ስለኮቪድ-19 የጻፉትን ተከትሎ ትዊተር የአወዛጋቢዋን አሜሪካዊት ፖለቲከኛ ገጽ አገደ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ትዊተር የአወዘጋቢዋን አሜሪካዊት ፖለቲከኛ ማርጆሪ ቴይለር ግሪን የግል ገጽ ማገዱን አስታወቀ።
የሪፐብሊካ ፓርቲ አባልና የአሜሪካ ሕግ አውጪ ገጻቸው የታገደባቸው የትዊተርን ሕግጋት በመተላለፋቸው፣ በተለይ ደግሞ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን አስመልክተው የሚለጥፉት መልዕክት አደጋ ሊያስከትል የሚችል በመሆኑ ነው ሲል ድርጅቱ ገልጿል።
ትዊተር ከዚህ በፊት የፖለቲከኛዋን ገጽ አራት ጊዜ በጊዜያዊነት ማገዱ የሚታወስ ነው።
የአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክርት ቤት አባል የሆኑት ማርጆሪ ቴይለር ግሪን ኩባንያው "የአሜሪካ ጠላት ነው" ሲሉ ገጻቸው በመዘጋቱ የተሰማቸውን በጠንካራ ቃላት ገልፀዋል።
ቴሌግራም በተሰኘው የማኅበራዊ ትስስር መድረክ ላይ ረዘም ያለ መግለጫ የለጠፉት ፖለቲከኛዋ "ማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች እውነቱን ማፈን አይችሉም" ብለው ትዊተር "የኮሚዩኒስት አብዮትን እያገዘ ነው" ሲሉ ወቅሰዋል።
ምንም እንኳ የአዋዘጋቢዋ ፖለቲከኛ የግል ገጽ ይዘጋ እንጂ ኦፊሴላዊ የኮንግረስ ገጻቸው ግን አሁንም እየሰራ ሲሆን፣ እዚህ ገጽ ላይ መልዕክት የሚለጥፉት ለሥራው የተመደቡ ሙያተኞች ናቸው።
የ47 ዓመቷ ማርጆሪ ቴይሌር ግሪን ባለፈው ቅዳሜ "አሜሪካ ውስጥ በርካታ ክትባት የወሰዱ ሰዎች እየሞቱ ነው" ሲሉ ያልተረጋገጠ ወሬ ማጋራታቸው ነው ገጻቸውን እንዲዘጋ ያደረገው።
የጆርጂያ ግዛት ሕዝብ እንደራሴዋ ከትዊተር የታገዱት የኮሮናቫይረስ የተሳሳተ መረጃ ፖሊሲን "በተደጋጋሚ በመጣሳቸው ነው" ሲሉ የትዊተር ቃል አቀባይ ለቢቢሲ በጽሑፍ አሳውቀዋል።
ቃል አቀባዩ እንደሚሉት ኩባንያው አራት ጊዜ ሕግ ጥሰው የሚገኙ ሰዎችን ገጽ በጊዜያዊነት ያግዳና ቆይቶም በቋሚነት ሊያግድ ይችላል።
"ሰዎች በተደጋጋሚ ጥፋት አጥፍተው ሲገኙ ገፃቸውን እስከወዲያኛው እናግዳለን" ብለዋል አፈ ቀላጤው።
ባለፈው የአሜሪካ ምርጫ ድምፅ አግኝተው ወደ ዋሺንግተን የመጡት ግሪን በአወዛጋቢ ድርጊታቸው ይታወቃሉ።
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ቀንደኛ ደጋፊ የሆኑት ግሪን፤ ትራምፕ ባለፈው ምርጫ አልተሸነፉም ምርጫው ተጭበርብሮ እንጂ ከሚሉት መካከል ናቸው።
አልፎም ሴትየዋ 'ኪውኤነን' ከተባለው የነጭ አሜሪካዊያን የሴራ ፅንሰ ሐሳብ አራማጅ ድርጅት ጋር ስማቸው ሲያያዝ ይሰማል።
ፖለቲከኛዋ፤ ምንም እንኳ አገራቸው አሜሪካ በቫይረሱ ምክንያት 825 ሺህ ሰዎች ብታጣም ቫይረሱን ለመከላከል የሚደረጉ እርምጃዎችን አጥብቀው በመቃውም ይታወቃሉ።
የክትባቶችን የመከላከል አቅም በተደጋጋሚ ሲወቅሱ የሚደመጡት ማርጆሪ ቴይለር ግሪን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ አልጠቀመም ብለው የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ውስጥ ግርግር እስከመፍጠር ደርሰው ነበር።















