ሶስት ሺህ የኒውዮርክ ሰራተኞች በክትባት ህግ ምክንያት ስራቸውን ሊያጡ ነው

አንከተብም የሚሉ ሰራተኞች

የፎቶው ባለመብት, EPA

ወደ ሶስት ሺህ የሚጠጉ መምህራን፣ የእሳት አደጋ ተከላካዮች እና ሌሎች የኒውዮርክ ከተማ ሰራተኞች በከተማይቱ እንዲከተቡ እስከተቀመጠላቸው ቀነ ገደብ መከተብ ባለመከተባቸው ምክንያት ስራቸውን እንደሚያጡ ተገልጿል።

አጠቃላይ ሰራተኞቹ እንዲከተቡ የተቀመጠው ቀነ ገደብ በያዝነው ሳምንት አርብ ተጠናቋል።

ከ3 ሺህ በላይ የሚሆኑት ያልተከተቡት ሰራተኞች መመሪያው ተግባራዊ ከሆነበት ሰኔ ወር ጀምሮ ያለ ክፍያ እረፍት እንዲወጡ ተደርገዋል።

ከዚህም በተጨማሪ 1 ሺህ የሚጠጉ ሌሎች ሰራተኞች ደግሞ መመሪያውን ተከትሎ እንከተባለን በማለት ቃል የገቡ ሲሆን የክትባት ማረጋገጫ ሰርቲፊኬት ካላመጡ ግን ስራቸውን እንደሚያጡ ተነግሯል።

የኒውዮርክ ከተማ ከንቲባ ኤሪክ አዳምስ ህጎቹን አልቀይርም ብለዋል። ከሳቸው በፊት የነበሩት ከንቲባ ፖሊሲውን ባለፈው አመት ባወጁበት ወቅት በከተማይቱ ለቀናት የቀጠለ ህዝባዊ ተቃውሞ አጋጥሟት ነበር።

በከተማይቱ የሚገኙ 95 በመቶ ሰራተኞች ህጎቹን ተግባራዊ አድርገው ተከትበዋል ተብሏል።

የክትባቱ ተቃዋሚዎች በበኩላቸው እነዚህ መስፈርቶች ነፃነታችንን ይፃረራሉ ይላሉ።

ይህንንም ተከትሎ አርብ እለት ተጨማሪ የተቃውሞ ሰልፎች የተደረጉ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ ወደ ክስ መሄዳቸው ተነግሯል። ለዚህም እንደ ማጣቀሻ ያያዙት የክትባት ህጎቹ ከሃይማኖት ጥበቃ በተቃራኒ ይሄዳል፣ ነጻነትን ይጥሳል የሚል ነው።

የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባለፈው ወር አስገዳጅ የክትባት ሃገር አቀፍ ፖሊሲ ወይም ለትልልቅ ኩባንያ ሰራተኞች ሳምንታዊ ምርመራዎችን የሚጠይቀውም ብሄራዊ ፖሊሲ ቢሽርም በተለያዩ ከተሞችና ግዛቶች ላይ ግን ተመሳሳይ አቋም ለመውሰድ ፈቃደኛ አልሆነም።

የኒውዮርክ ከተማ ከንቲባ ኤሪክ አዳምስ ሐሙስ ዕለት በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት ከተማዋ ሰራተኞቿን እያባረረች ሳይሆን ነገር ግን "ሰዎች ስራቸውን በገዛ ፈቃዳቸው እያቆሙ ነው" ብለዋል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በአሜሪካ ሲከሰት የቫይረሱ ማዕከል የሆነችው የኒውዮርክ ከተማ በህዝብ ተቋሟት ላይ የሚሰሩ ሰራተኞችን ክትባት አስገዳጅ ያደረገችው ብቸኛ ከተማ አይደለችም።

ሳን ፍራንሲስኮ፣ቦስተን እና ቺካጎ ተመሳሳይ ህጎችን ተግባራዊ ካደረጉ ከተሞች እና ግዛቶች መካከል ናቸው። ባለሙያዎች ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል አስተማማኙ መንገድ ክትባት ነው የሚለውንም እየተገበሩ ይገኛሉ።