የፕሪሚየር ሊግ ተጫዋቾች የኮቪድ ክትባት እንዲወስዱ በመንግሥትና በሊጉ ተጠየቁ

የዌስት ብሮም ተጫዋች ካለም ሮቢንሰን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የዌስት ብሮም ተጫዋች ካለም ሮቢንሰን መከተብ እንደማይፈልግ ጥቅምት ወር ላይ አሳውቆ ነበር

የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ እና የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) መንግሥት የእግር ኳስ ተጫዋቾች የኮቪድ-19 ክትባትን እንዲወስዱ አሳሰቡ።

በሳምንቱ መጨረሻ ሊደረጉ የነበሩት የከፍተኛ ሊግ ጨዋታዎች ግማሾቹ ክለቦች ላይ እንደ አዲስ በተቀሰቀሰው ወረርሽኝ ምክንያት ለሌላ ጊዜ ተላልፏል።

25 በመቶ የሚሆኑ ተጫዋቾች ክትባት የማግኘት ፍላጎት እንደሌላቸው በመግለጻቸው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ቅዳሜ ሊደረጉ የታቀዱ 19 ጨዋታዎች ተሰርዘዋል።

የዩኬ የስፖርት ሚኒስትር ኒጄል ሃድልስተን "ክትባት መውሰድ ማኅበራዊ ኃላፊነት ያለበት ተግባር ነው" ብለዋል።

"እግር ኳስ ተጫዋቾችን ጨምሮ ማንኛውም ሰው እራሱን፣ ባልደረቦቹን እና የሚወዳቸውን ሰዎች ከቫይረሱ ለመጠበቅ ማድረግ የሚችለው እና በጣም ወሳኙ ነገር ክትባት መውሰድ እና ማጠናከሪያ ክትባት ማግኘት ነው" ብለዋል ሚኒስትሯ።

"አንዳንድ ተጫዋቾች ለምን ክትባት ለመውሰድ እንደሚያመነቱ ለመረዳት የእግር ኳስ አመራሮች ከተጫዋቾች ጋር እየሰሩ መሆናቸውን አውቃለሁ" ሲሉም አክለዋል።

የሊቨርፑሉ አስልጣኝ የርገን ክሎፕ ክትባቱን መውሰድ ግዴታ መሆን አለበት ብለው የሚያምኑ ሲሆን "ከሥነ ምግባር አንጻር" 99 በመቶ የሚሆኑት የቡድናቸው አባላት ሁለቱንም ዙር ክትባት ወስደዋል።

ዋናው "የማሳመን ጉዳይ ነው" ነው የሚሉት አሰልጣኙ "በዙሪያዬ ያሉትን ሰዎች የሚረዳ አንድ ነገር ካደረግኩ እንደ ግዴታዬ እወስደዋለሁ። አንዳንድ ሰዎች ግን ይህንን በተለየ መንገድ እንደሚያዩት ግልጽ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

"እኔ 54 ዓመቴ ነው እናም ሰዎችን ስለ ትክክለኛ ነገሮች ማሳመን እንደምችል በትልቁ አምናለሁ። ነገር ግን በዚህ ልዩ ጉዳይ ላይ ሰዎችን ማሳመን እንደምችል እርግጠኛ አይደለሁም" ሲሉም አክለዋል።

በጥቅምት ወር የታተመ አንድ የፕሪሚየር ሊግ መረጃ 81 በመቶ የሚሆኑት የሊጉ ተጫዋቾች ቢያንስ አንድ ጊዜ የተከተቡ ሲሆን 68 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ሁለት ዙር ክትባት አግኝተዋል።

በመላው ዩናይትድ ኪንግደም 89 በመቶ የሚሆኑት ከ12 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎች የመጀመሪያውን ክትባት ወስደዋል፣ 82 በመቶዎቹ ደግሞ ሁለተኛውን ዙር የወሰዱ ሲሆን 44 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ የማጠናከሪያ ክትባት አግኝተዋል።

በዩኬ ያልተከተቡ ሰዎች በኮሮናቫይረስ ከተያዘ ሰው ጋር የቅርብ ግንኙነት ካላቸው ለ10 ቀናት ራሳቸውን ማግለል እንዳለባቸው መንግሥት ያወጣው ሕጋዊ መመሪያ ያዛል።

የፕሪሚየር ሊጉ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሪቻርድ ማስተርስ ሁሉም የሊጉ ክለቦች ተጫዋቾቻቸውን እንዲከተቡ "አበክረው እንዲያበረታቱ" በደብዳቤ ጠይቀዋል።

"የክትባትን አስፈላጊነት በጋራ አስምረንበታል እናም ከዚህ የበለጠ አስፈላጊ የሆነ ነገር የለም" ሲሉ አስፍረዋል።

ጨምረውም ኃላፊው "እባካችሁ ሙሉ በሙሉ ያልተከተቡት ክትባቱን እንዲወስዱ አጥብቃችሁ አበረታቷቸው። የኦሚክሮን ዝርያን ብቸኛው የመከላከያ ሽፋን የሆነውን ማጠናከሪያ እንዲያገኙም አበረታቷቸው" ሲሉ ጠይቀዋል።

አንዳንዳንዶች በክትባቱ ውጤታማነት ላይ እምነት በማጣት፣ ሌሎች ደግሞ የጎንዮሽ ጉዳቶችን ወይም መርፌን መፍራትን ጨምሮ በርካታ ምክንያቶችን በመጥቀስ አለመከተብን ይመርጣሉ።

በቁጥር አነስ ያሉ ሌሎች ደግሞ ከኢንተርኔት በተለይም በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በሚያገኟቸው የተሳሳቱ መረጃዎች እና የሴራ ትንታኔዎች ምክንያት ክትባት አይወስዱም።