4ኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ አረፉ

ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ

የፎቶው ባለመብት, EOTC

የምስሉ መግለጫ, ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ

አራተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።

ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ባጋጠማቸው የጤና እክል ምክንያት በሆስፒታል ተኝተው የሕምና ድጋፍ ሲደርጋላቸው ነበር።

በ1980 ዓ.ም. 4ኛ ፓትርያርክ ሆነው የተሾሙት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ፤ በገጠማቸው ፖለቲካው ጫና መንበራቸውን ለቀው ከአገር ወጥተው በመሰደድ በአሜሪካን አገር ለበርካታ ዓመታትን ቆይተዋል።

የፓትርያርኩ ሕልፈተ ሕይወት ከተሰማ በኋላ በርካቶች ሐዘናቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ፓትርያርኩ "ማረፋቸውን በመስማቴ ጥልቅ ኀዘን ተሰምቶኛል" ብለዋል።

"ተለያይተው የነበሩት ሁለቱ ሲኖዶሶች አንድ እንዲሆኑ ቅዱስነታቸው ወሳኙን ሚና መጫወታቸውን አስታውሳለሁ። ነገሮችን በአርምሞ እየተመለከቱ አገራችንን በፀሎት ያግዙ ነበር። በዚህ ወቅት እርሳቸውን ማጣት ከባድ ጉዳት ነው። ለሁላችንም መጽናናትን እመኛለሁ" ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ የሆኑት ወ/ሮ አዳነች አቤቤም በፓትሪያርኩ ዜና እረፍት የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን በእራሳቸውና በከተማዋ መስተዳደር ስም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ አራተኛው የቤተ ክርስቲያኒቱ ፓትርያርክ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ሥርዓተ ቀብር መጋቢት 4/2014 ዓ.ም በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንደሚፈጸም አሳውቋል::

ብፁዕ ወ ቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ 4ኛ ፓትርያርክ ኾነው የተሾሙት ነሐሴ 29/1980 ዓ.ም. ሲሆን ኢትዮጵያ ውስጥ በመንበራቸው ላይ የቆዩት ለሦስት ዓመታት ብቻ ነበር።

ወታደራዊው መንግሥት ወድቆ ኢህአዴግ አገሪቱን ከተቆጣጠረ ከጥቂት ወራት በኋላ ከአዲሱ መንግሥት አጋጠማቸው በተባለ ፖለቲካዊ ጫና መንበራቸውን ለቀው ነሐሴ 28/1983 ዓ.ም. ከአገር ወጥተው መሰደዳቸው ይታወቃል።

አቡነ መርቆሪዎስ ለ26 ዓመታት አሜሪካ ውስጥ የቆዩ ሲሆን እዚያ የነበረውን የቤተክርስቲያኒቱን ሲኖዶስ ሲመሩ ቆይተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ባደረጉት የዕርቅ ጥረት ሐምሌ 25/2010 ዓ.ም. ወደ አገራቸው መመለሳቸው ይታወሳል።