በየመን በሁቲ አማጺያን የታገተው ኢትዮጵያዊ የመርከብ ቴክኒሻንና የቤተሰቦቹ ጭንቀት

ኢትዮጵያዊው የመርከበት ቴክኒሺያን አየናቸው መኮንን ይሰራባት የነበረችው መከርብ ታኅሣሥ 24/2014 ዓ.ም በሁቲ አማጺን ቁጥጥር ሥር ገብታለች።

የፎቶው ባለመብት, Social Media

የምስሉ መግለጫ, ኢትዮጵያዊው የመርከበት ቴክኒሺያን አየናቸው መኮንን

በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የጭነት መርከብ ላይ በቴክኒሻንነት ይሰራ የነበረው ኢትዮጵያዊው አየናቸው መኮንን ከሳምንታት በፊት በሁቲ አማጺያን ከታገተ በኋላ ያለበት ሁኔታ እንዲሁም ደኅንነቱ ቤተሰቦቹን በእጅጉ አሳስቧል።

እሁድ ታኅሣሥ 24/2014 ዓ.ም የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ሰንደቅ አላማ የሰቀለች "ራዋቢ" የተሰኘችው የደረቅ ጭነት ተሸካሚ መርከብ ከየመኗ ሶኮትራ ተነስታ ወደ ቀዳሚ መነሻዋ ሳዑዲ በመጓዝ ላይ ሳለች ነበር በሁቲ አማጺያን እጅ የገባችው።

መርከቡ ውስጥ ከነበሩት 11 ሠራተኞች መካከል አየናቸው መኮንን የተባለ ኢትዮጵያዊ እንደሚገኝበት የታወቀው ከቀናት በኋላ ለቤተሰቦቹ ስልክ መደወሉን ተከተሎ ነበር።

አየናቸው ለቤተሰቦቹ የመን ሰነአ አካባቢ እንደሚገኝ እና የሁቲ አማጺያን የሚሰራበትን መርከብ መቆጣጠራቸውን እንደተናገረ እህቱ ፍሬሕይወት መሐሪ ለቢቢሲ ትገልጻለች።

ላለፉት ሰባት ዓመታት በእርስ በእርስ ጦርነት እንዲሁም ኃያላን አገራት የበላይነት ለመያዝ በሚያደርጉት ከባድ ፍልሚያ መሃል የወደቀችው የመን፤ በሳዑዲ መራሹ ጥምር ጦር እንዲሁም በኢራን በሚደገፉት የሁቲ አማጺያን መካከል ያለው ግጭት ተባብሶ ቀጥሏል።

የሁቲ አማጺያን የጭነት መርከቧ ወታደራዊ ቁሶችን ይዛ ነበር ሲሉ፤ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በበኩሏ በመርከቧ ላይ የሕክምና መገልገያዎች እንደተጫኑ ስትገልጽ ቆይታለች።

በአካባቢው ኃያል አገር በሆነችው የነዳጅ ምርት ባለፀጋዋ ሳዑዲ አረቢያና በየመን አማጺያን መካከል ለዓመታት በቆየው ፍጥጫ ሳቢያ በተጠለፈችው መለስተኛ እቃ ጫኝ መርከብ ላይ ሲሰራ የቆየው ኢትዮጵያዊው አየነናቸው ተጎጂ ሆኗል።

አየናቸው

የፎቶው ባለመብት, family

አየናቸው መኮንን በመርከብ ቴክኒሺያንነት ሙያው ላለፉት ሰባት ዓመታት ያህል አሁን እየሰራበት ካለው ድርጅት በተጨማሪ በተለያዩ የባሕር መጓጓዣ ተቋማት ውስጥ በሙያው ተቀጥሮ ሲሰራ ቆይቷል።

አየናቸው ለሥራ ሲወጣ ለወራት ከቤተሰቡ ተለይቶ እንደሚቆይ የምትናገረው እህቱ ፍሬሕይወት፣ ምንም እንኳ ለረጅም ጊዜ ከአገር ርቆ ቢቆይም ለቤተሰቡ በተለይም ለባለቤቱ በተደጋጋሚ ስልክ እንደሚደውል ታስረዳለች።

የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መርከብ የተጠለፈች ሰሞን ከሌላው ጊዜ በተለየ ድምጹ ጠፍቶ በመቆየቱ አጠቃላይ ቤተሰቡ በእጅጉ ተጨንቆ ነበር። ከቀናት በኋላ ግን ወደ ቤተሰቦቹ ስልክ የደወለው አየናቸው በየመን የባሕር ዳርቻ አቅራቢያ መርከባቸው በሁቲ አማጺያን እጅ መግባቷንና እሱም በቁጥጥራቸው ስር መሆኑን ተናገሯል።

