ሳዲዮ ማኔ ከሞ ሳላህ - የአፍሪካ ዋንጫ ፍፃሜ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በካሜሩን አስተናጋጅነት ሲካሄድ የሰነበተው የ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የፍፃሜ ተፋላሚዎች ታውቀዋል። ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሴኔጋል ከሰሜን አፍሪካዊቷ ግብፅ ጋር እሑድ ምሽት 4 ሰዓት የሚያደርጉት ጨዋታ የውድድሩ መቋጫ ይሆናል።
ለፍጻሜው ጨዋታ የደረሱት ሁለቱ ቡድኖች ኢትዮጵያ ትገኝበት የነበረው ምድብ 'ሀ' ውስጥ የነበሩትን አዘጋጇን ካሜሩንና ቡርኪና ፋሶን ረተው ነው ወደ ለዋንጫ የደረሱት።
ሴኔጋል በሳዲዮ ማኔ ታግዛ ቡርኪና ፋሶን 3 ለ 1 በመርታት ለተከታታይ ሁለተኛ ጊዜ ለፍፃሜ መድረሷን አረጋግጣለች።
ግብፅ ደግሞ አዘጋጇ ካሜሩንን ከሁለት ሰዓታት ጨዋታ በኋላ በፍፁም ቅጣት ምት በመርታት ነው ለዋንጫው ጨዋታ የቀረበችው።
በሁለቱ የሊቨርፑል አጥቂዎች ሳዲዮ ማኔ እና ሞ ሳላህ የሚመሩት ሴኔጋልና ግብፅ ለአፍሪካ ዋንጫ ፍፃሜ መድረስ ብርቃቸው አይደለም።
ሰኔጋል ባለፈው የአፍሪካ ዋንጫ ከአልጄሪያ ጋር ለፍጻሜ ደርሳ 1 ለ 0 በመሸነፏ ሁለተኛ ሆና ውድድሩን ማጠናቀቋ አይዘነጋም።
ግብፅ ደግሞ በውሮፓውያኑ 2017 በተደረገው የአፍሪካ ዋንጫ ፍፃሜ በካሜሩን 2 ለ 1 በመረታቷ የአህጉሪቱ የእግር ኳስ ቁንጮ ሳትሆን ርታ ነበር።
ፈርዖኖቹ በሚል ቅጽል የሚታወቀው የግብፅ ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫን ለበርካታ ጊዜያት በማንሳት የውድድሩን ክብረ ወሰን ይዘዋል።
በአሁኑ ወቅትም የዓለም ኮከቡ እግር ኳሰኛ ሞሐመድ ሳላህ "ከምንም በላይ የአፍሪካ ዋንጫን ማንሳት እሻለሁ" ማለቱ የእሑዱን ጨዋታ ተጠባቂ አድርጎታል።
ከካሜሩን ጋር በነበረው የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ባሳዩት ያልተገባ ባሕሪይ ከሜዳ በቀይ ካርድ የተወገዱት የግብፁ አሰልጣኝ ካርሎስ ኬሮዥ ተጫዋቾቻቸው ካሳለፉት የጨዋታ ጫና እረፍት እንዲያገኙ የፍፃሜው ጨዋታ ቀን ይቀየርልን እያሉ ነው።
ነገር ግን የአፍሪካ እግርኳስ የበላይ አካል የሆነው ካፍ ግን የኬሮዥን ሐሳብ የሚሰማ አይመስልም። አስካሁንም ያለው ነገር ስለሌለ በተያዘው መረሃ ግብር መሠረት የፍጻሜው ጨዋታ እሑድ ይደረጋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎችን ለ120 ደቂቃዎች የተጫወተችው ግብፅ ከሁለት ቀናት እረፍት በኋላ ለፍፃሜው ወደ ያውንዴ ታቀናለች።
ሴኔጋል ምንም እንኳን ስመ ጥር እግር ኳስ ተጫዋቾችን ያፈራችና በበርካታ የአፍሪካ ዋንጫ ውድድሮች ላይ ተሳትፋ ሁለት ጊዜ ለፍፃሜ ብትደርስም ዋንጫውን የማንሳት ዕድል ግን ሳታገኝ ቆይታለች።
በሊቨርፑሉ የፊት መስመር ተጫዋች ሳዲዮ ማኔ የሚመሩትና 'የቴራንጋ አናብስት' ተብለው የሚታወቁት ሴኔጋላውያን ተጫዋቾች እሑድ ከግብፅ ጋር በሚኖራቸው የፍጻሜ ጨዋታን በማሸነፍ የአገራቸውን ስም በውድድሩ የአሸናፊዎች መዝገብ ላይ ለማስጻፍ ከፍ ያለ ጉጉት አላቸው።
በተጫዋችነት ዘመኑ ለአገሩ ሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን ተሰልፎ ለዓለም ዋንጫ ሩብ ፍፃሜ መድረስ የቻለው የቡድኑ አሰልጣኝ አሊዩ ሲሴ ዋንጫውን ካነሰ ከቡድኑ ጋር ስሙ በወርቅ ይፃፍለታል።
የ45 ዓመቱ አሊዩ ሲሴ ቀደም ሲል ሴኔጋል በአፍሪካ ዋንጫ ሁለት ጊዜ ለዋንጫ ደርሳ ስትረታ አንድ ጊዜ በተጫዋችነት በሌላኛው በአሠልጣኝነት ተሳትፏል።
ምንም እንኳ ሴኔጋል የአፍሪካ ዋንጫን በማሸነፍ ለማንሳት ሳትችል ብትቀርም በዓለም የብሔራዊ ቡድኖች ሰንጠረዥ ላይ የአፍሪካ አውራ ናት።
ዋንጫውን ማን ያነሳው ይሆን?
ከኢትዮጵያና ሱዳን ጋር የአፍሪካ ዋንጫን መስርታ ሰባት ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ በመሆን ክብረ ወሰን የጨበጥችው ግብፅ ወይስ ባለፈው የአፍሪካ ዋንጫ ለፍፃሜ ደርሳ ያልቀናት ሴኔጋል?
መልሱን ጊዜ ይፈታዋል። እሑድ ምሽት 4 ሰዓት።














