታል።
አብራሞቪች በመግለጫቸው "ሁሌም ውሳኔዎችን የምወስነው የክለቡን ፍላጎት ከግምት በማስገባት ነው" ብለዋል።
"አሁን ባለው ሁኔታ ለክለቡ፣ ለደጋፊው፣ ለሠራተኞቹ እንዲሁም ለክለቡ ስፖንሰሮች እና አጋር አካላት ይጠቅማል ብዬ ስለማምን ክለቡን ለመሸጥ ወስኛለሁ።" በማለት ገልጸዋል።
"የክለቡ ሽያጭ ፈጣን ሳይሆን ተገቢውን ሂደት የሚከተል ነው። ምንም ዓይነት ብድር እንዲከፈልም አልጠይቅም።"
"ከሽያጩ የተገኘው ገንዘብ በሙሉ የሚለግስበት የበጎ አድራጎት ድርጅት እንዲያቋቁም ለቡድኔ መመሪያ ሰጥቻለሁ። ፋውንዴሽኑ በዩክሬን በጦርነት ተጎጂ ለሆኑ ጥቅም ላይ ይውላል።"
ቢቢሲ ስፖርት እንደተረዳው ከሆነ የቼልሲ ፋውንዴሽን ክለቡን ለመቆጣጠር እስካሁን አልተስማማም። አብራሞቪች ቅዳሜ ዕለት ባወጡት መግለጫ ሩሲያ በዩክሬን ላይ የፈፀመችውን ወረራ ባለመጥቀሳቸው ተወቅሰዋል።
የቡድኑ ተጫዋቾች ዜናው ቀደም ብሎ እንዲደርሳቸው አልተደረገም ተብሏል። ተጫዋቾች ዜናውን የሰሙት ከሉተን ታውን ከሚያደርጉት የአምስተኛው ዙር የኤፍኤ ካፕ ጨዋታ ጥቂት ደቂቃዎች ቀደም ብሎ ነው።
በጨዋታው ቡድኑ ከመመራት ተነስቶ 3 ለ 2 በማሸነፍ ወደ ሩብ ፍጻሜው ተቀላቅሏል።
አብራሞቪች ቼልሲን እአአ በ2003 በ140 ሚሊዮን ፓውንድ መግዛታቸው ይታወሳል። ባለሃብቱ በመግለጫቸው ግዢው "ለንግድም ሆነ ለገንዘብ ሲባል የተደረገ አልነበረም። ለስፖርቱ እና ለክለቡ ንጹህ ፍቅር ሲባል የተደረገ ነው" ብለዋል።
አብራሞቪች በክለቡ ውጤታማ ነበሩ?
ክለቡን ከገዙበት ጊዜ ጀምሮ ቼልሲ ከመለወጥ ባለፈ በፕሪሚየር ሊጉ በትልቅ ደረጃ ለመወዳደር ገንዘብ ምን ያህል እንደሚያስፈልግ ምሳሌ ሆኗል።
አብራሞቪች ለክለቡ ከ 1.5 ቢሊዮን ፓውንድ በላይ ብድር የወሰዱ ሲሆን ይህም ትልቅ ስኬት አስመዝግቧል።
በእርሳቸው የባለቤትነት ክለቡ የሚቻለውን ሁሉ ትልልቅ ዋንጫ ማንሳት ችሏል። የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግን ሁለት ጊዜ፣ ፕሪሚየር ሊግ እና ኤፍኤ ካፕ አምስት አምስት ጊዜ፣ ዩሮፓ ሊግ ሁለት ጊዜ እና የሊግ ዋንጫን ሦስት ጊዜ ማንሳት ችሏል።
ባለፈው ነሐሴ የዩኤፋ ሱፐር ካፕን ያሸነፉ ሲሆን በየካቲት ደግሞ የመጀመሪያውን የዓለም የክለቦች ዋንጫን አንስተዋል።
13 የተለያዩ አሰልጣኞችን የሾመ ሲሆን ክለቡ በዝውውር ገበያው ሁለት ቢሊዮን ፓውንድ በላይ ወጪ አድርጓል።
የቼልሲ ሴቶች ቡድንም በአብራሞቪች ስር ውጤማ መሆን ችሏል። የሴቶችን ሱፐር ሊግ አራት ጊዜ ሲያነሳ የሴቶችን ኤፍ ኤ ካፕ ሦስት ጊዜ ማሸነፍ ችሏል። ባለለፈው ዓመትም ለሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ ደርሷል።
የክለቡ ስም በመግነኑ እንደ አውስትራሊያዊቷ ሳም ኬር እና ዴንማርካዊው አጥቂ ፔርኒል ሃርደር ያሉ የዓለም ኮከቦች ወደ ክለቡ ሊዘዋወሩ ችለዋል።
አብራሞቪች ለምን መሸጥ መረጡ?
ሌሎች የሩሲያ ቢሊየነሮች ንብረታቸው ከመታገድ ባለፈ የአውሮፓ ህብረት ማዕቀብ ዒላማ ሆነዋል።
ይህ ደግሞ ከኤቨርተን ጋር ግንኙነት ያላቸውን ሩሲያዊው ቢሊየነር አሊሸር ኡስማኖቭንም ያጠቃልላል።
የዩናይትድ ኪንግደም መንግስት በአብራሞቪች ወይም በኡስማኖቭ ላይ እስካሁን እገዳ አልጣለም። የሌበር ፓርቲ ተወካይ የሆኑት ክሪስ ብራያንት ማክሰኞ ዕለት ለህዝብ እንደራሴዎች አራርሞቪች "ማዕቀብ በጣም በመፍራቱ ቤቱን ነገ ሊሸጥ ነው። ሌላውም የመኖሪያ አፓርታማው ይቀጥላል" ብለዋል።
ረቡዕ ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ጥያቄዎችን ባስተናገዱበት ወቅት የሌበር ፓርቲ መሪው ኬይር ስታርመር አብራሞቪች ለምን ማዕቀብ እንዳልተጣለባቸው ጠይቀው ነበር።
"አሁን ባለው ደረጃ በማንኛውም ግለሰብ ጉዳዮች ላይ አስተያየት መስጠት ተገቢ አይደለም" ሲሉ ጆንሰን ምላሽ ሰጥተዋል።
የሩሲያዊው ቃል አቀባይ ግን የሌበር ፓርቲ መሪውን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ አብራሞቪች ምንም ማእቀብ የሚያስጥል ነገር አላደረጉም ብለዋል።
ዊስ አክለውም "አብራሞቪች በእንግሊዝ ያሏቸውን ቪላዎቻቸውን በሙሉ ለመሸጥ እየሞከሩ ነው። ቼልሲንም በፍጥነት መሸት ይፈልጋሉ" ብለዋል።
"እኔ እና ሌሎች ሶስት ሰዎች ቼልሲን ከአብራሞቪች ለመግዛት ማክሰኞ ቀርቦልን ነበር።"
የአብራሞቪች ቃል አቀባይ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም።












