የኢትዮጵያ መንግሥት የሂዩማን ራይትስ ዋች ሪፖርትን 'ፈጠራ' ሲል አጣጣለ

አምባሰደር ዲና ሙፍቲ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኢትዮጵያ መንግሥት ከሳዑዲ አረቢያ የተመለሱ የትግራይ ተወላጆች እስርና እንግልት ገጥሟቸዋል ሲል የሰብአዊ መብቶች ተቆርቋሪው የሂዩማን ራይትስ ዋች ያወጣውን ሪፖርት አጣጣለ።

ስለሪፖርቱ ተጠይቀው ምላሽ የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ይህ የሂዩማን ራይትስ ዋች ክስ "ፈጠራ" ነው ሲሉ አጣጥለውታል።

"ሂዩማን ራይትስ ዋች ኢትዮጵያን የተመለከቱ በርካታ ድርሰቶች አሉት" ያሉት አምባሳደር ዲና፤ ይህ ሪፖርት "ከድርሰቶቹ መካከል አንዱ ነው" ብለዋል።

ዓለም አቀፉ የመብት ተሟጋች ቡድን ሂዩማን ራይትስ ዋች ከሁለት ቀናት በፊት ባወጣው ሪፖርት የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በቅርቡ ከሳዑዲ አረቢያ የተመለሱ በሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆችን ከሕግ ውጪ አስረው በደል ፈጽመውባቸዋል ብሎ ነበር።

የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቱ ከሳዑዲ የተመለሱት የትግራይ ተወላጆች እስር፣ መንገላታት እና የደረሱበት እንዳይታወቅ መደረጋቸውን አመልክቶ የሳዑዲ መንግሥትም ስደተኞቹን የሚይዝበትን አስከፊ ሁኔታና ወደ ኢትዮጵያ መመለሱን እንዲያቆም ጠይቋል።

የሚኒስቴሩ ቃል አቃባይ ዲና ሙፍቲ በሰጡት መግለጫ፣ የተቋሙ ሪፖርት "በኢትዮጵያ ላይ እየተደረጉ ያሉ ጫናዎች አካል ነው" ብለዋል።

ሂዩማን ራይትስ ዋች ከሳዑዲ አረቢያ ተመላሽ የሆኑ የትግራይ ተወላጆች የገጠማቸውን እንግልት በተመለከተ 23ቱን ማናገሩን ጠቅሶ ለወራት በአዲስ አበባ፣ በአፋር ሰመራ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ሾኔ፣ በኦሮሚያ ጅማ ውስጥ በሚገኙ የማቆያ ቦታዎች ተይዘው መቆየታቸውን ነግረውኛል ብሏል።

የሰብአዊ መብት ድርጅቱ በሪፖርቱ ላይ እንዳለው ጉዳዩን በሚመለከት ምላሽ ለማግኘት ለአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን፣ ለፌደራል ፖሊስ፣ ዋሽንግተን ለሚገኘው የሳዑዲ ኤምባሲ እና ለሳዑዲ የአገር ውስጥ ሚኒስቴር በደብዳቤ ቢጠይቅም ምላሽ አለማግኘቱን ገልጿል።

ስለሂዩማን ራይትስ ዋች ሪፖርት የኢትዮጵያ መንግሥት ምላሽን የተጠየቁት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ "በሰፈር፣ በማንነት የተለየ እና የተጎዳ ሰው አልነበረም። እንደዚያ አይነት አሰራርም አልነበረም" ሲሉ አስተባብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በሳዑዲ አረቢያ ውስጥ ሕገወጥ ተብለው በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ጥረት እያደረገ መሆኑን የገለጸ ሲሆን፣ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በሺዎች የሚቆጠሩት ወደ አገራቸው ተመልሰዋል።

አንድ ዓመት ያስቆጠረው ትግራይ ውስጥ የተቀሰቀሰው ጦርነት መባባሱን ተከትሎ በአዲስ አበባና በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች ውስጥ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች እንግልትና እስር እያጋጠማቸው መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንን ጨምሮ የተለያዩ የመብት ተቋማት በሪፖርቶቻቸው አመልክተዋል።

ከዚህ ቀደም መንግሥት በመዲናዋ እና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ሰዎች በቁጥጥር ስር የሚውሉት በማንነታቸው ምክንያት ሳይሆን ከሕገ ወጥ ቡድኖች ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ተጠርጥረው መሆኑን መግለጹ ይታወሳል።