ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች ለብሔራዊ ቡድኑ የማይጠሩት ለምንድን ነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images/Hoffenheim.de
ከዘጠኝ ዓመታት ቆይታ በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ የተመለሰው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከምድቡ ማለፍ ባለመቻሉ በጊዜ ወደ አገሩ ተመልሷል።
በወጣት ተጫዋቾች የተዋቀረው የዋሊያዎቹ ስብስብ ሁለት ከኢትዮጵያ ውጪ የሚጫወቱ ተጫዋቾችን ቢያካትትም ሁለቱም ተጫዋቾች ይህ ነው የሚባል ሚና አልነበራቸው።
ለግብፁ ክለብ ኤል ጉናን የሚጫወተው ሽመልስ በቀለ በጉዳት ምክንያት፤ ለአልጄሪያው ጄኤስ ካቢሌ የሚጫወተው ሙጂብ ቃሲም ደግሞ የአሠልጣኙ የመጀመሪያ ምርጫ ባለመሆኑ ሜዳ ላይ አልታዩም።
በአፍሪካ ዋንጫ ከተሳተፉ 24 ቡድኖች መካከል አንድም ከአፍሪካ ውጪ የሚጫወት እግር ኳሰኛ ያላካተተችው ኢትዮጵያ ብቻ ነበረች።
ለምሳሌ ወደ ዙር 16 ተሻጋግራ ከካሜሩን ጋር እህል አስጨራሽ ፍልሚያ አድርጋ የወደቀችው ኮሞሮስ የመጀመሪያ ምርጫ የሆኑ 11 ተጫዋቾች በአውሮፓ ሊጎች የሚጫወቱ ናቸው።
በሌላ በኩል ከአልጄሪያና ኮትዲቯር ጋር ተደልድላ ከምድብ ከማለፍ አልፋ ማሊን በመርታት ወደ ሩብ ፍፃሜ የተሸጋገረችው ኢኳቶሪያል ጊኒ ስፔንና ጣልያን ባሉ ሁለተኛና ሦስተኛ ዲቪዚዮን የሚጫወቱ ተጫዋቾችን ነው የያዘችው።
በሩብ ፍፃሜ ከካሜሩን ጋር የተፋለመችው የአፍሪካ ዋንጫ የመጀመሪያዋ የሆነውና በቀድሞው የዋሊያዎቹ አሠልጣኝ ቶም ሴንትፊት የምትመራው ጋምቢያም እንዲሁ ከአገር ውጪ በመጡ ተጫዋቾች የታጀበች ናት።
ለመሆኑ ዋሊያዎቹ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ተጫዋቾችን ማካተት ለምን አልቻሉም? በአውሮፓ የሚጫወት ተጫዋች ስለሌለን? ወይስ ሌላ?
'የፓስፖርት ጉዳይ'
ከምድቡ አንድ ነጥብ ይዞ ከአህጉሪቱ ትልቁ ውድድር የተሰናበተው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ወደ አገር ቤት ከተመለሱ በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ "ተሳትፏችን መልካም ነበር" ብለዋል።
በሌላ በኩል የፌዴሬሽኑ ዋና ፀሐፊ ባሕሩ ጥላሁን ደግሞ የተፈለገውን ውጤት ባለማምጣታችን "የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ እንጠይቃለን" ሲሉ ተደምጠዋል።
ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን በተመለከተ ከጋዜጠኞች ጥያቄ የቀረበላቸውን ዋና ፀሐፊው እንደዋነኛ ምክንያት የጠቀሱት የፓስፖርት ጉዳይ ነው።
"ኢትዮጵያ ጥምር ዜግነት ስለማትፈቅድ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን በቡድኑ ውስጥ ማከተት አልቻንም" ሲሉ ምላሻቸውን ሰጥተዋል።
ከዚህ ቀደም ለብሔራዊ ቡድኑ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ቡና የተጫወተው ትውልደ ጀርመናዊው ዴቪድ በሻህ ግን ይህ ምክንያት ሊሆን አይገባም ይላል።
