የጠፋበትን ሞተርሳይክል ለመግዛት ልጁን ሊሸጥ የነበረው አባት ላይቤሪያ ውስጥ ተያዘ

ላይቤሪያ ገንዘብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ላይቤሪያ ገንዘብ

የላይቤሪያ ፖሊስ አንድ ሴራሊዮናዊ ግለሰብ የ10 ዓመት ወንድ ልጁን ሊሸጥ ነበር ሲል በቁጥጥር ሥር አውሎ ክስ እንደመሰረተበት አስታወቀ።

የ29 ዓመቱ አባት ልጁን ለመሸጥ የፈለገው ከቤቱ የተሰረቀበትን ሞተር ሳይክል ለመተካት የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለማሟላት እንደሆነም ተነግሯል።

ግለሰቡ በላይቤሪያዋ ዋና ከተማ ሞንሮቪያ ውስጥ በፖሊስ ከተያዘ በኋላ ለመርማሪዎች እንዳስረዳው ልጁን ለመሸጥ የተገደደው፣ የጓደኛው የነበረ ሞተርሳይክል ከእሱ ቤት ከተሰረቀ በኋላ ያንን ገዝቶ ለመተካት ነበር ልጁን ለሽያጭ ያቀረበው።

በሽያጩ 146ሺህ የላይቤሪያ ዶላር ወይም አንድ ሺህ የአሜሪካ ዶላር ለማግኘት አቅዶ ልጁን ለመሸጥ ድንበር ተሻግሮ ላይቤሪያ መግባቱን ለፖሊስ ተናግሯል።

ግለሰቡ ይህንን እዳውን ለመሸፈን በፍጥነት ገንዘቡን አገኝበታለው ያለው መንገድ ልጁን ከጎረቤት አገር ሴራሊዮን ወደ ላይቤሪያ በመውሰድ የሚገዛውን ሰው ለመፈለግ መሞከር ነበር።

እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው በአገሩ ውስጥ ድንበር ተሻግሮ ልጁን የሚገዛው ሰው ለማግኘት ቀላል እንደሆነ አንዳንድ ሰዎች ከነገሩት በኋላ መሆኑን ገልጿል።

ከዚያም ልጁን የመሸጡ ሂደት በደላላ አማካይነት የተመቻቸ ሲሆን ታዳጊውን ለመሸጥ የተደረገው ስምምነት የሰው ልጅ ሽያጭ መሆኑ እንዳይታወቅም በሻጭና በገዢ መካከል በሚደረገው ድርድር ወቅት የሚሸጠው ሰው ሳይሆን ዶሮ እንደሆነ እየተጠቀሰ ነበረ።

ነገር ግን ፖሊስ ጥቆማ አግኝቶ ባደረገው ክትትል ታዳጊውን የገዙት ሰዎች ልጁን ሊወስዱ ከሞንሮቪያ ወጣ ብሎ ከሚገኝ ከተማ እየመጡ ሳለ አባትየው በቁጥጥር ሥር ውሏል።

የላይቤሪያ የበይነ መረብ የዜና ምንጭ የሆነው 'ግሎባል ኒውስ ኔትወርክ' እንደዘገበው ሊሸጥ የነበረው ልጅ በአሁኑ ጊዜ ጉዳዩ በሚመለከተው የአገሪቱ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ጥበቃ ሥር ይገኛል።

በተመሳሳይ ከጥቂት ሳምንታት በፊት እዚያው ላይቤሪያ ውስጥ አንዲት የ26 ዓመት እናት የአምስት ወር ጨቅላ ልጇን ለአንዲት ለማታውቃት ሴት በ60 ዶላር ሸጣለች በሚል በሕገ ወጥ የሰው ዝውውር ተጠርጥራ በፖሊስ ተይዛ ጉዳይዋ በፍርድ ቤት እየታየ መሆኑ ተዘግቧል።

ላይቤሪያና ሴራሊዮን በሚገኙበት በምዕራባዊው የአፍሪካ ክፍል የሰዎች ዝውውር ዋነኛ አሳሳቢ ችግር ነው።

በእነዚህ አገራት ውስጥ ህጻናት ለዘመናዊ ባርነት የሚሸጡ ሲሆን ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዳይገናኙ ይደረጋል። ልጆቹ በአብዛኛው ከባድ የቤት ውስጥ እና የጉልበት ሥራ እንዲያከናውኑ ይደረጋል።