ኢምር አብደልቃድር፡ በፈረንሳይ የአልጄሪያ የጦር ጀግና ምሥል ያለበት ቅርጽ ከመመረቁ ከሰዓታት በፊት ፈረሰ

የኢምር አብደልቃድርን ምሥል የያዘው ቅርጽ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, የአልጄሪያ የጦር ጀግና ምሥል ያለበት ቅርጽ የፈረሰው ከመመረቁ ከሰዓታት በፊት ነው

በማዕከላዊ ፈረንሳይ የቆመው የአልጄሪያ የጦር ጀግና ምሥል ያለበት ቅርጽ ከመመረቁ ከሰዓታት በፊት ፈረሰ።

አልጄሪያ ከፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ነጻ የወጣችበትን 60ኛ ዓመት ለማሰብ የቆመው ቅርጽ በአንድ ወቅት 'የፈረንሳይ ጠላት' እየተባለ በሚጠራው ኢምር አብደልቃድር በመባል የሚታወቁትን አብደልቃድር ኢብን ሙህዲን ምሥልን ያሳያል።

አብደልቃድር እአአ በ1830 ፈረንሳይ አልጄሪያን መውረሯን በመቃወም ትግሉን ከፊት ሆነው መርተዋል።

አሁን ቅርጻቸው በቆመበት የፈረንሳይዋ ከተማ አምቦሴም ለአራት ዓመታት ያህል ታስረዋል።

ቅዳሜ በሚካሄደው ሥነ ስርዓት ላይ ለመገኘት ወስነው የነበሩት የከተማ ከንቲባ "ይህንን የኪነጥበብ ሥራ በዚህ መልኩ ባፈረሱት ሰዎች አፍሬያለሁ" ብለዋል።

"ይህ ዕለት የኅብር እና የአንድነት ቀን ነው። እናም እንዲህ ዓይነት ባህርይ በቃላት የሚገለጽ አይደለም" ብለዋል ቴዮሪ ቡታርድ።

በፈረንሳይ የአልጄሪያ አምባሳደር በበኩላቸው ድርጊቱ " በቃላት ሊገለጽ የማይችል የሞራል ማጣት ነው" ብለውታል።

ቅርጹ የፈረሰው ፈረንሳይ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ለማካሄድ ዘመቻ ላይ ባለችበት ወቅት ሲሆን ለአንዳንድ ፕሬዚደንታዊ እጩዎች ስደት እና እስልምና ወሳኝ መከራከሪያዎች ናቸው።

የ37 ዓመቷ ትውልደ አልጀሪያዊቷ ፈረንሳዊት " አሁን በሰፈነው ጥላቻ እና የሚያስጠላ ሁኔታ ይህ መሆኑ ምንም የሚያስደንቅ ባይሆንም አሳፋሪ ነው" ብላለች።

የጦር መሪ ከመሆናቸው በፊት የእስልምና ምሁር የነበሩት ኢምር አብደልቃድር የፈረንሳይን አገዛዝ በመቃወም ባደረጉት አስተዋጽኦ ከአሁኗ አልጄሪያ መሥራቾች አንዱ እንደሆኑ ይታሰባሉ።

ይሁን እንጂ በ19ኛው ክፍለ ዘመን እርሳቸው ሲመሩት የነበረው አመጽ በመክሸፉ ተይዘው ወደ ፈረንሳይ ተወስደዋል።

እዚያ ከተወሰዱ በኋላም በደቡብ ምዕራብ ፓሪስ በምትገኘው አምቦሴ ከተማ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለአራት ዓመታት በእስር አሳልፈዋል።

ከዚያም ከእስር ከተለቀቁ በኋላ በሄዱበት መካከለኛው ምሥራቅ ክርስቲያኖችን ከጥቃት በመከላከል ዓለም አቀፍ እውቅናን አግኝተዋል።

አልጀሪያ የሁለቱን አገራት ግንኙነት ካወሳሰበውና ከስምንት ዓመት ደም አፋሳሽ ጦርነት በኋላ ከፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ነጻ የወጣችው እአአ በ1962 ነው።

በጦርነቱም ከ400 ሺህ እስከ 1 ሚሊየን የሚደርሱ ሰዎች እንደሞቱ ይገመታል።

አብደልቃድር ታስረውበት ከነበረው ቤተ መንግሥት በሎይር ወንዝ ማዶ የሚታየው አዲሱ ቅርጽ የተሰራው የፈረንሳዩ ፕሬዚደንት ኢማኑኤል ማክሮን በአልጄሪያ የነበረውን ጦርነት እና የፈረንሳይ አገዛዝ መጥፎ ትውስታ የሚፈወስበትን መንገድ እንዲፈልግ በተጠየቁት የታሪክ ምሁር ሃሳብ ነው።