"እርግጥ ነው ከኔም ልምድ በመነሳት የሌላ አገር ዜግነት ካለህ ለኢትዮጵያ መጫወት አትችልም። አሊያም ደግሞ የያዝከውን ዜግነት አሳልፈህ መስጠት አለብህ።"
ዴቪድ ከአፍሪካ ዋንጫ በፊት ለኢትዮጵያ ለመጫወት ፈቃደኛ የሆኑ መቀመጫቸው አውሮፓ የሆነ ዘጠኝ ተጫዋቾችን ስም ዝርዝር ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና ለአሠልጣኙ አቅርቦ ነበር።
"ጊዜው አጭር ነበር። እኔ ተጫዋቾቹን መመልመል የጀመርኩት መስከረም ወር መጨረሻ ነበረ። ነገር ግን ጥሩ አቋም ላይ ያሉ ወጣት ተጫዋቾችን ለአሠልጣኙ ባቀርብም አሠልጣኙ በተጫዋቾቹ ብቃት ደስተኛ እንዳልሆነ ነበር የነገረኝ።"
ዴቪድ ተጫዋቾቹን ለአፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት የነበረው ጊዜ እጅግ አጭር እንደነበር ቢስማማም አንዳንዶቹ ተጫዋቾች ለትላልቅ ቡድኖች የሚጫወቱና ጥሩ አቋም ያላቸው ናቸው ይላል።
"በተለይ ወደፊት በመገስገስ የሚያጠቁ ተጫዋቾችን ነበር ለብሔራዊ ቡድኑ የመለመልኩት። አንድ ኖርዌይ የሚጫወት ወጣት ግብ ጠባቂም መርጬ ነበር። ቢያንስ አሠልጣኙ ተጫዋቾቹን ጠርቶ በልምምድ ሜዳ ብቃታቸውን ቢፈትሽ መልካም ነበር። በተሰጠኝ ምላሽ ደስተኛ አይደለሁም" ይላል።
ትውልደ ጀርመናዊው ዴቪድ "ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ተሰጥዖ አውቃለሁ። እኔም ለስድስት ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ ተጫውቻለሁ" ይላል።
"ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች ያላቸውን ብቃት አሟጠው እንደሚጫወቱ አውቃለሁ። ነገር ግን ያለን መሠረተ ልማት ጠንካራ አይደለም። እነ ጋምቢያ፣ ኬፕ ቬርድ፣ ሴራ ሊዬን እንዲሁም ሌሎች ብሔራዊ ቡድኖችን ብትመለከት ውጭ የሚጫወቱ ተጫዋቾችን አካተዋል" በማለት ያሳዩትን ብቃት በዋቢነት ጠቅሷል።
ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አመለካከት "አውሮፓ የሚገኙ ተጫዋቾች እንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ አሊያም ላሊጋ ወይም ቡንደስሊጋ ካልተጫወቱ የተጫዋቾቹን ብቃት የሚፈትሹበት መንገድ የላቸውም" ይላል።
"ለምሳሌ ከመለመልኳቸው ተጫዋቾች መካከል አንዱ በጀርመን ሦስተኛው ሊግ የሚጫወት ነው። አንድም የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ቡድን ይህንን ሊግ እንደማይቋቋመው አውቃለሁ።"
አሠልጣኙ "ተጫዋቾቹን እዚህ አምጥቼ አቋማቸውን ብፈትሽ ችግር አልነበረውም ነገር ግን የፖስፖርት ጉዳይ ያግደኛል" የሚለው ዴቪድ፣ የፓስፖርት ጉዳይ አፋጣኝ ፖለቲካዊ መፍትሔ እንደሚሻ ይናገራል።
'ጉዳዩ የፓስፖርት አይደለም'
በፈረንጆቹ ከ2011 ጀምሮ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾችን ለብሔራዊ ቡድኑ በመመልመል የሚታወቁት ፋርሃን ሞሐመድ ጉዳዩ የፓስፖርት አይደለም ይላሉ።
