ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር የተገናኙት የዩኬ የአፍሪካ ሚኒስትር ጦርነቱ እንዲቆም አሳሰቡ

የፎቶው ባለመብት, Vicky Ford
ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ተገናኝተው የተወያዩት የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) የአፍሪካ ሚኒስትር ቪኪ ፎርድ "ጦርነቱ ለመግለጽ የሚከብድ ሰቆቃ አድርሷል። መቆም አለበት" ሲሉ አሳሰቡ።
ቪኪ ፎርድ ወደ ኢትዮጵያ ተጉዘው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ከምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና ከገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ጋር መወያየታቸውን የዩኬ መንግሥት ድረ-ገጽ አመልክቷል።
የዩኬ የአፍሪካ ሚንስትሯ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከአገሪቱ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ባደጉት ንግግር ለጦርነቱ ሰላማዊ መፍትሔ እንዲሰጥ መጠየቃቸው ተገልጿል።
ቪኪ ፎርድ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ስላደረጉት ውይይት በትዊተር ገጻቸው ላይ "እስረኞች መፈታታቸው እና ብሔራዊ ውይይት ሊካሄድ መሆኑ እንዳስደሰተን ነግሬያቸዋለሁ" ሲሉ ጽፈዋል።
ዩናይትድ ኪንግደም የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት እጅግ እንዳሳሰባት እና በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እንደምትሻም ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መግለጻቸውን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ከአምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ጋር ስላደረጉት ውይይት በትዊተር ገጻቸው "በሰሜን ኢትዮጵያ ሰላም ማስፈን ስላለው ዋጋ ተወያይተናል። ስለ ግልጽ ውይይታችን አመሰግንዎታለሁ" ሲሉ አስፍረዋል።
ለ14 ወራት የዘለቀው ጦርነት እንዲያከትም የአፍሪካ ሕብረት እያደረገ ያለውን የማሸማገል ጥረት የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት እንደሚደግፍም ሚኒስትሯ ቪኪ ተናግረዋል።
"የኢትዮጵያ መንግሥትን እና የትግራይ ኃይሎችን ለማደራደር እንዲሁም ለጦርነቱ ሰላማዊ መቋጫ ለመስጠት የአፍሪካ ሕብረት እያደረገ ያለውን ጥረት እንደግፋለን" ብለዋል።
"ሁሉም ወገኖች ውጊያ አቁመው የሰላም ጥረቱን መደገፍ አለባቸው" ያሉት ሚኒስትሯ በአፍሪካ ሕብረት መሪነት የሚደረገውን የድርድር ጥረት ሁሉም አካላት እንዲደግፉም ጠይቀዋል።
አያይዘውም "የብሔራዊ ውይይት ኮሚሽን መቋቋሙን በበጎ እናየዋለን። የፖለቲካ እስረኞች መፈታታቸውም ጥሩ እርምጃ ነው" ብለዋል።
ከሰሜኑ ጦርነት በተጨማሪ በሌሎችም የአገሪቱ ክፍሎች ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ መፈጠሩ እንዳሳሰባቸው የገለጹት ሚኒስትሯ፤ የዩኬ መንግሥት በደቡብ ኢትዮጵያ ለተከሰተው ድርቅ የ5 ሚሊዮን ፓውንድ ድጋፍ እንደሚሰጥም ቃል ገብተዋል።
በተጨማሪም በግጭት ሳቢያ ለተጎዱ ወገኖች የጤና እና ትምህርት አቅርቦት የሚውል 5 ሚሊዮን ፓውንድ እንዲሁም ሰላም እና ሰብዓዊ መብት ለማስጠቅ ተጨማሪ 4.5 ሚሊዮን ፓውንድ በዩኬ መንግሥት መመደቡብ ገልጸዋል።
"ይህ ገንዘብ የዩኬ መንግሥት ሰብአዊ ቀውሱን ለማሻሻል ለትግራይ፣ ለአማራ እና አፋር ክልሎች ከመደበው 76 ሚሊዮን ፓውንድ በተጨማሪ የሚሰጥ ነው" ተብሏል።
ኢትዮጵያ በአሥርት ዓመታት ያልታየ ድርቅ እንደገጠማት እና በዚህ ፈታኝ ወቅት ዩኬ ከኢትዮጵያ ጎን እንደምትቆም ተገልጿል።
ሚኒስትሯ በኢትዮጵያ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት አገራቸው ቃል የገባችው ገንዘብ "ለአሥርታት ባልታየ ድርቅ ሳቢያ ለተጎዱ 200,000 ዜጎች ሕይወት አድን ምግብ ያቀርባል" ተብሏል።
በተጨማሪም ወሲባዊ ጥቃት የደረሰባቸውን ዜጎች ለመደገፍ እንዲሁም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንን አቅም ለማጎልበት ይውላል።












