በአምላክ ተሰማ የዓለምን ቀልብ የገዙበት የአፍሪካ ዋንጫ ፍልሚያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኢትዮጵያዊው አርቢትር በአምላክ ተሰማ ትላንት ምሽት የስፖርቱ ዓለም መነጋገሪያ ሆነው አምሽተዋል። ለምን?
ካሜሩን እያስተናገደችው የምትገኘው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ ፍፃሜውን ቀጣይ እሑድ ሲያገኝ ሴኔጋል የዋንጫ ተፋላሚ መሆኗን አውቃለች።
ረቡዕ ምሽት ከቡርኪና ፋሶ ፍፃሜ የተጫወተችው ሴኔጋል በኮከብ አጥቂዋ ሳዲዮ ማኔ ታግዛ 3 ለ 1 በሆነ ውጤት ፍልሚያውን ረታለች።
ቢሆንም ከዚህ እልህ አስጨራሽ ጨዋታና ውጤት ትይዩ ኢትዮጵያዊው የመሃል ዳኛ በአምላክ ተሰማ መነጋገሪያ ሆነው አምሽተዋል።
በአምላክ ተሰማ በካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫ ሦስተኛ ጨዋታቸውን ረቡዕ ምሽት ዳኝተዋል።
በአምላክ ከዚህ ቀደም ሴኔጋል ከጊኒ እንዲሁም አዘጋጇ ካሜሩን ከኮሞሮስ ያደረጉትን ጨዋታ በመሃል ዳኝነት ግብፅ ከናይጄሪያ እንዲሁም ከሱዳን ያደረገችውን ጨዋታ ደግሞ በአጋዥ ተንቀሳቃሽ ምስል [ቪኤአር] ዳኝነት መርተዋል።
ነገር ግን ሴኔጋል ከቡርኪና ፋሶ ለዋንጫ ለማለፍ ያደረጉትን ፍልሚያ የመሩት 'ኢንተርናሽናል' አልቢትር የመገናኛ ብዙኃንና የማኅበራዊ ሚዲያ መነጋገሪያ ሆነዋል።
በጨዋታው ምን ተፈጠረ?
በደማቅ ፈገግታቸው የሚታወቁት በአምላክ ተሰማ ከተጫዋቾች ጋር እሰጥ አገባ መግባት የሚፈልጉ ዳኛ አይደሉም።
የማስጠንቀቂያ ቢጫ ካርድ አንዳንዴም ቀይ ካርድ ሲሰጡ በፈገግታ ታጅበው ነው። የወደቀ ተጫዋች ለማንሳት የሚቀድማቸውም የለም።
በረቡዕ ምሽቱ ጨዋታ የሰኔጋሉ ኩያቴ ከቡርኪና ፋሶው ግብ ጠባቂ ኮፊ ጋር የተጋጨበትን ክስተት የተመለከቱት በአምላክ ለሴኔጋል ፍጹም ቅጣት ምት ይሰጣሉ።
ሁለቱ ተጫዋቾች ክፉኛ በመጎዳታቸው ምክንያት ሕክምና እስኪያገኙ የጠበቁት ዳኛው ወደ ቪኤአር መስኮት በማቅናት ተሳስቻለሁ ፍጹም ቅጣት ምት አይደለም ሲሉ ይወስናሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የመጀመሪያው አጋማሽ መገባደጃ ገደማ ደግሞ የቡርኪናቤው ተከላካይ ኤድሞን ታፕሶባ ኳስ ፍጹም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ነክቷል በማለት ዳኛው ለሴኔጋል 'ሪጎሬ' ይሸልማሉ።
አልፎም ተጫዋቹ ለፈፀመው ቅጣት ማስጠንቀቂያ ቢጫ ካርድ ይሰጡታል።
ነገር ግን ውሳኔያቸውን ከማጽደቃቸው በፊት አጋዥ ተንቀሳቃሽ ምስል እንዲመለከቱ ረዳቶታቸው ይጠቁሟቸዋል።
ከሜዳው ጠርዝ ወደቆመው የቪኤአር መስኮት ያቀኑት በአምላክ ፍጹም ቅጣት ምቱን ሽረው ወደ ታፕሶባ አቅንተው ቢጫ ካርድህ ተሰርዞልሃል ብለው ይቅርታ ሲጠይቁት በቴሌቪዥን መስኮት ታይተዋል።
የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ያለምንም ግብ ቢጠናቀቅም የስፖርት ቤተሰቡ የበአምላክን ስም እያነሳ ሲያወድሳቸው ተስተውሏል።
ሁለቱም የፍጹም ቅጣት ምቶች አሳማኝ አይደሉም ያሉ በርካታ የስፖርት ወዳጆች ዳኛው ቪኤአርን በአግባቡ መጠቀማቸውን ሳያደንቁ አላለፉም።
ቁጥራቸው የበዛ አፍሪካዊያን የስፖርት ጋዜጠኞች በማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ የበአምላክን ስም እያነሱ ሲያንቆለጳጵሷቸው ታይተዋል።
በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ የትዊተር ተከታዮች ያሉት ጋናዊው እውቅ የስፖርት ጋዜጠኛ ሳዲቅ አዳምስ "ድንቅ ውሳኔ" ብሎ ሲያሞግሳቸው ኬንያዊቷ ታዋቂ የስፖርት ጋዜጠኛ ካታሚ ሚሼል ደግሞ "ሁሉም ውሳኔዎቹ አግባብ ናቸው" ስትል ለዳኛው አድናቆቷን ገልፋለች።
ደቡብ አፍሪካዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ሊሬንዝ ኮለርም ለበአምላክ አድናቆታቸውን ከቸሩ ሰዎች መካከል ነው።
ጎል ዶት ኮም የተሰኘው የእግርኳስ ድረ-ገፅ እስቲ ስለ በአምላክ ያላችሁን አስተያየን አጋሩን ብሎ በትዊተር ገፁ ከለጠፈው መልዕክት ሥር በርካታ የስፖርት ወዳጆች ለዳኛው አድናቆታቸውን ሲያጎርፉ ነበር።
አልፎም በርካታ ኢትዮጵያውያንም የዳኛውን ብቃት በማድነቅ 'ኮርተንብሃል' ሲሉ ለዳኛ በአምላክ ያላቸውን ክብር አሳይተዋል።
33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በበርካታ ክስተቶች የታጀበ፤ በዳኞች ቢጫና ቀይ ካርድ የተከበበ መሆኑን ተከትሎ በአምላክ ይህን ፈታኝ ጨዋታ በብቃት መዳኘታቸው ከበሬታ አጎናፅፏቸዋል።
ጨዋታውን ሴኔጋል በሳዲዮ ማኔ፣ በአብዱ ዲያሎና በኢድሪስ ጉዬ ጎሎች በማሸነፍ ለሁለተኛ ተከታታይ ጊዜ ለፍፃሜ ማለፏን አረጋግጣለች።
ዛሬ ሐሙስ ምሽት ደግሞ ግብፅ አዘጋጇ ካሜሩንን ትገጥማለች።