"እመነኝ ጉዳዩ የፓስፖርት አይደለም። እንደዚያ ከሆነ ዴቪድ በሻህ አውሮፓ ሄዶ ተጫዋቾችን እንዲመለምል ለምን ላኩት? የተጫዋቾቹን ስም ዝርዝር ይዞ ሲመጣ አሠልጣኙም የሰጡት ምላሽ ብቃታቸው ጥሩ አይደለም የሚል ነው።"
ፋርሃን ችግሩ ያለው አሠልጣኞች ጋር ነው ሲሉ ይሞግታሉ።
"ከአሠልጣኝ ሰውነት ቢሻው ጊዜ ጀምሮ ተጫዋቾችን ለመመልመል ሞክሪያለሁ። ነገር ግን ኢትዮጵያውያን አሠልጣኞች ፈቃደኛ አይደሉም። ማሪያኖ ባሬቶ ብቻ ነው ፈቃደኛነቱን ያሳየኝ። ፌዴሬሽኑ ተጫዋቾችን ከውጭ እንዲያመጣ ግፊት በማድረጉ በእሱ ጊዜ እነዩሱፍ ሳልህ፣ ዋሊ ዳታና አሚን አስካር መጥተው ነበር።"
በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ስለትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች በመፃፍ የሚታወቀው አዶናይ ኤርሚያስም ይህ ምክንያት ሊሆን አይገባም ሲል ይላል።
"እኔ ባገኘሁት መረጃ አውሮፓ ውስጥ ብቻ 35 ገደማ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች አሉ" በማለት ከመካከላቸው የተወሰኑትን ይጠቅሳል።
በዚህም ኖርዌይ ዳንኤል፣ ከጀርመን የሊቨርፑሉ መልካሙ ወንድም መለሰ ፍራውንዶርፍን እንዲሁም ለአትላንታ የሚጫወተው አንዋር ሜዴሮን በማንሳት፣ በእስራኤል የመጀመሪያው ዲቪዚዮንም እንዲሁ ሦስት ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች አሉ ይላል።
አዶናይ የጠቀሳቸውን ተጫዋቾች ጨምሮ ስዊትዘርላንድ የሚጫወተው ማረን ኃይለ ሥላሴንና አሚን አስካር ለዋሊያዎቹ አስፈላጊ ናቸው ይላል።
"ዩሱፍ ሳላህ፣ ዋሊ ዳታ እና አሚን አስካር ለኢትዮጵያ እንዲጫወቱ የተጠሩት በአሠልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶ ጊዜ ይመስለኛል። ኢትዮጵያውያን አሠልጣኞች ከሚያውቁት ተጫዋች ጋር መሥራት እንጂ ከውጭ የሚመጡ ተጫዋቾችን ማከተት ይፈልጋሉ ብዬ አላስብም።"
ዴቪድ በሻህም በዚህ ሐሳብ ይስማማል። በተለይ ባለፉት ጊዜያት አሠልጣኞች ብዙም ፍላጎት እንደሌላቸው ይናገራል።
አዶናይ የፓስፖርት ምክንያት ውሃ የሚያነሳ አይደለም ይላል።
"ፊፋ 2014 ባወጣው አዲስ መመሪያ መሠረት አንድ ተጫዋች በእናቱና በአባቱ አሊያም በአያቶቹ ኢትዮጵያዊ ከሆነና ላደገበት አገር ዋና ብሔራዊ ቡድን ካልተጫወተ ለኢትዮጵያ የመጫወት መብት አለው። አሁን አሁን ፌዴሬሽኑ ይህንን ችግር ለመቅረፍ እየሠራ ያለ ይመስለኛል።"
'የማጣሪያ ጊዜ ለምን አይመጡም?'
ዴቪድና አዶናይ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ዋንጫ አሊያም ለሌላ ውድድር ስታልፍ ብቻ ነው የሚመጡት በሚለው ሐሳብ አይስማሙም።
"የውጭ ተጫዋቾች ምልመላን የጀመርኩት መስከረም ላይ ነው። ከዚያ በፊት ማን ጠርቷቸው ያውቃል? ማን ኑና ተሳተፉ ብሏቸው ያውቃል? ማንም። ነገር ግን ተጫዋቾቹ ጥሪ ብቻ ነው የሚጠብቁት። አሁን ለአፍሪካ ዋንጫ ካለፍን በኋላ የምልመላ ሥራውን ስለሰጡኝና ጊዜው ስለተገጣጠመ እንዲህ ማለት አይቻልም" ይላል ዴቪድ።
"ተጫዋቾቹ በማንኛውም ጊዜ ለኢትዮጵያ ለመጫወት ዝግጁ ናቸው። ነገር ግን ማንም ጠርቷቸው አያውቁም። ካልተጠሩ እንዴት ነው የሚመጡት?"
