ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በቃለ ምልልሳቸው ምን አሉ?

ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ

የፎቶው ባለመብት, EriTV

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሰኔ ወር መጨረሻ ላይ ከመቀለና ከተለያዩ ትግራይ አካባቢዎች መውጣቱ "ያልጠበቅነውና ድንገተኛ ነው" ሲሉ የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ተናገሩ።

ፕሬዚዳንት ኢሳያስ የመከላከያን ሠራዊት ከትግራይ ለቆ የመውጣት ውሳኔም ስልታዊ ማፈግፈግ ነበር ሲሉ የተናገሩት በትናንትናው ዕለት ታኅሣሥ 30/2014 ዓ.ም ከኤርትራ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ላይ ነው።

ፕሬዚዳንቱ በቀጥታ በተላለፈው ቃለ መጠይቅ ጦሯቸው በትግራይ ጦርነት እንዴት እንደተሳተፈ፣ ቀጣናዊ ጉዳዮችን፣ የአገራቸውን ወቅታዊ ሁኔታና ዓለም አቀፍ ፖለቲካውን በተመለከተ በዝርዝር ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ከቃለ መጠይቁ በፊት ከቀናት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ብሔራዊ እርቅን ለማምጣት እና "አንድነትን" ለማጎልበት ባሉት እርምጃ የቀድሞ የህወሓት አመራሮችን፣ የተቃዋሚ ፖለቲከኞችንና አባላትን የተፈቱ ሲሆን በተመሳሳይም የኤርትራው ፕሬዚዳንት ለፖለቲካ እስረኞች ምህረት ያደርጋሉ ብለው በርካታ ኤርትራውያን ቢጠብቁም እውን ሳይሆን ቀርቷል።

ከዚህም ጋር በተያያዘ በርካታ ኤርትራውያን ዲያስፖራዎችም ቅሬታቸውን በማኅበራዊ የትስስር ገጾች እየገለጹ ይገኛሉ።

ፕሬዚዳንቱ ኢትዮጵያንና ቀጠናውን በተመለከተ ምን አሉ?

ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ኤርትራን የገዙት የኤርትራው ፕሬዚዳንት ጦራቸው ወደ ትግራይ የገባው ህወሓት በተኮሰው ሚሳኤል ተገፍተው እንደሆነ በትናንትናው ቃለ መጠይቅ ተናግረዋል።

ህወሓት በኤርትራ ላይ ሚሳኤል እንደተኮሰና 100 አካባቢዎችን ኢላማም አድርገው ነበር ብለዋል። በትግራይ ጦርነት የተሳተፉትም ራሳቸውን ለመከላከል እንደሆነም ገልጸዋል።

በትግራዩ ጦርነት የተሳተፈው የኤርትራ ሠራዊት በርካታ እንደ ጦር ወንጀል ሊቆጠሩ የሚችሉ ወንጀሎችን ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ መጠቀምን ጨምሮ፣ መድፈር፣ ግድያና ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕግና የስደተኛ ሕግ ጥሰቶችን ፈፅሟል በሚልም በርካታ ክሶች ቀርበውበታል።

በርካታ አገራትና ተቋማትም ኤርትራ ሠራዊቷን ከኢትዮጵያ እንድታስወጣ በተደጋጋሚ ጫና ሲያደርጉ ቆይተዋል። ኤርትራ በበኩሏ ይህ የተቀናጀ ጥቃት ነው በሚል ክሱን አጣጥለዋለች።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሰኔ ወር መጨረሻ ላይ ከመቀለና ከተለያዩ ትግራይ አካባቢዎች መውጣቱ "ያልጠበቅነውና ድንገተኛ ነበር" ካሉ በኋላ ውሳኔው ስልታዊ ማፈግፈግ ነበር ብለውታል።

በወቅቱ የፌደራሉ መንግሥት የተኩስ አቁም ያወጀው እና መቀለን ለቅቆ የወጣው ግጭቱ እንዲቆም እና የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ በሚል ምክንያት ስለመሆኑ ገልጿል። ህወሓት በበኩሉ ሠራዊቱ ተሸንፎ ከትግራይ መውጣቱን መግለጹ የሚታወስ ነው።

በዚህ ቃለ መጠይቅ ስለ ጦርነቱ ጅማሮ የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ ጥቅምት 24 የትግራይ ኃይሎች በሰሜን ዕዝ ላይ በነበረው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት ከፈጸሙ በኋላ አምስትና ስድስት ሺህ የሚሆኑት የመከላከያ ሠራዊት አባላት ወደ ኤርትራ መሸሻቸውን ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንቱ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ አገራቸው የሚያሳስባት አሁን በኢትዮጵያ የተከሰተው ጦርነት ብቻ ሳይሆን ስር የሰደደና ረዥም ታሪክ ያለው እንደሆነ ጠቅሰዋል።

ለዘመናት በኢትዮጵያ የነበሩ የተለያዩ ሥርዓቶች የኤርትራን ሕዝብ ሲጎዱ ቆይተዋል በማለትም ወቅሰዋል። ከአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ፣ በደርግና በህወሓት/ኢህአዴግ ሥርዓት ለዘመናት እየተንከባለለ የመጣና የኤርትራን ሕዝብ የሚጎዳ አካሄድ ሲተገበር መቆየቱንም በቃለ መጠይቁ ወቅት ተናግረዋል።

