አርጀንቲናዊው የእግር ኳስ ኮከብ ሊዮኔል ሜሲ ኮቪድ-19 ተገኘበት

ሜሲ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ሊዮኔል ሜሲ ኮቪድ-19 ከተገኘባቸው አራት የፓሪስ ሴይንት-ዠርሜይን ተጫዋቾች አንዱ እንደሆነ ታወቀ።

አርንቲናዊው አጥቂ እንዲሁም የቡድን አጋሮቹ የሆኑት ሁዋን በርናት፣ ናታን ቢቱማዛላ እንዲሁም ሰርጂዮ ሪኮ ናቸው ኮቪድ-19 እንደተገኘባቸው የተገለጸው።

ተጫዋቾቹ ቡድናቸው ፒኤስጂ በፍሬንች ካፕ ፍልሚያ ከቫኔስ ጋር ሊጫወት ሲሰናዳ ነው ውጤታቸው የተነገራቸው።

አራቱም ተጫዋቾች ራሳቸውን አግልለው የጤና ሁኔታቸውን እየተከታተሉ ነው።

የፒሴስጂው አሠልጣኝ ሞሪሲዮ ፖቼቲኖ እንዳሉት ሜሲ ለበዓል እረፍት ወደ አገር ቤት ስለሄደ የኮቪድ-19 ምርመራ ውጤቱ ኔጋቲቭ እስኪሆን ድረስ እዚያው ይቆያል።

ከጨዋታው በፊት እንደተለመደው ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት ፖቼቲኖ አክለው ሜሲ መቼ ሊመለስ ይችላል የሚለውን መገመት እንደሚያዳግታቸውም ተናግረዋል።

ፒኤስጂ ከፍሬንች ካፕ ሲመለስ ከበዓል እረፍት በኋላ በሚቀጥለው እሑድ ሊዮንን ይገጥማል።

ሌላኛው የክለቡ አጥቂ ብራዚላዊው ኔይማር ካጋጠመው ጉዳት ስላላገገመ በዚህ ጨዋታ የመሳተፉ ነገር አጠራጣሪ ሆኗል።

ፒኤስጂ የ29 ዓመቱ ኔይማር በሚቀጥሉት ሦስት ሳምንታት ወደ ሜዳ ሊመለስ ይችላል ተብሏል።

የፈረንሳይ ሊግን እየመራ የሚገኘው ፒኤስጂ በቻምፒዬንስ ሊግ ፍልሚያ በጥሎ ማለፍ ጨዋታ ከሪያል ማድሪድ ጋር ይፋለማል።

አርጀንቲናዊው አጥቂ ሜሲ በፈረንሳይ ሊግ ብዙም እየተሳካለት አይደለም።

ሜሲ እስካሁን በሊጉ ያስቆጠረው አንድ ጎል ነው። በቻምፒዬንስ ሊግ ደግሞ በምድብ ጨዋታ አምስት ጎሎችን በስሙ አስመዝግቧል።