አዶናይ በበኩሉ ይህ ምክንያት የተጫዋቾችን ሞራል የሚነካ ነው ሲል ይከራከራል። ለዚህ ነው አንዳንድ ተጫዋቾች ለኢትዮጵያ የመጫወት ፍላጎታቸው እየቀነሰ የመጣው ይላል።
ፋርሃን 'ለዋንጫ ስናልፍ ብቻ ነው የሚመጡት' የሚለው ምክንያት ትርጉም አልባ ነው ይላሉ።
"የማጣሪያ ጨዋታ በሚደረግበት ወቅት ለአሠልጣኙ ሳይቀር እነዚህን ተጫዋቾች ተመልከቷቸው ብዬ መልዕክት ልኬ ነበር። ነገር ግን ከምንም ምላሽ አላገኘሁም።"
"ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾችን መጥራት ቀላል ነው። በግሌ ማኅበራዊ ሚድያን ጨምሮ በተለያየ መንገድ ያገኘኋቸውን ተጫዋቾች እንኳ ሊቀበሉ አልፈለጉም። አንዳንዴ ለአውሮፕላን ትኬት መክፈል አንችልም ይሉኛል። ተጫዋቾቹ ራሳቸው የትኬት ወጪያቸውን ይሸፍኑ ያሉኝ ጊዜም ነበር።"
'የስፖርት ቪዛ'
ዴቪድ ይህ የጥምር ዜግነት ጉዳይ ለሌሎችም አገራት ደንቃራ የነበረ ጉዳይ ነው ይላል። ነገር ግን አብኞቹ አገራት ይህንን ችግር እንደቀረፉ ይጠቅሳል።
ዴቪድ እንደምሳሌ ሱሪናም የተሰኘችውን ደቡብ አሜሪካዊት አገር ይጠቅሳል።
"99 በመቶ የሚሆኑት የኔዘርላንድስ ጥቁር ተጫዋቾች ከዚያ ነው የመጡት። ቫን ዳይክ ብትል፣ ክሎይቨርት፣ ሲዶርፍና ሌሎችም ከሱሪናም ናቸው። ነገር ግን ከሁለት ወይም ሦስት ዓመታት በፊት ይህን ችግር ለመቅረፍ 'ስፖርት ፓስ' አዘጋጁ። ይህ ፓስፖርት ለስፖርተኖች ብቻ የሚሰጥ ነው።
"ለምሳሌ ለቼልሲ የተጫወተው ሃስልባንክ ወንድም ልጅ በዚህ ፓስፖርት ምክንያት ሱሪናምን የወከለ የመጀመሪያው ተጫዋች ነው። ሌሎች ተጫዋቾችም ይህን ተከትለው መጥተው ሱሪናም ባለፈው ዓመት በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ለኮንካፍ ጎልድ ዋንጫ ማለፍ ችላለች።"
ዴቪድ ለዚህ ነው ይህ ጉዳይ ከታሰበበት መፍትሔ ማበጀት ቀላል ነው የምለው ይላል።
"ለምሳሌ እኔ ለብሔራዊ ቡድኑ በተጫወትኩበት ወቅት ፓስፖርት ያስፈልጋችኋል ብለው አምጥተው ሰጡን። በወቅቱ በኦፊሴላዊ መንገድ ላይሆን ይችላል ያደረጉት። አሁን ግን ይህ ችግር ፖለቲካዊ መፍትሔ ሊሰጠው ይገባል ነው የምለው።"
ይህ ሁኔታ ጊዜ እንደሚወስድ የሚገነዘበው ዴቪድ ሂደቱን ማፋጠን ይገባል ይላል። "ኢትዮጵያ ይህን መመሪያ የምታራምድ የመጨረሻ አገር ሳትሆን አትቀርም። እጄ ላይ ለምሳሌ 150 ተጫዋቾች አሉኝ። አብዛኞቹ በአካል ባላውቃቸውም በጊዜ ሂደት ማወቄና መመልመሌ አይቀርም።"
ዴቪድ በሻህ የውጭ ተጫዋቾች ይምጡ ማለት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚጫወቱት ይቀመጡ ማለት አይደለም ሲል ያሰምራል። "እኔ ዓላማዬ ብሔራዊ ቡድኑን በትውልደ ኢትዮጵያዊያን መሙላት አይደለም። በፍፁም። እኔ ማየት የምሻው ብሔራዊ ቡድኑ የድንቅ ተጫዋቾች ስብስብ ሆኖ ውጤት እንዲያመጣ ነው።"
ዴቪድ አክሎ ምንም እንኳ ኃላፊነቱን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቢሰጠውም ወጪውን ራሱ እየሸፈነ ተጫዋቾችን እንደሚመለምልና ከፌዴሬሽኑ ጋር በዚህ ጉዳይ ለመነጋገር እንዳቀደም ይናገራል።
"እኔ ተጫዋቾችን መመልመል እቀጥላለሁ። ትኩረቴን ወጣቶች ላይ ነው የማደርገው። ያሉበት ድረስ ሄጄ እገመግማለሁ። ማን ያውቃል የወቅቱ አሠልጣኝ ባይጠራቸው ቀጣዩ አሠልጣኝ ይጠራቸው ይሆናል. . . "














