ከጣሊያን ወደ ሕንድ በተደረገ በረራ ላይ የተሳፈሩ ከ100 በላይ ሰዎች ኮሮና ተገኘባቸው

የፎቶው ባለመብት, RAVINDER SINGH ROBIN
በቻርተር በረራ ከጣልያን ተነስተው በህንድ ሰሜን ክፍል በሚገኘው አምሪሳር ከተማ የደረሱ 125 መንገደኞች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተረጋግጧል።
ቫይረሱ የተገኘባቸው ተጓዦች ወደ ለይቶ ማቆያ እንደሚገቡም የጤና አስተዳደር ሰዎች ተናግረዋል።
ቫይረሱ የተገኘባቸው ተጓዦች ከአንድ ቀን በፊት ከጣልያን ሚላን ተነስቶ አምሪሳር ባረፈው በረራ ላይ ከነበሩ 179 ተሳፋሪዎች መካከል ነበሩ።
ትላንትና ሃሙስ ህንድ ከ90 ሺህ በላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን የመዘገበች ሲሆን ይህም ከባለፈው ሳምንት ወደ ስድስት እጥፍ የሚጠጋ ብልጫ ያለው ነው። ባለሙያዎች የዚህ ምክንያቱ ኦሚክሮን የተሰኘው ዝርያ የመዛመት ፍጥነት ነው ብለዋል።
ሕንድ በ24 ሰዓት ውስጥ 325 ሰዎች በኮሮናቫይረስ ምክንያት መሞታቸውን መዝግባለች። ከዚህ ውስጥ አንድ ሰው ብቻ ከኦሚክሮን ዝርያ ጋር በተያያዘ መሞቱን ታውቋል።
በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩ ህጻናት እና ጨቅላዎች በተደረገላቸው ምርመራ ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸውን ዘገባዎች ጠቁመዋል። ሆኖም ምርመራ ከተደረገላቸው 160 መንገደኞች ውስጥ 125ቱ በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።
አምቡላንሶች ከአየር ማረፊያው ውጭ ተሰልፈው በቫይረሱ ተያዙትን ተሳፋሪዎች ሲወስዱ ታይተዋል።
ባለሥልጣናት የኦሚክሮን ዝርያ በሕንድ ከተሞች ላይ ዋነኛ ችግር ነው ያሉ ሲሆን በሰፊው መሰባሰብ መቅረት አለበት ብለዋል።
በሕንድ ማሃራሽትራ፣ ዌስት ቤንጋል፣ ዴሊ፣ ኬራላ፣ ታሚል ናዱ፣ ካርናታካ እና ጃርክሃንድ ግዛቶች በየሳምንቱ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች እና የመያዝ ምጣኔው በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመሩ ለሀገሪቱ "አሳሳቢ ሁኔታ" ተደርጎ ተወስዷል።
ሕንድ እስካሁን ከ35 ሚሊየን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ኮሮና እንደተያዙ ያረጋገጠች ሲሆን ወደ 482 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በቫይረሱ መሞታቸውን አስታውቃለች።