ይህን ላለፉት 80 ዓመታት የቀጠለውን ሁኔታ አገራቸው በአትኩሮት እንደምትከታተለውም አፅንኦት ሰጥተዋል።

"በኢትዮጵያ ውስጥ መረጋጋት ሳይመጣና ለዚህ የሚያበቃ ሥርዓተ መንግሥት ሳይዘረጋ ከመጣው ሥርዓት ሁሉ እየተፋተግን መቀጠል አንችልም። ለዚህም የራሳችንን አስተዋፅኦ ማበርከት ስላለብን እጃችንን አጣጥፈን የምንመለከተው አይሆንም" ሲሉም ተደምጠዋል።

ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መምጣት ጋር ተያይዞ በሁለቱ አገራት መካከል የነበረው ውጥረት ይፈታል የሚል እምነት ቢኖራቸውም ህወሓትና በስም ያልጠቀሷቸው አጋሮቹ ብለው የጠራቸው አካላት ለውጡን ባለመቀበላቸው ከመጀመሪያው ጀምሮ የሰላሙ ሁኔታ ያሳስባቸው እንደነበር ተናግረዋል።

"አንዳንዱ ሰው ተስፈኛ ስለሆነ ሰላም፣ ሰላም ሲባል ሁኔታዎችን በጥልቀት ሳይገመግም በአዎንታዊ መልኩ አይቶታል" ብለዋል ፕሬዚዳንቱ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት በርካታ የኢትዮጵያ ታጣቂ ኃይሎች በኤርትራ መቀመጫቸውን አድርገው መቆየታቸው የሚታወስ ነው።

ፕሬዚዳንቱ ባለፉት ሰላሳ ዓመታት ስላለው የኢትዮጵያ ሁኔታ የገመገሙ ሲሆን በኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረው መቃቃር መቼ እልባት እንደሚያገኝ ማን እንደሚፈታው ትልቅ ጥያቄ ነው ብለዋል።

"ሆኖም የራሳቸው ጉዳይ ነው ብለን ዝም አንልም። ሆኖም [የእኛ ተሳትፎ ] በዘፈቀደ ሳይሆን በእውቀትና በእቅድና በዲዛይን የሚደረግ ይሆናል" በማለት አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ ያለውን በብሔር ላይ የተመሰረተ ፌደራሊዝም በተደጋጋሚ ሲነቅፉ የሚሰሙት ፕሬዚዳንቱ በትናንትናውም ቃለ መጠይቅ በዜግነት ላይ የተመሰረተ ሀገር ከመገንባት ይልቅ የብሔረሰቦች አገራትንና ተቋማትን መፍጠር የሚፈልጉ የውጭ ኃይሎች እጅ አለበት ብለዋል።

ቀጣናውንም አስመልክቶ ያነሱ ሲሆን ባለፉት ሰላሳ ዓመታት በሶማሊያ ላይ የታየው መከፋፈልና በቅርብ ጊዜም በሱዳን ላይ እየታየ ያለው ቀውስ እንደሚያሳስባቸው ተናግረዋል።

ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችን በተመለከተ

በትናንትናው ቃለ መጠይቅ በያንዳንዱ የዓለም አካባቢ የሚፈጠር ቀውስ በራሳቸው መንገድ ለመፍታት በበላይነትና በብቸኝነት ለመፍታት ጥረት የሚያደርጉና የተለየ ጥቅም ጠባቂዎች ሲሉ የአሜሪካ ባለሥልጣናትን ከሰዋል።

"ኤርትራ የኛን ጥቅም የምታገለግል አይደለችም" በማለት በተከተሉት ፖሊሲ ምክንያት የኤርትራ ሁለት ትውልዶችን መስዋዕትነት አስከፍለዋል ሲሉም ወንጅለዋል።

እነዚህ የተለየ ጥቅም ጠባቂ ያሏቸው የአሜሪካ ባለሥልጣናት ከተለያዩ የጎረቤት አገሮች ጋር ግጭት በመቀስቀስ ኤርትራ ወደፊት እንዳትራመድ በክስና በስም ማጥፋት ለዘጠኝ ዓመታት ያህል በማዕቀብ መቅጣታቸውን አስታውሰው፣ አሁንም ከትግራይ ጦርነት ጋር በተያያዘ ፍትሃዊ ያልሆነ ማዕቀብ ተጥሎብናል በማለት ወቅሰዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ የአሜሪካ መንግሥት በአራት የኤርትራ ተቋማትና በሁለት ኤርትራውያን ላይ በያዝነው ዓመት ማዕቀብ ጥሏል።

ማዕቀቡ የኢትዮጵያን መረጋጋትና አንድነት እያናጋ ነው ባለው ቀውስና ግጭት ውስጥ አስተዋጽኦ አላቸው ያላቸውን የኤርትራ ተቋማትና ዜጎችን ኢላማ ያደረገ መሆኑን የአሜሪካ የፌደራል ግምጃ ቤት በወቅቱ አመልክቷል።

በዚህም መሠረት ዕቀባው የተጣለባቸው ተቋማት የኤርትራ መከላከያ ኃይል፣ የኤርትራ ገዢ ፓርቲ ህዝባዊ ግንባር ለዴሞክራሲና ለፍትህ፣ ህድሪ ትረስ እና ሬድ ሲ ትሬዲንግ ኮርፖሬሽን ሲሆኑ ግለሰቦቹ ደግሞ አብረሃ ካሳ ነማሪያም እና ሐጎስ ገብረሕይወት ወልደኪዳን የተባሉት ናቸው።

በኤርትራ የሁለት ቀናት ጉብኝት ከሰሞኑ ያደረጉት የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ በኤርትራ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ አውግዘዋል።

ፕሬዚዳንቱም የቻይናን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርን ጉብኝት በማንሳት ከአገሪቱ ጋር ያለውን ስትራቴጂካዊ አጋርነት ወደ ትግበራ የሚገባበት ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ጠቅሰዋል።