ሳዑዲ አረቢያ "ሐሜት የሚያሰራጩ ሰዎችን በእስር እቀጣለሁ" ስትል አስጠነቀቀች

ሳዑዲ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሳዑዲ ባለሥልጣናት ማኅበራዊ ድር አምባዎች ላይ "እርባና ቢስ" ሐሜት የሚያሰራጩ ሰዎች እስከ አምስት ዓመት እስራትና ከባድ የገንዘብ ቅጣት እንደሚጠብቃቸው አወጁ።

ይህ የሆነው አንድ የሙዚቃ ድግስ መሰረዙን ተከትሎ ወደ ቤታቸው እየተመለሱ ያሉ ወጣት ሴቶች ትንኮሳ እየደረሰባቸው ነው የሚል ዜና ኢንተርኔት ላይ ከተሰራጨ በኋላ ነው።

አንዳንድ ሴቶች በዚህ የሙዚቃ ድግስ ላይ የተፈጠረውን ነገር ለመናገር እንደሚፈሩ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የሳዑዲ መዝናኛ ባለሥልጣን ኃላፊ ሴቶቹ ያቀረቡትን ቅሬታ በተደጋጋሚ እየተረቡ ውድቅ ሲያደርጉ ታይተዋል።

ሳዑዲ በጣም ዝግና ጥብቅ ከሆነ አገዛዝ አሁን የሙዚቃ ኮንሰርቶችን ወደ ማዘጋጀት ብትሸጋገርም ባህላዊና ማኅበረሰባዊ መስተጋብሩ ሲጋጩ በተደጋጋሚ ይስተዋላል።

የኬ-ፖፕ የሙዚቃ ባንድ የሆኑት ስትሬይ ኪድስ ባለፈው ሳምንት ሊያቀርቡ የነበረው የሙዚቃ ድግስ የተሰረዘው በከባድ ነፋስ ምክንያት ነው።

በዚህ የተበሳጩ የሙዚቀኞቹ አድናቂዎች ከሪያድ ወጣ ብሎ ከሚገኘው የድግስ ስፍራ ወደ ቤታቸው ለመመለስ እክል ገጥሟቸው ነበር።

በዚህ ጊዜ ነው አንዳንድ ሴቶች የገቡበት አልታወቀም፤ ወሲባዊ ትንኮሳም እየገጠማቸው ነው የሚሉ ክሶች ማኅበራዊ ድር አምባው ላይ መናፈስ የጀመሩት።

በስፍራው ምን እንደተፈጠረ እስካሁን በውል ባይታወቅም በርካታ ሰዎች ድንጋጤ ውስጥ እንዳሉ ሲጽፉ ተስተውለዋል።

በሌላ በኩል በርካታ በስፍራው ነበርን ያሉ ሰዎች ደግሞ ምንም ነገር አልተፈጠረም፤ እንደውም አዘጋጆቹ ሁኔታውን በደንብ ተወጥተውታል ሲሉ ጽፈዋል።

በስፍራው ወሲባዊ ትንኮሳ ነበር ያሉ ሰዎች ወንዶች ትንኮሳ ሲፈጽሙ የሚያሳይ ምስል ቢለቁም አብዛኛዎቹ ፎቶዎቹ ከዚህ በፊት የተነሱ እንዲሁም የታዋቂ ሰዎች ሆነው ተገኝተዋል።

ይህ ጉዳይ በስፍራው ወሲባዊ ትንኮሳ ተፈጽሞ ነበር የሚሉ ሴቶችን ክስ ያንኳሰሰ ሆኖ ተገኝቷል።

የሳዑዲ የመዝናኛ ባለሥልጣን ኃላፊ የሆኑት ተርኪ አል-ሸይኽ በትዊተር ገጻቸው የሴቶቹን አቤቱታ የሚያጣጥል ተደጋጋሚ መልዕክት ጽፈዋል።

ይህን ተከትሎ ወጣት ሴቶች ጠፍተዋል አሊያም ወሲባዊ ትንኮሳ ደርሶባቸዋል በሚሉ ዜናዎች ላይ ተረብና የሳዑዲ መንግሥትን ስም ለማጥፋት የተደረገ ነው የሚል ወቀሳ ይደርስ ጀመር።

ነገር ግን ቢቢሲ በመሰል የመዝናኛ ሥፍራዎች ላይ የሚደርስን ትንኮሳ አስመልክቶ ከዚህ በፊት ያናገራቸው ሴቶች አንዳንዱ ወሬ እውነት ነው ይላሉ።

እኒህ ሴቶች እንደሚሉት መሰል ቅሬታዎችን ማሕበራዊ ድር አምባዎች ላይ የሚለጥፉ አሊያም ውይይት የሚቀሰቅሱ ሰዎች ማስፈራሪያ ይደርሳቸዋል፤ ካልሆነም ገጻቸው ይዘጋባቸዋል።

ሴቶቹ እንደሚሉት፤ ባለሥልጣናት ይህንን ቅሬታ የሚያጣጥሉት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ነፃና የመዝናኛ ማዕከል ተደርጋ እየተቀረፀች ያለችው ሳዑዲ ስም እንዳይቆሽሽ ነው።

ነገር ግን ይህ የመንግሥት ድርጊት ሴቶች የደረሰባቸውን ወሲባዊ ትንኮሳ በአደባባይ እንዳይናገሩ ያደርጋል፤ ይህ ደግሞ በፊትም ቢሆን በባህል ምክንያት ነጋሪ ያጣ ጉዳይ ነው ይላሉ።

በቅርቡ አንድ ወሲባዊ ትንኮሳ አድርሷል የተባለ ግለሰብ ስሙ በመገናኝ ብዙሃን እንዲጠራ ተደርጓል። ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ የሆነ ነው።

የልዑል አልጋ ወራሹ ደጋፊዎች ሳዑዲ ትልቅ ለውጥ ላይ ነው ያለችው፤ እንዲህ ዓይነት ለውጦች ደግሞ እክል ሊያጋጥማቸው ይችላል ሲሉ ይከራከራሉ።

ነገር ግን ባለፈው ሳምንት በተሰረዘው የሙዚቃ ድግስ ላይ የነበሩ ሴቶች የደረሰባቸውን ከመናገር እንዲሸማቀቁ ተደርገዋል።