"ኮሮናቫይረስ በአዲሱ ዓመት ይረታል የሚል ተስፋ አለኝ" ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የዓለም የጤና ድርጀት ዋና ኃላፊ ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም የዓለም አገራት በጋራ የሚሠሩ ከሆነ ኮሮናቫይረስ በአዲሱ የአውሮፓዊያኑ አዲስ ዓመት 2022 ይረታል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ገለጹ።
የዓለም የጤና ድርጅት በቻይና የተቀሰቀሰውን ቫይረስ በተመለከተ ሪፖርት ከደረሰው ሁለተኛ ዓመቱ በተቆጠረበት በዚህ ወቅት አዲሱን ዓመት በማስመልከት በሰጡት መግለጫ "ጠባብ ብሔርተኝነት እና ክትባትን ማከማቸት" አደጋ ናቸው ሲሉም አስጠንቅቀዋል።
እስካሁን በመላው ዓለም በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ287 ሚሊዮን የተሻገረ ሲሆን ከ5.5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።
ዶ/ር ቴድሮስ አሁን ላይ ኮሮናቫይረስን ለማከም የተሻሉ መንገዶች መኖራቸውን ገልጸው፣ ፍትሐዊ የሆነ የክትባት ክፍፍል ባለመኖሩ ቫይረሱ ቅርጹን እየቀያየረ እንዲከሰት ዕድል ፈጥሯል ብለዋል።
"በአንዳንድ አገሮች ጠባብ ብሔርተኝነት እና የክትባት ክምችት ፍትሐዊነትን አጓድሏል። እናም ለኦሚክሮን ዝርያ መፈጠር ተስማሚ ሁኔታዎችን ፈጥሯል። ቫይረሱ እየተለዋወጠ በመጣ ቁጥር የመቆጣጠር እና የመተንበይ አቅማችን እየቀነሰ ይሄዳል" ያሉት ዶ/ር ቴድሮስ "ኢ-ፍትሐዊነትን ከገታን ወረርሽኙን እንገታዋለን" ሲሉም አክለዋል።
በአውሮፓ እና በአሜሪካ ሰዎች ቢያንስ አንድ ዙር የኮሮናቫይረስ ክትባት የወሰዱ ሲሆን የዓለም የጤና ድርጅት የአውሮፓዊያኑ 2021 ከመጠናቀቁ በፊት በመላው ዓለም ቢያንስ 40 በመቶ ሕዝብ ክትባት እንዲያገኝ ያቀደው ዕቅድ በተለይም በአብዛኛው የአፍሪካ አገራት ሳይሳካ ቀርቷል።
ዶ/ር ቴድሮስ ከዚህ ቀደም የበለፀጉ አገራት የዓለም አቀፍ የክትባት አቅርቦትን "በማግበስበስ" አብዛኛው ሕዝባቸውን ሁለት ዙር ሲከትቡ ሌሎች የመጀመሪያውን ዙር ክትባት እየተጠባበቁ ይገኛሉ በማለት ወቅሰዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት ለመጪው አዲስ ዓመት 2022 ባስቀመጠው አዲስ ግብ፣ ወረርሽኙን ለማጥፋት በሁሉም አገራት ቢያንስ እስከመጪው ነሐሴ ድረስ 70 በመቶ ክትባቱን ለማዳረስ አቅዷል።












