የፕላስቲክ ብክለትን ለመቆጣጠር አስገዳጅ ስምምነት እንዲደረስ ጥያቄ ቀረበ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከፕላስቲክ ምርቶች ጋር ተያይዞ የሚከሰት የአካባቢ ብክለት ዓለማችንን በእጅጉ የሚያሳስባት ጉዳይ እንደሆነና ይህንን ለመቆጣጠር የተባበሩት መንግሥታት አገራትን ከስምምነት እንዲሰርሱ ማድረግ እንዳለበት አንድ ጥናት ጠቆመ።
ዓለም አቀፉ የከባቢ አየር ምርመራ ኤጀንሲ (ኢአይኤ) እንደሚለው ስለብክለቱ ለበርካታ አስርት ዓመታት ሲጠራቀም የነበረው ጥናት በቂ ማሳያ ነው ብሏል።
ኤጀንሲው እንደሚለው የፕላስቲክ ብክለት ከአየር ብክለት ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ጉዳት አለው።
አሁን ላይ የዓለማችን ሕዝቦች የሚተነፍሱት አየር የፕላስቲክ ቅንጣቶች አሉት። በተጨማሪም የአርክቲክ የበረዶ ግግር፣ የምድራችን አፈር እና የምመገበው ምግብ ጭምር በውስጣቸው የፕላስቲክ ቅንጣቶች አሉባቸው።
ሪፖርቱ እንደሚለው በታይላንድ ከቆሻሻ ማጠራቀሚያ ውስጥ ፕላስቲኮችን የተመገቡ 20 ዝሆኖች ህይወታቸው አልፏል።
የሪፖርቱ አዘጋጆች የተባበሩት መንግሥታት የዓለም አገራት የፕላስቲክ ምርትን ለመቀነስና በተገቢው መንገድ ለማስወገድ እንዲስማሙ እንዲያደርግ አጥብቆ ጠይቋል።
"በዚህ ፍጥነት እየሄደ ያለው ብክለት በቶሎ መፍትሔ ካልተበጀለት በ2040 የፕላስቲክ መጠን በመላው ዓለም ከሚገኙ አሳዎች መጠን በላይ ሊሆን ይችላል" ሲል ያስረዳል ከኤጀንሲው የተወከለው ቶም ጋማጅ።
የተባበሩት መንግሥታት ዓለማችንን የሚያሰጓት ነገሮች ብሎ ሦስት ጉዳዮችን አንስቷል። የመጀመሪያ የአየር ንብረት ለውጥ ሲሆን ሁለተኛው የብዝኃ ሕይወት መጥፋት እንዲሁም ሦስተኛው ደግሞ ብክለት ነው። ድርጅቱ እንደሚለው እነዚህ ሦስት አሳሳቢ ችግሮች በፍጥነት መልስ ሊሰጣቸው ይገባል።
የአየር ንብረት ለውጥን እንዲሁም የብዝኃ ሕይወት መጥፋትን በተመለከተ አገራት ለ30 ዓመታት የቆየ ስምምነት ቢኖራቸውም ለውጥ ማምጣት ላይ እንዲሁም የበካይ ጋዞች መጠንን መቀነስ ላይ እምብዛም ውጤት አላሳዩም።
በቅርብ ዓመታት የፕላስቲክ ምርትና አወጋገድን በተመለከተ አገራት ሊደርሱበት የነበረው ስምምነት በአንዳንድ አገራት ተቃውሞ ገጥሞታል።
ነገር ግን ከ100 በላይ የሚሆኑ አገራት ይህ ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን የፊታችን የካቲት እና መጋቢት ላይ በሚካሄደው የተባበሩት መንግሥታት የከባቢ አየር ስብሰባ ላይ ጉዳዩ እንዲነሳ ተስማምተዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከዚህ በፊት በዶናልድ ትራምፕ ተቀባይነት ያላገኙ ዓለም አቀፋዊ ስምምነቶችን አገራቸው እንደምትቀበል አስታውቀዋል።
ነገር ግን ይህንን ሀሳብ የአሜሪካ ኮንግረስ ይቀበለው፣ አይቀበለው አይታወቅም። ምክንያቱ ደግሞ በርካታ የአሜሪካ ድርጅቶች የነዳጅና ጋዝ ተረፈ ምርታቸው ፕላስቲክ መሆኑ ነው።
በሌላ በኩል ጃፓን ይህንን ስምምነት እምብዛም እንደማትደግፈው እየተገለጸ ነው። የአረብ ባሕረ ሰላጤው አገራት እና ቻይና ደግሞ በጉዳዩ ላይ እስካሁን ምንም አይነት አስተያየት አልሰጡም።
ምንም እንኳን አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም ከፍተኛውን የፕላስቲክ መጠን ቢያመርቱም ቻይናም ቀላል የማይባል ድርሻ አላት።
በጉዳዩ ላይ ከፍተኛ ምርምር የሚያደርጉት ፕሮፌሰር ሪቻርድ ቶምፕሰን እንደሚሉት የተባበሩት መንግሥታት ፕላስቲኮች ጥቅም ላይ ከዋሉ በኋላ ሙሉ በሙሉ ከምድረ ገጽ ለማጥፋት የሚያስችሉ መንገዶች መፈለግ አለበት።
"በመጀመሪያ ትልቁ ችግር ጥናት ላይ ያልተመሰረተ የፕላስቲክ ምርትና አጠቃቀም ነው። ፕላስቲኮችን መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚረዱ ፖሊሲዎችን ማርቀቅ እምብዛም አይጠቅመንም። ከሆነ ዓመት በኋላ ፕላስቲኮቹ ተመልሰው ወደ ምድራቸው መጣላቸው አይቀርም'' ይላሉ።















