ኦሚክሮን ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ፍጥነት እየተሰራጨ ነው- የዓለም ጤና ድርጅት

ክትባት በደቡብ አፍሪካ

የፎቶው ባለመብት, AFP

አዲሱ የኮሮናቫይረስ ልውጥ አሚክሮን በዓለም ላይ ታይቶ በማይታወቅ ፍጥነት እየተሰራጨ ነው ሲል የዓለም ጤና ድርጅት አስጠነቀቀ።

ይህ ልውጥ ዝርያ በ77 አገራት ውስጥ መኖሩ ተረጋግጧል።

ነገር ግን በጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ገብረእየሱስ እንዳሉት ምናልባት እስካሁን ያልታወቁ በሌሎች አገራት ውስጥ ሊኖር ይችላል ብለዋል።

ዶክተር ቴዎድሮስ ልውጡን ዝርያ ለመጋፈጥ በቂ ስራ አለመሰራቱ እንዳሳሰባቸው ተናግረዋል።

"በእርግጥ እስካሁን ድረስ ይህ ቫይረስ የጋረጠውን አደጋ አቅልለን እንደምንመለከተው ተረድተናል ። ምንም እንኳን ኦሚክሮን ብዙም የከፋ በሽታ ባያመጣም፤ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ብዛት እንደገና ያልተዘጋጁ የጤና ስርዓቶችን ሊያሽመደምድ ይችላል" ብለዋል።

ኦሚክሮን የተሰኘው ልውጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው በደቡብ አፍሪካ በህዳር ወር ላይ ሲሆን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በሃገሪቱ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር አሳይቷል።

የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ባደረጉት ምርመራ በኮቪድ-19 መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም ከሚታይባቸው ቀለል ካሉ ምልክቶች ለማገገም ራሳቸውን ለይተው ይገኛሉ።

ኦሚክሮን መከሰቱን ተከትሎ ደቡብ አፍሪካን እና ጎረቤቶቿን የሚጎዳ የጉዞ እቀባ በርካታ ሃገራት ቢጥሉም ይህ ግን በመላው አለም እንዳይስፋፋ ማድረግ አልቻለም።

በትናንትናው ዕለት፣ ማክሰኞ ዶክተር ቴድሮስ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አንዳንድ ሃገራት ለኦሚክሮን ምላሽ ለመስጠት የክትባት መርሃ ግብራቸውን ያጠናከሩ ሲሆን ከዚህም ጋር ተያይዞ ስለ ክትባት ኢ-ፍትሃዊነት ያላቸውን ስጋት በድጋሜ አንፀባርቀዋል።

የቅርብ ጊዜ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የፋይዘር ክትባት በኦሚክሮን ላይ ከዋናው ዝርያ ሲነፃፀር ውጤታማነቱ በጣም ያነሰ ቢሆንም ይህ ጉድለት በሶስተኛና በማበረታቻ ክትባት ሊቀለበስ እንደሚችል አሳይቷል።