"ለባለቤቱ ደውሎ ሁቲ በሚባሉ ሰዎች መታገቱን ተናገረ። ከመካከላቸው ሰባቱ ሕንዳውያን መሆናቸውን እና መንግሥታቸውም እነሱን ለማስለቀቅ እና ማንነታቸውን ለማስረዳት ጥረት እያረገ እንደሆነ ነገራት" ትላለች ፍሬሕይወት።

አየናቸው ሕንዳውያኑ እንዳደረጉት ባለቤቱ ወደ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሄዳ ማንነቱን የሚያስረዳ እንዲሁም ከመርከብ ቴክኒሺያንነት ሥራው ውጪ ምንም ሚና እንደሌለው ማስረጃ እንድታመጣ ጠይቋታል።

ባለቤቱ እንደተባለቸው ወደ ውጭ ጉዳይ ብትሄድም፤ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በየመን ኤምባሲ እንደሌላት እንዲሁም የመን ውስጥ ባሉ የመንግሥት እስር ቤቶች ውስጥ አየናቸው ተፈልጎ ሊገኝ እንዳልተቻለ ተገልጾላታል።

ይህንንም ተከትሎ በአማጺያኑ ተይዞ ካለበት ስፍራ ለሁለተኛ ጊዜ ስልክ በደወለበት ወቅት ሌሎች ከእሱ ጋር ያሉት ባልደረቦቹ ከመንግሥታቸው ማንነታቸውን የሚፈገልጽ ማስረጃ ማግኘታቸውን እርሱ ግን ምንም ሰነድ እንደሌለው መናገሩን እህቱ ገልጻለች።

በተጨማሪም ለሁለተኛ ጊዜ ጥር 08/2014 ዓ.ም መልሶ ወደ ቤተሰቦቹ ባደረገው የስልክ ጥሪ ላይ ያገቷቸው ታጣቂዎች እሱንና ባልደረቦቹን ወዳለወቁት አዲስ ስፍራ እንዳዘዋወሯቸው ተናግሯል። ቦታውም ሆቴል መሆኑን አየናቸው እንደተናገረ እህቱ ፍሬሕይወት ታስታውሳለች።

ሮይተርስ የዜና ወኪል የተባበሩት መንግሥታት ሠራተኞች አየናቸው ይገኝባት የነበረችውና የተጠለፈችውን መርከብ አስ-ሳሊፍ በተሰኘው ወደብ ላይ ከርቀት መመልከታቸውን እና የመርከቧን ሠራተኞች ማነጋገራቸውን ጥር 04/2014 ዓ.ም ዘግቦ ነበር።

አየናቸው የሁለት እና የሦስት ወር ጨቅላ ልጆች አባት ሲሆን በሥራው ምክንያት ከአገር ርቆ በመቆየቱ ሁለተኛ ልጁን ከተወለደች እንዳላያት እህቱ ትናግራለች።

አየናቸው መኮንን አሁን ባለበት ሁኔታ ቤተሰቦቹ በእጅጉ ለደኅንነቱ መጨናቃቸውን በተደጋጋሚ እየገለጹ ሲሆን፣ ጉዳዩን ለተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ተቋም አሳውቀው እሱን የሚመለከቱ ማስረጃዎችን በሙሉ መስጠታቸውን ፍሬሕይወት አክላለች።

በሁቲ አማጺያን እጅ ገብታለች የተባለችው መርከብ ባለቤት እና የአየናቸው መኮንን ቀጣሪ መሆኑ በቤተሰቦቹ የተገለጸው "ካሊድ ፋራጅ" የመርከብ ጭነት አገልግሎት ሰጪ ድርጅት፣ ሠራተኞቹ ስላሉበት ሁኔታና ስለደኅንነታቸው የሚያውቀው ነገር ካለ በሚል ከቢቢሲ ለቀረበለት የኤሜይል ጥያቄ እስካሁን ምላሽ አልሰጠም።

ነገር ግን አየናቸው ለቤተሰቦቹ ስልክ በደወለበት ወቅት አሰሪ ድርጅቱ ጋር መገናኘት አለመቻሉን እና በአድራሻው ቢደውልም ሊገኝ አለመቻሉን መናገሩን እህቱ ፍሬሕይወት ተናግራለች።

ኢትዮጵያዊው አየናቸው መኮንን ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የመርከብ ድርጅት ጋር ለመሥራት የሁለት ዓመት ውል የገባ ሲሆን፣ የሚሰራባት መርከብ በየመን አማጺያን ስትታገት ሥራውን ከጀመረ ገና ስምንት ወሩ ብቻ ነበር።

ቢቢሲ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሁቲ አማጺያን በተያዘችው መርከብ ላይ ይሰራ ስለነበረው መርከበኛ አየናቸው መኮንን ያገኘው መረጃ ይኖር እንደሆነ ለማወቅ አምባሳደር ዲና ሙፍቲን በስልክ ለማነጋገር ያደረገው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።