ኮቪድ- 19፡ በአሜሪካ በወረርሽኙ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ800 ሺህ አለፈ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተከሰተ ጀምሮ ከ800 ሺህ በላይ አሜሪካውያን በቫይረሱ ሳቢያ ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን ይህም በዓለም ከተመዘገበው የሞት ቁጥር ከፍተኛው ነው ተባለ።
ሰኞ ዕለት በአሜሪካ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ቁጥርም 50 ሚሊየን መድረሱ ተገልጿል።
አብዛኛዎቹ ሞቶች የተመዘገቡት ባልተከተቡና እድሜያቸው በገፉ ሰዎች ነው።
አብዛኞቹ አሜሪካውያን በወረርሽኙ ሳቢያ የሞቱት ከ2020 ይልቅ እየተጠናቀቀ ባለው የአውሮፓውያኑ 2021 መሆኑ ተነግሯል።
በአሜሪካ በድጋሜ በሚያስደነግጥ ፍጥነት የሞት ቁጥር እየጨመረ መጥቷል።
የመጨረሻዎቹ 100 ሺህ ሰዎች ሞቶች የተመዘገቡት ባለፉት 11 ሳምንታት ውስጥ ሲሆን ይህም ካለፈው ክረምት በበለጠ ከፍተኛ ጭማሬ እና ፍጥነት የታየበት ነው።
በጆንስ ሆፕኪንስ ብሉምበርግ የኅብረተሰብ ጤና ትምህርት ቤት ኢፒዲሚዮሎጂስት የሆኑት ዶ/ር ኬሪ አልቶፍ " በሕዝብ ደረጃ የበሽታ መከላከል አቅም ከፍተኛ እስከሚሆን ድረስ የምናያቸው የወረርሽኙ ማዕበሎች ይቀጥላሉ" ብለዋል።
በሲያትል ዋሽንግተን የመጀመሪያው አሜሪካዊ የኮቪድ ታማሚ ሕይወቱ ካለፈ ከ650 ቀናት በላይ ሆኗቸዋል።
ለመጀመሪያ ጊዜ በአሜሪካ የፀደቀው የፋይዘር ክትባት ባለፈው ክረምት አንስቶ መሠጠት ከጀመረ ወዲህ 300 ሺህ የሚጠጋ ተጨማሪ ሞት ተመዝግቧል።
ሚያዝያ ወር ላይ ሁለት ተጨማሪ ክትባቶች ማለትም ሞደርና እና ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን በአሜሪካ ፈቃድ ያገኙ ሲሆን ሦስቱም ክትባቶች በሁሉም የእድሜ ክልል ለሚገኙ አዋቂዎች ቀርበዋል።
በአገሪቷ የተመዘገበው 800 ሺህ የሞት ቁጥር እንደ ቦስተን እና ዋሺንግተን ዲሲ ካሉ ከተሞች የሕዝብ ቁጥር የሚበልጥ ነው።
በ2ኛው የዓለም ጦርነት ከሞቱት አሜሪካውያንም በወረርሽኙ የሞቱት በእጥፍ የሚቆጠሩ ናቸው።
የአሜሪካ የሞት ቁጥር በዓለም ካሉ ሌሎች አገራትም እጅግ የላቀ ነው።
በብራዚል ከ616 ሺህ በላይ ሞት የተመዘገበ ሲሆን ከአሜሪካ በመቀጠል በሟቾች ቁጥር በሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
በሦስተኛ ደረጃ ላይ ደግሞ የተቀመጠችው ሕንድ ስትሆን ከ475 ሺህ በላይ የኮቪድ ሞት ተመዝግቦባታል።
እንደ ጆስን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ ከሆነ በዋና ከተሞቻቸው በተመዘገበው የሞት ቁጥር ደግሞ አሜሪካ ከዓለም በ20ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ከአሜሪካ በቀዳሚነት የተዘረዘሩት የደቡብ አሜሪካ እና የአውሮፓ አገራት ናቸው።












