የኬንያው ፕሬዝዳንት በአገራቸው ቁርጥራጭ ብረታ ብረቶች እንዳይሸጡ አገዱ

ቁርጥራጭ ብረት የያዘ ግለሰብ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በአገሪቱ ከግንባታዎች ላይ የተነሱ፣ ያገለገሉ እንዲሁም የተጣሉ ብረታ ብረቶች ሽያጭ እንዳይካሄድ አስቸኳይ እገዳ ጣሉ።

ይህ የፕሬዝዳንቱ ድንገተኛ እገዳ ይፋ የተደረገው መንግሥት እየጨመረ ነው ያለውን በአገሪቱ ውስጥ በሚገኙ የሕዝብ ንብረቶች ላይ የሚፈጸም ዝርፊያና ውድመትን ለመከላከል ጥረት እያደረገ ባለበት ወቅት ነው።

ይህ የወዳደቁና አሮጌ ብረቶች ሽያጭ እገዳ ተግባራዊ የሚሆነው የኬንያ መንግሥት የእነዚህን ብረታ ብረቶች ምንጭ፣ ንግድና ወደ ውጭ የሚላኩበትን ሁኔታ በተመለከተ ለመቆጣጠር የሚያስችል ደንብ አውጥቶ ተግባራዊ እስኪሆን ድረስ ነው።

ባለፈው ሳምንት በዋና ከተማዋ ናይሮቢ በሚገኝ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ተሸካሚ መስመር ላይ ተፈጸመ በተባለ ዘረፋ ምክንያት በአገር አቀፍ ደረጃ የኤሌክትሪክ መቋረጥ አጋጥሞ ነበር።

በመላዋ ኬንያ በተቋረጠው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ሰበብ ዘጠኝ የኬንያ መብራት ኃይል አቅራቢ ተቋም ከፍተኛ ሥራ አስኪያጆች በቁጥጥር ስር ውለው ፍርድ ቤት ቀርበዋል።

የባቡር ሃዲዶችን፣ የኮምዩኒኬሽን ማማዎችን እንዲሁም የኤሌክትሪክ ማስተላላፊያ መስመሮችን ጨምሮ ኬንያ ውስጥ በሚገኙ የሕዝብ መሠረተ ልማቶች ላይ ተደጋጋሚ የሆነ ዘረፋና ውድመት ማጋጠሙ ተነግሯል።

ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የወዳደቁ አሮጌ ብረቶችን ባገዱበት ወቅት እንዳሉት በሕዝብ ቁልፍ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚፈጸመው ዘረፋና ጥፋት ከምጣኔ ሀብት አሻጥር ጋር የሚስተካከል በመሆኑ የአገር ክህደት ተግባር ነው ብለዋል።

በመሠረተ ልማቶች ላይ የሚፈጸሙ ዘረፋዎችን በበተመለከተ የኬንያው ፕሬዝዳንት ማስጠንቀቂያ ሲሰጡ የአሁኑ የመጀመሪያው አይደለም።

ከሦስት ዓመት በፊት የአገሪቱን ግዙፍ የባቡር መስመር ግንባታ ባስጀመሩበት ጊዜ ከቻይና በተገኘ ብዙ ቢሊዮን ዶላር ብድር በሚሰራው መሠረተ ልማት ላይ ጉዳት የሚያደርስ ሰው በሞት እንዲቀጣ እንደሚያጸድቁ አስጠንቅቀው ነበር።

የተለያዩ ግዙፍ ሕዝባዊ መሠረተ ልማቶች የተገነቡባቸውን የተለያዩ የብረት አካላት ዘራፊዎች ነቅለው ወይም ቆርጠው በመውሰድ ለሽያጭና የተለያዩ ነገሮችን ለመስራት ያውሉታል።

ይህ የኬንያ ችግር ብቻ ያልሆነው የብረታብረቶች ዝርፊያና ውድመት ከተለያዩ መሠረተ ልማቶች የተዘረፉት ቁርጥራጭ የብረት አይነቶን ከአገር ውጪ በመውሰድ ለሌሎች ወገኖች እንደሚሸጡ ይነገራል።