በአፍሪካ ዋንጫ የሚታደሙ ተመልካቾች የተከተቡና ከቫይረሱ ነጻ መሆን አለባቸው ተባለ

ያለፈው የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ የአልጄሪያ ቡድን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኢትዮጵያን ጨምሮ 24 አገራትን የወከሉ ቡድኖች የሚሳተፉበት እና በጥር ወር በካሜሩን በሚካሄደው የአፍሪካ እግር ኳስ ዋንጫ ላይ መታደም የሚችሉት የኮቪድ-19 ክትባትን ሙሉ ለሙሉ የወሰዱ እና ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸው የሚያረጋገጡ ደጋፊዎች ብቻ መሆናቸውን አዘጋጆቹ አስታወቁ።

የካሜሩን መንግሥት እና የእግር ኳስ ማኅበሩ እንዲሁም የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በጋራ ባወጡት መግለጫ ውድድሩ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከጥር 9 እስከ የካቲት 6 ባለው ጊዜ ውስጥ እንደሚከናወን አረጋግጠዋል።

በዚህ ውድድር 24 ቡድኖች የሚሳተፉ ሲሆን በእግር ኳሱ ዓለም እውቅና ያላቸው እንደ ግብፃዊው መሐመድ ሳላህ፣ ሴኔጋላዊው ሳዲዮ፣ አልጄሪያውያኑ ማህሬዝ እና ሪያድ ማህሬዝን የመሳሰሉ ተጨዋቾች ይሳተፉበታል።

መግለጫው "የካሜሩን መንግሥት ለአፍሪካ ዋንጫ ልዩ የጥንቃቄና እና ፀረ-ኮቪድ መመሪያ አዘጋጅቷል" ሲል ገልጿል።

"ደጋፊዎች ለአፍሪካ ዋንጫ ግጥሚያዎች ወደ ስታዲየም መድረስ የሚችሉት ሙሉ በሙሉ ከተከተቡ እና በ72 ወይም በ24 ሰዓታት ውስጥ በተደረገ ምርመራ ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸውን የሚያሳይ ሰነድ ካቀረቡ ብቻ ነው" ተብሏል።

"በውድድሩ ወቅት በሁሉም የውድድሩ ስፍራዎች ላይ ክትባቶችን እና የኮቪድ ምርመራዎችን ለማመቻቸት የጤናው ዘርፍ ባለሥልጣናት አስፈላጊውን ሁሉ እርምጃዎች ይወስዳሉ" ሲልም መግለጫው አክሏል።

በአሁኑ ጊዜ 2 በመቶው የሚሆነው የካሜሩን ሕዝብ ሙሉ በሙሉ የተከተበ መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ።

በወረርሽኙ ምክንያት ለአንድ ዓመት የዘገየው የአፍሪካ ዋንጫ የካሜሩን ዋና ከተማን ያውንዴን ጨምሮ በአምስት ከተሞች ይካሄዳል።

ከአንድ ሳምንት በፊት የአውሮፓ ክለቦች ማኅበር አዲሱ የኦሚክሮን ኮሮናቫይረስ መምጣት እና "ለሕዝብ ጤና አሳሳቢ ሁኔታ" መከሰቱን ተከትሎ የተጫዋቾች ደኅንነትን በተመለከተ ያለውን "ጥልቅ ስጋት" ገልጿል።

በአዲሱ የቫይረስ ዝርያ ምክንያት ውድድሩ በዚህ ወር ሊራዘም ወይም ቦታ ሊቀየር ይችላል የሚሉ ወሬዎች የተናፈሱ ቢሆን ካፍ ባለፈው ሳምንት ለቢቢሲ ስፖርት አፍሪካ ወሬው ሐሰት ነው ብሏል።

ባለፈው ረቡዕ የካፍ ኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን ሉክስ ሴፕቴምበር የአፍሪካ ዋንጫ ሊሰረዝ ይችላል ለሚል አንድ ዘገባ በሰጡት ምላሽ "ውሸት" ሲሉ ተችተዋል።

ካፍ በትላንት መግለጫው ደግሞ ውድድሩ እንደታቀደው እንደሚከወን ያለውን ፍላጎት በድጋሚ ገልጿል።

"ይህ ወረርሽኙ የሚያስከትለው ተጨማሪ ፈተና ቢኖርም የአፍሪካ ዋንጫ መከናወኑ ግን የግድ ነው" ሲል አክሏል።

"ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የኮቪድ ወረርሽኝን ለመግታት ተገቢ እና በቂ እርምጃዎችን እንድንወስድ ይጠይቃል። ይህም ከባዱን እና ትክክለኛ አደጋ እንድንጋፈጥ ነው" ያለው መግለጫው "ነገር ግን ህይወት መቀጠል አለባት ከቫይረሱ ጋር እንዴት መኖርን እንዳለብን መማር አለብን" ሲል አክሏል።