ጦርነቱ መፍትሔ እንዲያገኝ ከኢትዮጵያ ጋር ተቀራርባ እንደምትሰራ ኬንያ ገለጸች

የፎቶው ባለመብት, Kenyan ministry of foreign affairs/fb
ኬንያ በጎረቤት ኢትዮጵያ ያለው ቀውስ መፍትሔ እንዲያገኝ የምታደርገውን ጥረት ሁሉ በሰከነ ሁኔታ ተቀራርባ በመስራቷ እንደምትቀጥል ገለጸች።
የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራይቼል ኦማሞ እንዳሉት አገራቸው ኢትዮጵያን ችላ እንደማትላትና የሰከነና የተለሳለሰ ዲፕሎማሲን በመጠቀም በአገሪቱ የተከሰተው ችግር እንዲያበቃ አብራት መስራቷን ትቀጥላለች።
ሚኒስትሯ ይህንን የተናገሩት አርብ ዕለት የኬንያን የውጭ ፖሊሲ እና አካባቢያዊ ሁኔታዎች በተመለከተ ናይሮቢ ውስጥ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራይቼል ኦማሞ "ምንም እንኳን ጊዜ የሚጠይቅ ቢሆንም ኢትዮጵያ ከስምምነት ላይ ለመድረስ የሚያስችል አቅም አላት" ብላ ኬንያ እንደምታምን ገልጸው፣ ለዚህም በቅርቡ የፖለቲካ እስረኞች የመለቀቃቸው እርምጃን እንደ በጎ ጅማሬ ጠቅሰዋል።
ሚኒስትሯ ጨምረውም በአገሪቱ ካለው ወቅታዊ ሁኔታ አኳያ በብሔራዊ ውይይት፣ በተኩስ አቁም እና ሰብአዊ እርዳታ እንዲቀርብ መንገድ ማመቻቸትን በሚመለከት ከኢትዮጵያ ጋር ተቀራርበው ሲሰሩ እንደነበር ተናግረዋል።
ኬንያ በምሥራቅ አፍሪካ የትልቅ ምጣኔ ሀብት ባለቤትና በአካባቢው አገራት መካከል ተጽእኖ ፈጣሪ ከሆኑ ጥቂት አንዷ ሰትሆን፤ በተጨማሪም ከምዕራባውያን አገራት ጋር የቀረበ ጠንካራ ግንኙነት ያላት አገር መሆኑ ይታወቃል።
በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ጦርነት ከተጀመረ በኋላ ምዕራባውያን አገራት ከኢትዮጵያ ጋር የነበራቸው ግንኙነት በሻከረበት ወቅት የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣንት ጦርነቱን በሚመለከት ከኬንያው ፕሬዝዳንትና ከአገሪቱ ባለሥልጣንት ጋር በተደጋጋሚ ይወያዩ ነበር።
በዚህም ኢትዮጵያ በግዛቷ ውስጥ ስላለው ሁኔታ በቀጥታ ከእሷ ጋር መነጋገር እየተቻለ አሜሪካ ከጎረቤት አገር ኬንያ ጋር በምታደርገው ውይይት ደስተኛ እንዳልሆነች የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ መግለጻቸው ይታወሳል።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ አንተኒ ብሊንከን ባለፈው ኅዳር ወር ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ ሦስት አገራት ያደረጉትን ጉብኝት ከኬንያ የጀመሩ ሲሆን፣ በጉዟቸው ከቀዳሚ አጀንዳቸው መካከል በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ አንዱ ነበር።
የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ከፕሬዝዳንት ባይደን ጋር እና ከውጭ ጉዳይ ኃላፊው ጋር በኢትዮጵያ ስለተከሰተው ቀውስ ከመነጋገራቸው ባሻገር ወደ ኢትዮጵያ ተጉዘው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ተወያይተዋል።
የኢትዮጵያ የቅርብ ወዳጅ የሆነችው ኬንያ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ የተለያዩ ጥረቶችን ስታደርግ የቆየች ሲሆን በዚህ ሂደት ስለነበሩ ጉዳዮች ግን እስካሁን ይፋ አድርጋ አታውቅም።
ከአንድ ዓመት በላይ የዘለቀው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በአሁኑ ወቅት ጋብ ያለ በሆንም በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ ግን ግጭቶች እንዳሉ ይነገራል።
ይህንን ጦርነት ለማስቆም የአፍሪካ ሕብረት እና አሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ አሰማርተው ጥረት እያደረጉ ሲሆን የተለያዩ አገራትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ደግሞ ጦርነቱ ሰላማዊ መፍትሔ እንዲያገኝ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።
ከዚህ ጋር ተያይዞ የአፍሪካ ሕብረት ልዩ ተወካይ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ እንዲሁም የአሜሪካው ልዩ መልዕክተኛ ዴቪድ ሳተርፊልድ ከከፍተኛ የውጭ ጉዳይ ባለሥልጣን ጋር ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ጦርነቱ ስሚያበቃበት ሁኔታ መወያየታቸው ይታወቃል።
ሰሞኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደውን ጦርነት ለማብቃትና ሰላም ለማውረድ የሚያስችል የሚታይ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ከኦባሳንጆ ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት መረዳታቸውንና ገልጸዋል።
በዚህም በኢትዮጵያና በአካባቢው የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለችግር ያጋለጠውና ከአንድ ዓመት በላይ የተካሄደውን ወታደራዊ ግጭት በማብቃት ሰላም ለማውረድ የሚያስችል ተጨባጭ ጥረት እየተደረገ መሆኑ እንዳስደሰታቸው የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ፀሐፊ ተናግረዋል።












